ስቅለተ – አምላክ?

ሼር ያድርጉ
499 Views

ሲጀምር “ሀ” ብሎ ፍጥረት
አባት አዳም በገነት
በነጻ ምድር- ነጻ ህይወት
ሁሉ ሃላል በሆነበት
ሁሉ ነገር በበቃበት
ከዛፊቱ በስተቀር…
ካሻው ሊያምቧትር
ተፍቅዶለት እንዲኖር
ሳይደክም ሳይታትር
ከዚህም ከዚያም እንዲቃርም
በአበቦቿ ሊምነሸነሽ በፍሬዎቿ ሊጣቀም
ከወንዞቿ ሊጎነጭ ከመብሏ ሊያጣጥም
ሲበረከት ሁሉ ለሱ -እሱ ለሁሉም
ለካስ ከሰው ጋር ነው ተድላም!!!
ከሰው ጋር ነው ሐሴት- ከሰው ጋር ነው ለቅሶም!!!
እናም አባት አዳም…
ጭርታው ሲደቁሰው አብዝቶ
የዘፍጥረት ላጤነቱ …ጎምርቶ
ሲኖር በተየለሌው ዓለም ብቸኝነቱ በርትቶ
በድንገት አምላክ ጩኸቱን ሰምቶ
“ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም
የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት”
ብሎ… ወዲያው…
በአዳም የእንቅልፍን ናዳ ንዶ
ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ
ስፍራውን በሥጋ ሞልቶ
ሴት አድርጎ አስውቦ ሰርቶ
ወደ አዳም ሲያመጣት በድንገት…
የደም-ገንቦ-የውበት ጥግ ተምሳሌት
ሃዋ- የህልቆ-መሳፍርት እመቤት
ያኔ…ህልሙ እውን ሆኖ ሲከሰት
አቤት የኣዳም አበሳ…!!!
ልቡ ከሞተበት ሲነሳ
ኤደንን ከሃዋ አመዛዝኖ
ጸጋዋን ሁሉ አብልሎ-አብኖ
ስለ ሃዋ ተሸከፈከፈ
በማለዳ ፍቅሯ ተሸንፈ
ስጋውም ደከመ-ሳሳ
ኤደንን ጨርሶ እስኪረሳ
አቤት ምታሃታዊነቱ!!!
እነሆ ህይወትን ከምንም ጀምረው ከርመው ሳይቦርቁ
ተንኮለኛው እባብ፦…ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ ራቁ
የሚል ብርቱ ትዕዛዛ ደርሷችኻ̱ልን?
ሴቲቱም፡- በገነት ከዛፍ ሁሉ ለቅመን መብላት እንችላለን
ነገር ግን እንዳንሞት -መቀመቅ እንዳንወርድ-የማቅ ልብስ እንዳንለብስ
ከበለሷ ፍሬ ነክተን እንዳንበልስ
ከወድያኛዋ ዛፍ ብንሰያም እንዳንቀጥፍ-ሞትን እንዳናተርፍ
ተከልክለናል ላንደርስባት
ለዝንተ-ዓለሙ ላናልማት
አለች…ፈራ-ተባ-ሆዷ እየባባ
እባቡም ደለላት…”የበላችሁ ለት”
“ሞትንማ አትሞቱም”… እያለ አባበላት
ዓይኖቻችሁ በርተው መልካሙን ከክፉ
ለይታችሁ አውቃችሁ
አማላክን መስላችሁ-አምላክን ሆናችሁ
እንዳትኖሩ ሰግቶ… ነው “ተው” ያላችሁ
ሲላት እባቡ… ከመቅጽበት…
ሃዋ አግደመደመች
ቀምሳ መጠበብን ከጀለች
ቀጥፋ ለራሷ… ለባሏም እንካ አለች
ያኔ አምላክ ተቆጥቶ
እርግማኑን በርሱም በርሷም ላይ አብዝቶ
ሲያባራቸው ከዔደን ምሎ
“በላብህ ጥረህ” ልትበላ ብሎ
በቃጤ መሬት ሊትኮሮኮር
ሲጣል..ሲገፈተር…ወደ ምድር-ለምድር
ቃል ገባለት ባፈ-ነቢብ -ባፈ-ታሪክ
ከልጅ ልጁ ተወልዶ በራሱ ልክ-በራሱ መልክ
ሊታደጋው ከሞት-ኃጢአት-ከዕዝናት
ሊበዥ ፍጥረተ-ዓለሙን
በ”ልጁ” እጅ የጎደፈውን
እንዳቀደ ነገረው…
የሰራውን ኃጢአት አንድ ቀን ሊምረው
እናም ቀኑ ደረሰና
“አምላክና” አዳም ዛሬም ከእንደገና
ሊታረቁ ከአምላክ ጋር -በአምላክ ደም
“ሲወለድ ከልጅ ልጁ” ከመሬም
.
.
.
በአጓጉል እምነት ወ ክህደት
በብኤልዜቡል መይሎታል ትዕቢት
የገዛ ወገኖቹ ሸሹት-አበሉት
ይቀጥልና ትርክቱ…
“አምላክ” ለሮማውያን ተላለፈ
ድብደባው በዛ… “እግሩም” አንከፈከፈ
“መስቀል” ተሸክሞ… ከድካው ደረሰ
ከብርቱ ጩኸት ጋር እንባው ረሰረሰ
ጸለየ ለራሱ- ወደ አልተሰቀለው-ከዙፋኑ ላለው…
ድረሱልኝ ምነው…
እኔስ ፈርቻለሁ!!!
“ላማ ሰበቅታኒ” …ይችን ጽዋ አንሳ
አውጣኝ ከአበሳ…ወይ ነፍሴን አትርሳ
ስሞት ከአነተ አኑራት
ሰይጣን “እንዳይነካት”
ብሎ ተመጻነ…ብሎ ለማመነ
የ”ዓለሙ ቤዛ” ድምጹ እየቀጠነ
አባትና መንፈስ- ሁለቱ ላይ ያሉት
ያበረታው እንደሁ መልአክ ሰደዱለት
መልአክ “ከአምላኩ” ወደ “አምላክ” ተልኮ
አንዣቦ …አንዣቦ ከእግሩ ተንበርክኮ
አበረታው ከሞት
መራራውን ቅጽበት
መለኮተ-ስጋ ከነፍስ ተላቀቀ
የአዳምና “አባት” ጸብ ፈቀቀ-ራቀ
“አባት” ይቅር አለ ቃል-ኪዳኑን ሞላ
ኩነኔም በነነነ ጽድቅ እንደ አሸን ፈላ
“ኃጢአት ተሰረየ ልጅም ከደም ጸዳ”
“አምላክ ሞቶ..ሞቶ ቀብሩን ገነበረ
እያዩት አርጎ ከአባቱ ጎን ኖረ
(ተጻፈ በወረሃ ነሃሴ 2008)