‹‹ሴቶቻችሁ ለናንተ እርሻ ናቸው!››

ሼር ያድርጉ
468 Views
እኔ እና እሱ

በአቡ ሀይደር

በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው

እሱ፡- ጤና ይስጥልኝ!
እኔ፡- ጤና ይስጥልኝ!

እሱ፡- መጠየቅ ይቻላል
እኔ፡- አው ይቻላል

እሱ፡- በትክክል ትመልስልኛለህ?
እኔ፡- መልሱን ካወቅሁት አዎ!

እሱ፡- የሱራ 2፡223ን ሀሳብ አስረዳኝ
እኔ፡- በአንቀጹ ላይ ያልገባህ ሀሳብ ምንድነው?

እሱ፡- ‹‹ሴቶቻችሁ ለናንተ እርሻ ናቸው፡፡ እርሻችሁንም በፈለጋችሁት ኹነታ ድረሱ፡፡ ለነፍሶቻችሁም (መልካም ሥራን) አስቀድሙ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ እናንተም ተገናኝዎቹ መኾናችሁን ዕወቁ፡፡ ምእመናንንም (በገነት) አብስር፡፡›› 2፡223
በዚህ አንቀጽ ሥር ሴቶችን እርሻ ብሎ እየጠራቸው ነው፡፡ እሱ ነው ያልገባኝ፡፡
እኔ፡- ሴትን ልጅ በእርሻ መመሰሉ ምኑ ነው ግራ እንድትጋባ ያደረገህ? ወይንስ እርሻ የመጥፎ ነገር ገጽታን ይገልጻል ብለህ ነው?

እሱ፡- እርሻ የመጥፎ ነገርን ገጽታ ይጠቁማል ብዬ ሳይሆን፡ የሴትን ክብር ዝቅ ያደርገዋል የሚል ሀሳብ መጥቶብኝ ነው፡፡
እኔ፡- ሴትን ልጅ በእርሻ መመሰሉ በምን መልኩ ክብሯን ዝቅ እንደሚያደርገው መግለጽ ትችላለህ?

እሱ፡- ሴትን በአፈር መመሰል ለሴት ክብር ነው ብለህ ታምናለህ አንተ?
እኔ፡- አይደለም በአፈር መመሰላችን ይቅርና በትክክልስ ራሳችን አፈር አይደለን እንዴ? ምነው አፈጣጠራችን ከምድር አፈር መሆኑ፣ ነገ የምንመለሰውም ወደዚህ አፈር መሆኑን ዘነጋኸው እንዴ? ታዲያ ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳህ›› (ዘፍ 3፡19)፡፡ የሚለውንስ የመጽሐፍህን ቃል አላነበብከውም?

እሱ፡- እሺ እሱን ተወውና የቁርኣኑን ሀሳብ አስረዳኝ
እኔ፡- የአንቀጹን ትክክለኛ መልእክት ለመረዳት አንቀጹ የወረደበትን ምክንያት ማወቁና መገንዘቡ መልካም ነው፡፡ አንቀጹ የወረደበት ምክንያት የአይሁዶችን የተሳሳተ ግልብ ግንዛቤ ለማስተካከልና፡ ሶሓቦችም (ረዲየላሁ ዐንሁም) በነሱ ስንኩል አስተሳሰብ አብረው እንዳይጠፉ ለማስተማር ነው፡፡ ጉዳዩም፡- አይሁዶች ሴቶቻቸው (ሚስቶቻው) የወር አበባ በመጣባቸው ወቅት፡ አብረዋቸው አይመገቡም፣ አብረው አይተኙም ነበር፡፡ ይህ በወር አበባ ወቅት ሴትን የማግለል ጉዳይ ዛሬም በኦሪት ዘሌዋውያን 15፡19-22 ላይ በግልጽ ሰፍሯል፡፡ ይህን ጉዳይ ሶሓቦች ለነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሲያቀርቡት፡ እንዲህ የሚለው የአላህ ቃልም ምላሽ ሆኖ ወረደ፡-

‹‹ከወር አበባም ይጠይቁሃል፡፡ እርሱ አስጠያፊ ነው፡፡ ሴቶችንም በወር አበባ ጊዜ ራቋቸው፡፡ ንጹሕ እስከሚኾኑም ድረስ አትቅረቡዋቸው፡፡ ንጹሕ በኾኑም ጊዜ አላህ ካዘዛችሁ ስፍራ ተገናኙዋቸው፡፡ አላህ (ከኃጢኣት) ተመላሾችን ይወዳል፤ ተጥራሪዎችንም ይወዳል በላቸው፡፡›› (ቅዱስ ቁርኣን 2፡222)፡፡

በዚህ አንቀጽ መሠረት በወር አበባ ወቅት የተከለከለው የግብረ-ሥጋ ግኑኝነት ብቻ እንጂ፡ ሌላ እንዳልሆነ ተገለጸ፡፡ አብሮ መብላት፣ መሳሳምና መተሸሸት እንዲሁም አብሮ መተኛት (በመተቃቀፍም ቢሆን) የተፈቀደ ነው ተባለ፡፡ ነቢዩ ሙሐመድም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ‹‹ኢስነዑ ኩልለ ሸይኢን ኢልለ-ኒካሕ›› (ከግብረ-ሥጋ ግኑኝነት በስተቀር ሁሉንም ነገር ፈጽሙ) በማለት ጉዳዩን አጠናከሩት ማለት ነው፡፡ (ሙስሊም የዘገበው)።

የቀጣዩ አንቀጽ መውረድ ሰበቡ ደግሞ፡- አይሁዶች ሰው ሚስቱን ከኋላ በኩል ከተገናኛት የሚወለደው ልጅ አይነ ሸውራራ ይሆናል ይሉ ነበር፡፡ ሶሓቦችም ይህን ቃል ይዘው መልክተኛውን ሲጠይቋቸው፡ ቀጣዩ የአላህ ቃል እንዲህ ሲል ወረደ፡-
‹‹ሴቶቻችሁ ለናንተ እርሻ ናቸው፡፡ እርሻችሁንም በፈለጋችሁት ኹነታ ድረሱ፡፡ ለነፍሶቻችሁም (መልካም ሥራን) አስቀድሙ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ እናንተም ተገናኝዎቹ መኾናችሁን ዕወቁ፡፡ ምእመናንንም (በገነት) አብስር፡፡›› (ቅዱስ ቁርኣን 2፡223)፡፡

እርሻ የለምነት ምልክት ነው፡፡ እርሻ ዘር የሚዘራበት ውድ ስፍራ ነው፡፡ እርሻ ለሰዎች፣ ለእንሰሳትና ለበራሪዎች የሕይወት መሠረት የኾነው መብል የሚበቅልበት ስፍራ ነው፡፡ እርሻ ለሀገር እድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ እኛም የዐይን ማረፊያ የሆኑ ልጆችን ከአላህ በኩል የምንለገሰው በሴቶቻችን አማካኝነት ነው፡፡ የወንዱ የዘር ፍሬ ማፍራት የሚችለው በሚስቱ ማኅጸን ስር ሲቀመጥ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ሴቶቻችሁ ለናንተ እርሻ ናቸው›› በማለት፡ ከነሱ የሰው ዘር እንደሚገኝ በእርሻ ምሣሌ መግለጹ ለሴት ክብር እንጂ ውርደት አይደለም፡፡

‹‹እርሻችሁንም በፈለጋችሁት ኹነታ ድረሱ›› በማለት ደግሞ፡ በግንኙነት ወቅት ባልና ሚስት በፈለጉት አይነት ፍቅራቸውን መገላለጽ እንደሚችሉ አስረዳ፡፡ ሰውየው ከፊት ሆነ ከኋላ፣ ከላይ ሆነ ከታች፣ ከቀኝ ጎን ሆነ ከግራ ሁሉም የተፈቀደ ነው፡፡ ዋናው ነገር ያንኑ የእርሻ ስፍራ (ማኅጸን) ሳይለቅ መሆን አለበትና፡፡ አይሁዶቹ እንደሚሉት ባል ሚስቱን ከኋላ ሆኖ ስለተገናኛት የሚወለደው ልጅ አይነ ሸውራራ አይሆንም፡፡ ይህ የነሱ አስተሳሰብ ሸውራራ መሆኑ ነው የሚጠቁመው፡፡

እሱ፡- ‹‹እርሻችሁንም በፈለጋችሁት ኹነታ ድረሱ›› ሲል፡ ከማኅጸን ውጭ በሌላም ስፍራ መገናኘት ይቻላል ማለት ነው?
እኔ፡- በፍፁም! አንቀጹ የሚለው ‹‹እርሻችሁን›› ነው፡፡ ዘር የሚዘራበትና ፍሬውም የሚበቅልበት እርሻ ደግሞ ማኀፀን ነው፡፡ ከዛ ውጭ ያለው ዘር የማይገኝበት በመሆኑ፡ በሱ በኩል መገናኘት አይፈቀድም፡፡ ነቢዩ ሙሐመድም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ በማድረግ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በወር አበባ ላይ ያለችን ሴት የተገናኘ፣ ሴትን ልጅ ከቆሻሻ መውጪያ በኩል የተገናኛት፣ ጠንቋይን በሚያወራው እውነት ብሎ ያመነ በርግጥም በሙሐመድ ላይ በወረደው ክዷል (ከሀዲ ሆኗል)›› (አሕመድ 9279፣ አቡ ዳዉድ 3904፣ ቲርሚዚይ 135)፡፡
በጣም የሚገርመው ግን፡ መጽሐፍ ቅዱስ አንድም ስፍራ ላይ ይህንን ድርጊት በቀጥታ አለማውገዙ ነው!

እሱ፡- የቱን ድርጊት?
እኔ፡- ሴትን ልጅ ከቆሻሻ መውጪያ ስፍራ መገናኘት! ልክ ዛሬ ምእራባውያን እንደሚፈጽሙት ማለት ነው፡፡ እስኪ በብሉይ ወይም በአዲስ ኪዳን ላይ ይህን ተግባር የሚኮንን አንድ ጥቅስ አቅርብልኝ!

እሱ፡- ወገኔ! ኢየሱስ ጌታ ነው! ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ ለኛ የተሰጠ ሌላ ስም የለም፡፡ በኢየሱስ ጌትነት አንተም ቤተሰብህም ብታምኑ ከዘላለም ሞት ትድናላችሁ፡፡ ቻው ጌታ ይባርክህ!
እሱ፡- ሁላችንንም ሊያድነን የሚችለው እውነተኛው ጌታ አላህ ብቻ ነው፡፡ ያልፈጠረን፣ ነቢያትን በመላክ በነሱ በኩልም መጽሐፍትን በማውረድ ህግና ስርአትን ያልደነገገ፣ በእለተ ሞታችንም ሩኃችንን ከሰውነታችን በመውሰድ ሞትን ያልወሰነ፡ በዕለተ ትንሳኤ እንዴት ሊያድነንም ሆነ ሊቀጣን ይችላል?

ጌታ አላህ ግን የፈጠረን እሱ፣ ነቢያትን በመላክ መለኮታዊ መጽሐፍትን አውርዶ ህግን የደነገገው እሱ፣ ምድራዊ ቆይታችን ሲጠናቀቅ በሞት የሚገድለንም እሱ፣ በዕለተ ትንሳኤም ሕያው በማድረግ ከመቃብር ዓለም የሚቀሰቅሰን እሱ በመሆኑ፡ ህጌን የት አደረሳችሁት? በማለት እኛን ሊተሳሰበን፡ ከዛም በቸርነቱ ሊያድነን ካልሆነም በፍትሐዊነቱ በእሳት ሊቀጣን የሚችለው እሱ ብቻ ነው፡፡ እናም ወዳጄ! አንተም መሰሎችህም ከዘላለም ስቃይና ቅጣት ወደ ዘላለማዊ ተድላና ምቾት መሸጋገር ከፈለጋችሁ፡ በአንድ አላህ ብቸኛ ተመላኪነት አምናችሁ የነቢዩ ሙሐመድን ነቢይነት መስክራችሁ በኢስላም ጥላ ሥር ልትኖሩ ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ ምንም መዳኛ አልነበረም! የለምም! አይኖርምም! ቻው አላህ ቅኑን ጎዳና ይምራህ!
‹‹ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለውም፡፡ እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው፡፡›› (ቅዱስ ቁርኣን 3፡85)፡፡

Shortlink http://q.gs/Ey5Jm