ሴቶችን ምቱ! የሚል ትእዛዝ በኢስላም የለም!

ሼር ያድርጉ
441 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው

ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

ለዛሬ የማስቃኛችሁ፡- ቅዱስ ቁርኣን ሚስቶቻችሁን ምቱ! በማለት ያዛል፡ ስለሆነም ሴቶች ተበድለዋል የሚለውን ቅጥፈት ነው፡፡ ለዚህ ክሳቸውም ተከታዩን የቁርኣን ክፍል ዋቢ አድርገው አቅርበዋል፡-

“ወንዶች በሴቶች ላይ ቋሚዎች (አሳዳሪዎች) ናቸው፤ አላህ ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ በማብለጡና (ወንዶች) ከገንዘቦቻቸው (ለሴቶች) በመስጠታቸው ነው። መልካሞቹም ሴቶች (ለባሎቻቸው) ታዛዦች አላህ ባስጠበቀው ነገር ሩቅን ጠባቂዎች (ክብራቸውንና ንብረታቸውን የሚጠብቁ) ናቸው። እነዚያንም ማመጣቸውን የምትፈሩትን ገሥጹዋቸው፤ በመኝታዎችም ተለዩዋቸው፣ (ሳካ ሳታደርሱ) ምቱዋቸውም። ቢታዘዙዋችሁም (ለመጨቆን) በነርሱ ላይ መንገድን አትፈልጉ። አላህ የበላይ ታላቅ ነውና።” (ሱረቱ-ኒሳእ 4:34)፡፡

በዚህ ቅዱስ አንቀጽ ውስጥ‹‹(ሳካ ሳታደርጉ) ምቷቸውም›› የሚለውን ኃይለ-ቃል ቆንጥሮ በማውጣት፡ ኢስላም ሴቶችን ምቱ ይላል ወደሚል ድምዳሜ ደረሱ፡፡ ይህ ለኛ የሚያሳየን በኢስላም ጉዳይ ውስጣቸው ምን ያህል እንደተቃጠለና፡ ለኢስላም እንዴት አይነት የከፋ ጥላቻ እንዳላቸው ነው፡፡ እንዴት እንደሆነም በምላሹ ውስጥ እንመለከተዋለን፡፡ ለዚህ የከፋ አስተሳሰብ ያለን ኢስላማዊ ምላሽ በመጠኑም ቢሆን እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

1ኛ. ኢስላም በትዳር ዓለም ውስጥ በባልና ሚስት መሀከል መልካም ግኑኝነት እንዲኖር ያዛል፡፡ በተለይ ባሎችን ለየት ባለ መልኩ ሚስቶቻቸውን በመልካም አንዋኗር እንዲያስቀምጧቸው ይመክራል፡፡ በዚሁ ሱራ ላይ የሚገኘው የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-

“እላንተ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! ሴቶችን ያስገደዳችሁ ሆናችሁ ልትወርሱና ግልፅን መጥፎን ስራ ካልሠሩ በስተቀር ከሰጣችኋቸው ከፊሉን ልትወስዱ፣ ልታጉላሏቸውም ለናንተ አይፈቀድም፤ በመልካምም ተኗኗርሩዋቸው፤ ብትጠሉዋቸውም (ታገሡ)፤ አንዳችን ነገር ልትጠሉ አላህም በርሱ ብዙ ደግ ነገርን ሊያደርግ ይቻላልና።” (ሱረቱ-ኒሳእ 4:19)፡፡

በዚህ አንቀጽ ውስጥ ከምናገኛቸው ቁም ነገሮች መሐከል፡-

ሀ. ዐረቦች ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) መላክ በፊት ያደርጉት እንደነበረው ልማድ፡ ሴትን ልጅ ባሏ ሲሞት ያለ ፈቃዷ እሷን እንደ ንብረት ቆጥሮ መውረስና በግዳጅም ማግባት እንዲሁም ላልፈለገችው ሰው መዳር እጅግ የተወገዘ መሆኑን፡፡

ለ. ከተሰጣቸው የመህር ገንዘብ ላይ ግልጽ የሆነ ዝሙትን ፈጽመው ካልተገኙ በስተቀር ልትወስዱባቸውና ልታጉሏሏቸው እንደማይገባ

ሐ. በመልካም አንዋኗር ልናሮራቸው እንደሚገባና

መ. እነሱን የምንጠላበት ምክንያቶች ቢከሰቱ እንኳ መታገስ እንደሚገባንና፡ የተወሰነ የምንጠላበት ነገር ቢኖርም አላህ በምትኩ ብዙ የተሻለ ነገርን ሊያደርግልን እንደሚችል እንማራለን፡፡

ነቢዩ ሙሐመድም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በትምህርታቸው ላይ የትኛውም እምነት ውስጥ ልናገኘው የማንችለውን ነገር እንዲህ በማለት አስተምረውናል፡-

عَنِ ابْنِ عَبَّاسٍ رضي الله عنهما عَنِ النَّبِىِّ صلى الله عليه وسلم قَالَ « خَيْرُكُمْ خَيْرُكُمْ لأَهْلِهِ وَأَنَا خَيْرُكُمْ لأَهْلِى ». ابن ماجه1977: الترمذي 3895: صحيح ابن حبان 4177.
ዐብደላህ ኢብኑ-ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደነገሩን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ከናንተ መሐል በላጭ ማለት ለሚስቱ መልካም የሆነ ሰው ነው፡፡ እኔ ለሚስቶቼ መልካም ሰው በመሆኔ በላጫችሁ ነኝ” (ኢብኑ ማጀህ 1977፣ ቲርሚዚይ 3895፣ ሶሒሕ ኢብኑ ሒባን 4177)፡፡

2ኛ. ክስ ወደ ቀረበበት ጥቅስ ስንመለስ አንቀጹ የሚጀምረው መልካም ሚስቶችን በማወደስና በማላቅ እንጂ ‹‹ግረፏቸው›› በማለት አይደለም፡፡ ጥቅሱ የሚናገረው፡-
“…መልካሞቹም ሴቶች (ለባሎቻቸው) ታዛዦች አላህ ባስጠበቀው ነገር ሩቅን ጠባቂዎች (ክብራቸውንና ንብረታቸውን የሚጠብቁ) ናቸው…” በማለት ነው፡፡

ጌታቸውን አላህን የሚታዘዙ፡ ባለቤታቸውን በሐቁ ትእዛዙን የሚጠብቁ፡ እሱ ከነሱ ሲርቅ (ለዳዕዋም ሆነ ለስራ በወጣበት) ደግሞ ብልታቸውንና ንብረቱን የሚጠብቁት ‹‹መልካሞች›› ናቸው አለ እንጂ ‹‹ምቷቸው›› አላለም፡፡ ታዲያ ይህን አንቀጽ ለምን መዝለል ተፈለገ? ነገሩ ልብ ከታወረ አይነ-ስጋ ቢመለከት ምን ይጠቅማል? አላህም በቃሉ እንዲህ አይደል ያለው፡- “…እነሆ ዓይኖች አይታወሩም ግን እነዚያ በደረቶች ውስጥ ያሉት ልቦች ይታወራሉ።” (ሱረቱል ሐጅ 22:46)፡፡

3ኛ. እነዚህን መልካም ሚስቶች ካወደሰ በኋላ ደግሞ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እነዚያንም ማመጣቸውን የምትፈሩትን ገሥጹዋቸው፤ በመኝታዎችም ተለዩዋቸው፣ (ሳካ ሳታደርሱ) ምቱዋቸውም።››፡፡ አሁን አንቀጹ የሚናገረው ስለ ‹አመጸኛ ሴቶች› (ሚስቶች) እንደሆነ ያስተውሉ፡፡ ‹‹ሴቶችን›› ብሎ በጥቅሉ መልካሞቹንም ሌላውንም ለመፈረጅ መሞከር በውስጥ የታመቀ የጥላቻ ስሜትን ከመግለጽ ውጪ ምንም ለባለቤቱ የሚጠቅመው ነገር የለም፡፡ እንደዛም ሆኖ የሚገርመው ነገር እነዚህን ‹‹አመጸኛ ሴቶች›› ወደ ትክክለኛው ባሕሪያቸው ለመመለስ ቁዱስ ቁርኣን ‹‹መምትን›› የመጀመሪያ መፍትሄ አድርጎ አልወሰደም፡፡ በዚህ አንቀጽ ላይ ብቻ እንኳ ብንመለከተው ሶስት መፍትሄዎችን ነው የጠቆመው፡፡ እነሱም፡-

ሀ. ‹‹ገሥጹዋቸው››:– ይህ የመጀመሪያው እርምጃ ነው፡፡ ኢስላም በተግሳጽ ስለሚያምን ማለት ነው፡፡ ተግሳጽ (መውዒዟህ) ማለት፡- ልብ ድረስ ዘልቆ ሊገባ የሚችል፡ ህሊናን የሚኮረኩር ምክርና ንግግር ማለት ነው፡፡ ስድብና ዘለፋ ያልታከለበት ማለት ነው፡፡ ሙጃሂድ ኢብኑ ጀብር (ረሒመሁላህ) የተባሉት ታቢዒይ እንደገለጹትም፡- ‹‹አላህን ፍሪና ተመለሺ: በሐቄ ታዘዢኝ ይበላት›› ነው ማለት የሚገባው (ተፍሲሩ-ጠበሪይ ሱረቱ-ኒሳእ 34፡ ቁ 9343)፡፡

ወደ አላህ መንገድ ስንጣራ አንዱ አካሄድ በመልካም ግሳጼ መሆኑን ቅዱስ ቁርኣን ሲጠቁመን ‹‹አል-መውዒዟህ›› በሚል ቃል ነው የተጠቀመው (ሱረተ-ነሕል 16:125)፡፡ ስለዚህም አመጸኛዋን ሚስትህን ምከራት፡ ገስጻት ተባልክ እንጂ ምታት አልተባልክም፡፡ መልካም፡፡ በዚህ መልኩ ካልተመለሰችና ካልታረመችስ ቀጣዩ እርምጃ ምንድነው?

ለ. ‹‹በመኝታዎችም ተለዩዋቸው››:– ይህ ሁለተኛው እርምጃ ነው፡፡ በመኝታ መለየት ሁለት ነገሮችን ያቅፋል፡፡ የመጀመሪያው፡- በአንድ ፍራሽ ላይ ሁነህ ግን ጀርባ በመስጠት ማኩረፍህን መግለጽ ሲሆን፡ ሁለተኛው ደግሞ፡- ፍራሽ በመለየት ለብቻህ ተኛ የሚለው ነው፡፡ ቤት ለቀህ ግን እንዳትወጣ! ተከልክለሀልና፡፡ ሚስት ባለቤቷ እሷን ጀርባ ሰጥቶ መተኛቱ ወይም ፍራሽ መለየቱ ለሷ ትርጉም አለው፡፡ መለየቱም አያስችላትም፡፡ ስለዚህ ከዚህ አመጸኛ ባሕሪዋ ተጸጽታ ትመለስ ዘንድ የባል ኩርፊያ አጋዥ ነው፡፡ አሁንም ደግማ ከዚህ ባሕሪዋ የማትመለስ ከሆነስ ቀጣዩ እርምጃ ምንድነው?

ሐ. ‹‹(ሳካ ሳታደርሱ) ምቱዋቸውም››:– የሚለው ነው፡፡ በጣም ከገረመኝ ድፍረታቸው ደግሞ (ሳካ ሳታደርጉ) የሚለው የአማርኛው የቅዱስ ቁርኣን ትርጉም ላይ ጭማሪ ያስገቡት ነው ማለታቸው ነው፡፡ አወቅሽ አወቅሽ ቢሏት… የተባለው ተረት ለናንተ ነበር ማለት ነው?

ለማንኛውም ይህ በቅንፍ የገባው ገላጭ ቃል ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐይሂ ወሰለም) ንግግር የተወሰደ ማብራሪያ እንጂ የተርጓሚዎች የግል ሀሳብ አይደለም፡፡ በሐጀቱል ወዳዕ (የመሰናበቻው ሐጅ) ላይ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ካስተላለፉት ሰፊ ትምሕርት ላይ የተወሰደ ነው፡፡ በዚህ የቅዱስ ቁርኣን አንቀጽ ውስጥ ‹‹ምቷቸው›› ለሚለው ቃል ምን አይነት መምታት? የሚል ጠያቂ ቢመጣ ምላሹ ይህ ይህ ይሆናል፡-

“…اتَّقُوا اللَّهَ فِى النِّسَاءِ فَإِنَّكُمْ أَخَذْتُمُوهُنَّ بِأَمَانَةِ اللَّهِ وَاسْتَحْلَلْتُمْ فُرُوجَهُنَّ بِكَلِمَةِ اللَّهِ وَإِنَّ لَكُمْ عَلَيْهِنَّ أَنْ لاَ يُوطِئْنَ فُرُشَكُمْ أَحَدًا تَكْرَهُونَهُ فَإِنْ فَعَلْنَ فَاضْرِبُوهُنَّ ضَرْبًا غَيْرَ مُبَرِّحٍ وَلَهُنَّ عَلَيْكُمْ رِزْقُهُنَّ وَكِسْوَتُهُنَّ بِالْمَعْرُوفِ… ” صحيح مسلم 1218: سنن أبي داود 1907
“… እናንተ ሰዎች ሆይ! በሴቶች ጉዳይ አላህ ፍሩ! እናንተ እነሱን በአላህ አደራ ነው የወሰዳችኋቸው፣ ብልቶቻቸውንም በአላህ ቃል (በመልካም ያዙዋቸው በሚለው) ነው ሐላል ያደረጋችሁት፣ እናንተም በነሱ ላይ በቤቶቻችሁ የማትፈልጉትን ሰው እንዳያስገቡ የመከልከል መብት አላችሁ፡፡ እምቢ ብለው ይህን ካደረጉ፡ ህመም የማያስከትልና ያልበረታ ምትን ምቷቸው፡፡ እነሱም በናንተ ላይ ሲሳያቸውን ልትችሉ፣ ልብሳቸውን በአግባቡ ልትሸፍኑ መብት አላቸውና…” (ሙስሊም 1218፣ አቡ ዳዉድ 1907)፡፡

የአማርኛ ቅዱስ ቁርኣን ተርጓሚዎችም በቅንፍ ውስጥ (ሳካ ሳታደርጉ) የሚለውን ከራሳቸው ሳይሆን የጨመሩት፡ የታላቁን ነቢይ የቁርኣን ማብራሪያ በመውሰድ ነው፡፡

4ኛ. አሁንም ‹‹ምቷቸው›› የሚለውን፡- በቀበቶና አለንጋ፣ በዱላና በከዘራ ነው በማለት የተንሸዋረረ ምልከታን ሰዎች እንዳይነዙ ታላቁ የቅዱስ ቁርኣን ተንታኝ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ብሎ አብራራው፡-

عن عطاء قال: قلت لابن عباس: ما الضرب غير المبرّح؟ قال: السواك وشبهه، يضربها به. تفسير الطبري سورة النساء 34: 9386
አጣእ ኢብኑ የሳር (ረሒመሁላህ) እንዲህ አለ፡- ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስን አገኘሁትና ‹‹ህመምን ያላስከተለና ያልበረታ ምት ምንድነው?›› አልሁት፡፡ እሱም፡- ‹‹በሲዋክና (መፋቂያ) በመሳሰለው መምታት ነው›› አለኝ፡፡ (ተፍሲሩ-ጠበሪይ፡ ሱረቱ-ኒሳእ 34፡ ቁጥር 9386)፡፡

አሁንስ ምን ይዋጣችሁ፡፡ አያችሁ! የምቱ ዓላማና ግብ አመጸኛዋ ሚስት አደብ እንድትይዝ እንጂ እሷን ለመጉዳት እንዳልሆነ ግልጽ ሆነላችሁ?

5ኛ. ደግሞም ኢስላም የተከበረውን ፊት ከመምታት እንድንቆጠብ ያዘናል፡፡ ተከታዩ ሐዲሥም ይህን ያብራራዋል፡-

وعَنْ مُعَاوِيَةَ بن حَيْدَة الْقُشَيْرِيِّ قَالَ : ” قُلْتُ : يَا رَسُولَ اللَّهِ مَا حَقُّ زَوْجَةِ أَحَدِنَا عَلَيْهِ ؟ قَالَ : ( أَنْ تُطْعِمَهَا إِذَا طَعِمْتَ وَتَكْسُوَهَا إِذَا اكْتَسَيْتَ أَوْ اكْتَسَبْتَ وَلَا تَضْرِبْ الْوَجْهَ وَلَا تُقَبِّحْ وَلَا تَهْجُرْ إِلَّا فِي الْبَيْتِ .رواه أبو داود ( 2142 ) وصححه الألباني في ” صحيح أبي داود ” .
ሙዓዊያህ ኢብኑ ሐይደቱል ቁሸሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “የአላህ መልክተኛን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አንዳችን ባለቤቱ በሱ ላይ ምን ሐቅ አልላት? አልኳቸው፡፡ እሳቸውም፡- ከምትመገበው ልትመግባት፣ ስትለብስ ልታለብሳት፣ ፊቷን ላትመታት፣ በመጥፎ ንግግር ላትናገራት፣(ካኮረፍካትም) እዛው ቤት ውስጥ ሁነህ እንጂ ላትተዋት›› በማለት መለሱልኝ” (አቡ ዳዉድ 2142)፡፡

6ኛ. አንቀጹ ይቀጥልና ደግሞ፡- ‹‹ቢታዘዙዋችሁም (ለመጨቆን) በነርሱ ላይ መንገድን አትፈልጉ። አላህ የበላይ ታላቅ ነውና።›› በማለት ይዘጋዋል፡፤ አዎ! ወደ ታዛዥነታቸው ከተመለሱ እነሱን ለመጨቆን አላህ ምንም መንገድን አላበጀም፡፡ የበላይነትን ለማሳየት የምንጥር ከሆነ ደግሞ፡ እርሱ ጌታችን አላህ የበላይና ታላቁ አምላክ መሆኑን ማስታወስ እንደሚገባን መከረን፡፡ ይህ ነው የኢስላም አስተምህሮ!!

7ኛ. አሁን ተራው የናንተ ነው፡፡ ኢስላም ሴቶችን ግረፉ ይላል በማለት ‹‹ወደ ገደለው እንግባ›› እንዳለው ሰውዬ: አንድ ቃልን ብቻ ከውስጥ በመምዘዝ ሃይማኖቱን ጥላሸት ለመቀባት የምትሞክሩት፡ በናንተ ዘንድ እንዲህ አይነት አመጸኛ ሴት ስትኖር ምን መፍትሄ መውሰድ እንዳለባችሁ መጽሐፋችሁ ምን ይነግራችኋል? በማለት እኛም እንጠይቃችሁ በተራችን፡፡ እስኪ ከሚናገረው መፍትሔ የምታውቁትን አካፍሉን፡፡ እነዚህን ጥቅሶችስ እንዴት ትፈቱታላችሁ፡-

“ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ከመቀመጥ በውጪ በቤት ማዕዘን ላይ መቀመጥ ይሻላል።” (መጽሐፈ ምሳሌ ምእ 21፡ 9)

“ከጠበኛና ከቍጡ ሴት ጋር ከመቀመጥ በምድረ በዳ መቀመጥ ይሻላል።” (መጽሐፈ ምሳሌ ምእ 21፡ 19)

“ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ከመቀመጥ በሰገነት ማዕዘን መቀመጥ ይሻላል።” (መጽሐፈ ምሳሌ ምእ 25፡ 24)

“በዝናብ ቀን የሚያንጠባጥብ ቤትና ጠበኛ ሴት አንድ ናቸው” (መጽሐፈ ምሳሌ ምእ 27፡ 15)

“ከደረቅ ሴት ጋር ከምትኖር ከምድር አውሬና ከአንበሶች ጋር መኖር ይሻላል” (መጽሐፈ ሲራክ 25፡16)፡፡ (የኦርቶዶክስ መጽሐፍ ቅዱስ)

ወገኖቻችን! ይሄ ነው መፍትሄው? ይህን ይዛችሁ ነው የኛን የምትተቹት?

8ኛ. በመጨረሻም ለነዚህ ወገኖች የምናስተላልፈው መልእክት፡- እባክችሁ በዕድሜያችሁ አትቀልዱ! በእሳት አትጫወቱ! የዘላለም ህይወት የሚገኝበትን ጀነትን ከፈለጋችሁ አንድ አምላክ ብቻ ወደሚመለክበት ኢስላም በፈቃደኝነት ኑ!

አላህን ላላመለከ፡ በነቢዩ ሙሐመድ ነቢይነት ያላመነና በዚሁ ክህደቱ እምቢ ብሎ የሞተ ሰው፡ ጀነት ለርሱ ዝግ ናት፡፤ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ካልሾለከ በስተቀር ወደ ጀነት አይመለስም፡፡ አላህ ሂዳያ ይስጣችሁ ለኛም ጽናቱን ይለግሰን፡፡ ሰላምም ቀጥታን በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን፡፡

“የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በኛና በናንተ መካከል ትክክል ወደሆነች ቃል ኑ፤ (እርሷም) አላህን እንጅ ሌላን ላንገዛ በርሱም ምንንም ላናጋራ፣ ከፊላችንም ከፊሉን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርጐ ላይይዝ ነዉ፤ በላቸዉ። እምቢ ቢሉም ፡- እኛ ሙስሊሞች መሆናችንን መስክሩ በሏቸው” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 64)፡፡

Shortlink http://q.gs/Ey5Kb