ረመዷን መጣ!! 1

ሼር ያድርጉ
437 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

ታላቁና ተወዳጁ ነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሶሐቦቻቸውን የረመዷንን መቃረብ አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ ብስራትን ሲገልጹ እንዲህ ይሏቸው ነበር፡- “የተባረከ ወር የሆነው ረመዷን መጣላችሁ!፡፡ አላህ ጾሙን በናንተ ላይ ግዳጅ አድርጓል፡፡ በዚህ ወር የሰማይ ደጃፎች ይከፈታሉ፡፡ የጀሀነም ደጃፎች ይዘጋሉ፡፡ አመጠኛ ሸይጧናት ይታሰራሉ፡፡ አላህ ከአንድ ሺህ ወር (ስራ) የምትበልጥ የሆነች አንድ ለሊት አለችው፡፡ የዚህን ወር መልካም ነገር የተነፈገ ሰው በርግጥም ከብዙ መልካም ነገራት የተነፈገ ነው፡፡” (አሕመድ 7148፣ ነሳኢይ 2106)፡፡
ይህ የነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ብስራት ዋና አላማው ሶሓባዎች ከወዲሁ ይህንን የተከበረ ወር ለመቀበል መንፈሳዊ ዝግጅት እንዲያደርጉ ማነሳሳት ነው፡፡ እኛስ ምን ያህል ተዘጋጅተናል?

ለዛሬ መግቢያ እንዲሆነን ስለ ረመዷን ፈዷኢል (በረከቶች) የተወሰነ ነገር እንነጋገር፡፡

1. የረመዷን ወር ክብር፡-

የረመዷን ወር በኢስላማዊው የወር አቆጣጠር መሰረት፡ ዘጠነኛ ወር ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ ወር ከተቀሩት 11ዱ ወራቶች ለየት የሚያደርገው የራሱ የሆኑ መለያዎች አሉት፡፡ ከነዚህም መለያዎቹ መካከል፡-

ሀ. የጀነት በሮች የሚከፈትበት ወር መሆኑ፡-

የመልካም ስራ መንገዶችና የጥመት ጎዳናዎች በአስራ ሁለቱም ወራት (ሙሉ ዓመት) ለፈላጊዎችና ለሰሪዎች ክፍት ነው፡፡ የአላህ ባሮች ከረመዷን በፊት፣ በረመዷን ውስጥና ከረመዷን በኋላ ባሉት ወራቶች ላይ ወደ ጌታቸው አላህ የሚያቃርባቸውን መልካም ስራ ከመስራት አይቦዝኑም፡፡ የሸይጧን ሰራዊቶች ደግሞ (ተውፊቁን ካላገኙ) ከአላህ የሚያርቃቸውን የጥፋት መስመሮች ከመከተልና ክፋትን ከመፈጸም ወደኋላ አይሉም፡፡ የረመዷን ወር የሚለየው ግን ጀነት ለፈላጊዎቿ ተሸሞንሙና ደጃፎቿ ወለል ብለው ተከፍተው ሲታዩ፡ የጀሀነም በሮች ደግሞ የሚከረቸሙ መሆናቸው ነው፡፡

አቢ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “የረመዷን የመጀመሪው ለሊት ላይ አመጸኛ ሰይጣናት ይታሰራሉ፣ የእሳት በሮች አንድም ሳይቀር ይከረቸማሉ፣ የጀነት በሮች አንድም ሳይቀር ይከፈታሉ፣ በእያንዳንዱ ለሊትም አንድ ተጣሪ እንዲህ በማለት ይጣራል፡- ‹‹መልካም ፈላጊ የሆንክ ሆይ! ፊትህን (ወደ መልካም ተግባር) አዙር፡፡ መጥፎን ፈላጊ የሆንከው ሆይ! (የምትሰራውን ክፋት) ቀንስ(አቁም)፡፡ በያንዳንዱ ለሊትም አላህ ከእሳት ነጻ የሚያደርጋቸው ባሮች አሉት” (አሕመድ 18438)፡፡

ለ. የኃጢአት ማስተሰረያ (ማጥፊያ) መሆኑ፡-

በማንኛውም ወቅት የሚሰራ መልካም ስራና ወደ አላህ የሚደረግ የንሰሀ ተውበት ኃጢአትን ያጠፋል (ሁድ 114፣ አዝ-ዙመር 53)፡፡ የረመዷን ወር ደግሞ በአግባቡ ከተጾመ፡ ቀጣዩ አመት ረመዷን እስኪመጣ ድረስ በመሀከሉ የተፈጸሙ ጥቃቅን ኃጢአቶችን በመላ ያጠፋል፡፡ ትላልቅ ኃጢአቶች (ከባኢረ-ዙኑብ) የግድ ባለቤቱ ተውበት ሊያደርግባቸው ያስፈልጋቸዋልና፡፡
አቢ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “አምስት ወቅት ሶላቶችን መስገድ፣ ጁሙዓ ተሰግዶ ቀጣዩ ሳምንት ጁሙዓህ እስኪመጣ፣ ረመዷን ተጹሞ ቀጣዩ ረመዷን እስኪመጣ ድረስ ሰውየው ትላልቅ ኃጢአትን እስከተጠነቀቀ ድረስ በመሀከላቸው ያለውን ትናንሽ ኃጢአት ያስሰርዛሉ” (ሙስሊም)፡፡

ሐ. የዑምራህ ደረጃህ ከፍ ማለቱ፡-

ከሐጅ ስርዓት ውጪ ዑምራን ብቻ መፈጸም አጅር የሚያስገኝ የሱና (ሙስተሐብ) ተግባር ነው፡፡ በረመዷን የሚፈጸም ከሆነ ግን አጅሩ ከፍ ብሎ በማደግ የሐጅን ምንዳ ያህል ይደርሳል፡፡
ዐብደላህ ኢብኑ-ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “በረመዷን የሚደረግ ዑምራ (ምንዳው) ከሐጅ ጋር ይስተካከላል” (ሙስሊም)፡፡

መ. ቁርኣን የወረደበት ወር መሆኑ፡-

የህይወታችን መመሪያ በመሆን፣ ማን እንደፈጠረን፡ ለምንስ እንደተፈጠርን፣ እንዴት መኖር እንዳለብንና ወደየት እንደምንጓዝ በቂ ምላሽን በመስጠት ማንነታችንን የጠራ መስታወት በመሆን የሚነግረን አምላካዊ ቃል የሆነው ቅዱስ ቁርኣን የወረደው በዚሁ የተከበረ ወር፡ በተከበረች ለሊት፡ በውሳኔዋ ምሽት (ለይለቱል ቀድር) ውስጥ ነው፡፡
“(እንድትጾሙ የተጻፈባችሁ) ያ በርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች (አንቀጾች) ሲኾን ቁርኣን የተወረደበት የረመዳን ወር ነው…” (ሱረቱል በቀራህ 185)፡፡
“እኛ (ቁርኣኑን) በተባረከች ሌሊት ውስጥ አወረድነው፤ እኛ አስፈራሪዎች ነበርንና።” (ሱረቱ-ዱኻን 3)፡፡
“እኛ (ቁርኣኑን) በመወሰኛዪቱ ሌሊት አወረድነው።” (ሱረቱል ቀድር 1)፡፡
ቁርኣን በረመዷን ወር ‹‹ወረደ›› የሚለው ሁለት መልእክትን ያቀፈ ነው፡-

1ኛ፡- ከለውሐል መሕፉዝ (ጥብቅ ሰሌዳ) ወደ ምድራዊ ሰማይ የተከበረው ቤት (በይቱል-ዒዝዛህ) ሲወርድ በጠቅላላ አንድ ጊዜ በዚህ ወር ውስጥ ወርዷል ሲሆን፡-

2ኛ. ከምድራዊው ሰማይ (በይቱል-ዒዝዛህ) ወደ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ልብ በመልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) አማካኝነት ሲወርድ በዚሁ ወር ነው መውረድ የጀመረው ማለት ነው፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡

ሠ. ለይለቱል-ቀድር (የውሳኔው ለሊት) የምትገኝበት ወር መሆኑ፡-

በዚህች አንድ ለሊት የሚሰራ መልካም ስራ አላህ ዘንድ ተቀባይነት ካገኘ፡ የስራው ደረጃ ሰውየው አንድ ሺህ ወራት (83 ዓመት ከ4 ወር) ተቀምጦ ከሚሰራቸው መልካም ስራዎች የበለጠ ይሆናል፡፡ አላህ ይወፍቀን፡፡
“መወሰኛይቱ ሌሊት ምን እንደ ሆነች ምን አሳወቅህ? መወሰኛይቱ ሌሊት ከሺሕ ወር በላጭ ናት።” (ሱረቱል ቀደር 2-3)፡፡

ረ. ቂያሙ ረመዷን (ሶላቱ-ተራዊሕ) የሚገኝበት መሆኑ፡-

በረመዷን ወር ሙስሊሞች ተሰባስበው ከዒሻእ ሶላት በኋላ በጀመዓ የሚሰግዱት ሶላት፡- ቂያሙ ረመዷን (ሶላቱ-ተራዊሕ) ይባላል፡፡
አቢ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “የረመዷንን ወር አምኖና (ምንዳውንም) ነይቶ (በዒባዳ) የቆመ ሰው፡ ከዚህ በፊት የፈጸማቸው (ጥቃቅን) ሃጢአቶቹ በመላ ይማራሉ” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡

ሰ. ኢዕቲካፍ የሚገኝበት ወር መሆኑ፡-

በማንኛውም ቀንና ሰዓት አንድ ሙስሊም የተወሰነ ሰዓታትን በዒባዳ ለማሳለፍ ወስኖ በመስጂድ ውስጥ ኢዕቲካፍ መቀመጥ ይችላል (አል በቀራህ 187)፡፡ በረመዷን ግን ለየት ባለ መልኩ የመጨረሻዎቹን ሙሉ አስር ቀናት በመስጂድ ውስጥ በዒባዳ ለማሳለፍ ራሱን በማገድ (ኢዕቲካፍ) ማድረግ ይቻላል፡፡

አዒሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- “የአላህ ነቢይ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) የረመዷንን የመጨረሻ አስርት ቀናት እስኪሞቱ ድረስ ሁሌም ኢዕቲካፍ ያደርጉ ነበር፡፡ ከሳቸውም ሞት በኋላ ሚስቶቻቸውም ኢዕቲካፍ ያደርጉ ነበር” (ቡኻሪይ)፡፡

ሸ. የቸርነትና የለጋስነት ወር መሆኑ፡-

ቸር መሆን በማንኛውም ቀንና በማንኛውም ሰዓት የተወደደ መልካም ተግባር ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በረመዷን!
ዐብደላህ ኢብኑ-ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ይላል፡- “የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከሰዎች ሁሉ በላይ ቸርና ለጋስ ነበሩ፡፡ በተለይም እጅግ ቸርና ለጋስ ይሆኑ የነበረው በረመዷን ጂብሪል በሚገናኛቸው ወቅት ነበር፡፡ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) በየለሊቱ እየመጣ ቁርኣንን ይጠናኑ ነበር፡፡ የሳቸው መልካም ነገር ላይ የነበራቸው ቸርነትም ከተላከ ነፋስ የፈጠነ ነበር” (ቡኻሪይ)፡፡

ቀ. አመጠኛ ሰይጣናት የሚታሰሩበት መሆኑ፡-

ሸይጧን በረመዷን ወር የሚታሰር መሆኑን ለማመን ከሐዲሡም ውጪ በተግባር የሚታይ እውነታ ነው፡፡ ቢያንስ ሁለት ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል፡-

1ኛ. የአላህ ቤቶች ሁሉ በሰጋጅ ይጨናነቃሉ፡፡ መስጂዶች ይሞላሉ፡፡ ሁሉም ሙስሊም ይህ ሁሉ ሰው ከየት መጣ! በማለት ይገረማል፡፡ ኢስላምን የሚቀበሉ አዲስ ገቢዎች ጥቂት ቢሆኑም፡ አብዝኃኛው ግን በቤቱና በስራ ቦታው ይሰግድ የነበረ፡ እንዲሁም ከሶላት ጋር ትውውቅ ያልነበረው ሰው ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ህዝብ ከረመዷን በፊት በአላህ ቤት ለመታየት ያልገራለት፡ አሁን በረመዷን ግን መምጣቱ ይፈታተነው የነበረው ሸይጧን መታሰሩን አያመላክትምን?

2ኛ. ዒባዳን ለመተግበር ይቀላል፡፡ ከረመዷን ውጪ ተዘግቶ በክብር ስፍራ የተቀመጠው ቁርኣን በረመዷን አንባቢው ይበዛል፡፡ 1ብር ለመለገስ የሰሰቱ የነበሩ ልቦች፡ በረመዷን ግን ለማስፈጠርና ለሶደቃ ግን ይቻኮላሉ፡፡ ይህን ኸይር ስራ አሁን ለመስራት ከገራልዎት፡ ከአላህ ተውፊቅ በኋላ የሸይጧን መታሰርን አይጠቁምምን?

“የተባረከ ወር የሆነው ረመዷን መጣላችሁ!፡፡ አላህ ጾሙን በናንተ ላይ ግዳጅ አድርጓል፡፡ በዚህ ወር የሰማይ ደጃፎች ይከፈታሉ፡፡ የጀሀነም ደጃፎች ይዘጋሉ፡፡ አመጠኛ ሸይጣናት ይታሰራሉ…” (አሕመድ 7148፣ ነሳኢይ 2106)፡፡

Shortlink http://q.gs/EwioM