ሰላቱ-ተራዊሕ “ቂያሙ-ለይል”

ሼር ያድርጉ
497 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኛ በሆነው፡፡

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡

በአላህ ፈቃድ ከዛሬ ምሽት ጀምሮ የረመዷን ሶላቱ-ተራዊሕ (ቂያሙ-ለይል) ይሰገዳል፡፡ ለማስታወስ ያህል ነው፡፡ ብዙ ጌዜ ወደ መስጂድ በመሄድ ከዒሻ ሱንነቱል-ባዕዲያ በኋላ የሚሰገደውን ሶላት (ቂያሙ-ለይል) ከኢማሙ ጋር አንጨርሰውም፡፡ መሐል ላይ እናቋርጣለን፡፡ ወይም ተራዊሕ ጨርሰን ዊትሩን ለቤት ብለን እንወጣለን፡፡፡ ይህ ተግባር የተከለከለ ባይሆንም አግባብነት የለውም፡፡ ለሊቱን ሙሉ በሶላት እንደቆመ እንዲታሰብለት የሚፈልግ አንድ ሙስሊም ከኢማሙ ጋር ሁሉንም አብሮ መጨረስ አለበት፡፡ በመሐል ያለ-ምንም አስገዳጅ ምክንያት ኳቋረጠ ቃል የተገባለትን አጅር ያጣል፡፡ ሐዲሡ የሚለው እንዲህ ነው፡-

አቢ ዘር (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ከኢማሙ ጋር እስኪያጠናቅቅ አብሮት የቆመ(የሰገደ) ለሊቱን ሙሉ እንደሰገደ ይጻፍለታል” (ነሳኢይ 1605፣ ቲርሚዚይ 806፣ ኢብኑ ማጀህ 1327)፡፡

በዚህ ምክንያት ሁሉንም ከኢማሙ ጋር ማጠናቀቅ ይገባናል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ደግሞ፡- በተጨማሪ ለሊት ላይ ተነስቼ ከሰሑር በፊት መስገድ ስለምፈልግ ነው ዊትሩን የተውኩት ይላሉ፡፡

አላህ ወፍቆት ለይል ላይ በድጋሚ ተነስቶ መስገድ የሚፈልግ ሰውም ተራዊሕን እስከ ዊትሩ ከኢማሙ ጋር አብሮ መስገዱ አይከለክለውም፡፡ ‹‹ከዊትር በኋላ ሶላት የለም!›› ወይም ‹‹የመጨረሻ ሶላታችሁን ዊትር አድሩጉ›› የሚለው ሐዲሥ፡ ክልከላን ሳይሆን አለመስገዱ የተወደደ መሆኑን ለማመላከት የመጣ እንደሆነ የኢስላም ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አንዳንድ ጊዜ ከዊትር በኋላ ረከዐተይን (ሁለት ረከዓህ) ይሰግዱ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም የሚጠቁመው ከዊትር በኋላ ሶላት መስገድ እንደሚቻል ነው፡፡ ስለዚህ ለይልን በድጋሚ ተነስተህ የምትሰግድ ከሆነ ባለ ጥንድ ረከዓህ (ሁለት ሁለት) እያደረግህ ስገድ፡፡ በድጋሚ ግን ዊትር እንዳትሰግድ፡፡ በአንድ ለሊት ሁለት ዊትር የለምና፡፡

ሌላው በተራዊሕ ወቅት በጁዝእ የሚሰገድባቸው መስጂድ ውስጥ ከሆንክ፡ ቁርኣን ወይም ሞባይልህ ውስጥ የጫንከውን ከፍተህ ኢማሙን ከምትከታተል፡ ሞባይልህን አጥፍተህ ቀልብህን ሰብስበህ የኢማምህን ቂርኣት በማዳመጥ መከታተሉ ላንተ በላጭ ነው፡፡ ምክንያቱም፡-

1ኛ. ቀኝ እጅን በግራ ላይ ደርቦ በደረት ላይ አሳርፎ የማስቀመጡ ሱንና አያመልጥህምና፡፡ ቁርኣኑን ወይም ሞባይሉን ከፍተህ የምትከታተል ከሆነ ግን የግድ ቀኝ እጅህ ካረፈበት ቦታ ይነሳል፡፡

2ኛ. አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን ትቆጥባለህ፡፡ ኢማሙ ጨርሶ ወደ ሩኩዕ ሲወርድ አንተ ግን፡ ሞባይልህን ወደ ኪስ ለመክተት፡ ቁርኣን ከሆነ ደግሞ መሬት ለማስቀመጥ ቦታ ፍለጋ ውስጥ ትገባለህ፡፡ ቁርአንን ደግሞ ከስሩ ምንም ነገር ሳይኖር መሬት ማስቀመጥ አግባብ አይደለምና፡፡

3ኛ. በሞባይል ቁርኣን እየተከታተልክ፡ ምንም ስልክህ ሳይለንት ቢሆንም ሰው ከደወለልህ ቁርኣኑን ሸፍኖ የደዋዩን ቁጥር ማሳየቱ አይቀርም፡፡ ስልኩን በመዝጋት ስራ ተጠምደህ አንተም አዛ ልትሆን ነው፡፡ ልብህም ከሶላቱ ወጥቶ (ኤጭ ምን አይነቱ ነው!) የሚል ስራ ውስጥ ሊገባ ነው፡፡ ታዲያ የቱ ይሻልሀል?

ሶስቱ ታላላቅ የኢስላም ሊቃውንቶች (ኢብኑ ዑሠይሚን፣ ኢብኑ ባዝ፣ አልባኒ ራሕመቱላሂ ዐለይሂም) በዚህ ጉዳይ ላይ ክልክል ነው ብለው ባያወግዙም በላጩ ግን መተዉ ነው በማለት መክረዋል፡፡

4ኛ. እኔ ከሞባይል ወይንም ዋናውን ቁርኣን ከፍቼ ካልተከታተልኩ እንቅልፍ ይመጣብኛል፡፡ ነሻጣዬም ይጠፋል፡፡ ድካም ድካም ይሰማኛል፡፡ ቀልቤ ከሶላት ይወጣል፡፡ ስከታተል ግን የበለጠ እጠነክራለሁ ምትሉ ካላችሁ ደግሞ፡- ታላቁ ዓሊም ሸይኽ ኢብኑ ጅብሪን (ረሒመሁላህ) ችግር የለውም መጠቀም ይችላሉ በማለት ፈትዋ ሰጥተዋል፡፡ ራሳችንን የምናውቀው እኛው ነን፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ሰው እየደወለ አዛ እንዳያደርገን የሞባይሉን ኔትወርክ ኦፍላይን እናድርገው፡፡ ወይም call setting ውስጥ በመግባት ወደሌላ ቁጥር divert እናድርገው፡፡ ወይም ሲስተሙን ቢዚ አድርጉት፡፡

ደግሞም ‹‹ኢንና አዕጠይና ፣ ለወገብ ጤና›› እያልን በጁዝእ ከሚሰገድባቸው መስጂዶች አንራቅ፡፡ ዛሬ በዚህ ዱንያ ላይ እግሮችህ ለአላህ መቆምን ካበዙ፡ በምትኩ ነጌ በአኼራ በቃጠሎው ቀን መቆሙ ይቀንስላቸዋልና፡፡ አላህ ይወፍቀን፡፡

ለእህቶች፡-

‹‹የአላህን ሴት ባሪያዎች ከአላህ ቤት (መስጂድ) መሄድን አትከልክሏቸው›› የሚለውን ስለ-መብታችሁ የተነገረውን ሐዲሥ ምርኩዝ አድርጋችሁ ከእህቶቻችሁ ጋር በኅብረት ለመስገድ ወደ አላህ ቤት ካቀናችሁ ቀጥሎ ያሉትን ነገራት አደራ ተጠንቀቁ፡-

1. ሒጃባችሁን ጠብቁ፡- ከቤት ስትወጡ ብቻ ሳይሆን፡ መስጂድ ገብታችሁ እስክትሰግዱ፡ ሰግዳችሁም ወደ ቤት እስክትመለሱ ድረስ ሒጃባችሁ ጥብቅ ይሁን፡፡ ወንዶችን የሚፈትን አይነት አለባበስ ለብሳችሁ አትውጡ፡፡ አላህን ፍሩ፡፡ ደግሞም ሽቶ ተቀብታችሁ አትውጡ፡፡ ለማነው የምትዋቡት? ውበታችሁና መዓዛችሁ ለባለቤታችሁ እና ለግላችሁ እንጂ ውጪ ላለ ሰው መሆን ስለሌለበት ከቤት ስትወጡ ተጠንቀቁ፡፡

2. ሰልፍ ማስተካከል፡- አንደኛው ችግራችሁ ነው ይባላል፡፡ (ባለቤቴ እንደነገረቺኝ)፡፡ ሶላት ላይ ተራርቃችሁ ሳይሆን ተጠጋግታችሁ፡ እግር ለእግር ተነካክታችሁ ስገዱ፡፡ በመሐል ሸይጣን እንዳይገባባችሁ ክፍተት አትፍጠሩ። ምነው በረመዷን ታስሮ አይደል? ካላችሁም፡ አዎ! አመጸኞቹ ታስረዋል፡፡ ሽሜዎቹ ግን ዕድላቸውን ይሞክራሉና ክፍተት አትፍጠሩላቸው፡፡ መስጂዱ ስላልሞላ በሚል ተበታትናችሁም አትስገዱ፡፡

3. ህጻናትን በተቻለ መጠን መስጂድ አታምጧቸው፡፡ እናንተም እህቶቻችሁም በነሱ ሰበብ አዛ እንዳትሆኑ፡፡ ማምጣቱ ግድ ከሆነና ሰውን አዛ የሚያደርጉ ከሆነም ተገንጥላችሁ ስገዱ፡፡

4. የመጣችሁበት ዓላማ ዒባዳ እስከሆነ ድረስ ሙሉ ተራዊሕን ከኢማሙ ጋር ስገዱ፡፡ አንዳንዴ ከሁለቱ ኢማሞች በድምጹ ማማር የምንወደው ኢማም ከግማሽ በኋላ ከሆነ እሱ እስኪመጣ ድረስ በማለት ገለል ብለን ቁርኣን መቅራት ወይም እንተኛና እሱ ሲጀምር ቀስቅሱኝ እንላለን፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ የለሊቱን ቂያም ሙሉ አጅር ከፈለግን ሁሉንም እንስገድ፡፡

ወሰላሙ ዐለይኩም ወራሕመቱላህ

Shortlink http://q.gs/EwimX