ረመዷን መጣ!! ቁጥር 5

ሼር ያድርጉ
669 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

5. ጾምን የሚያበላሹ ተግባራት

በጾም ወቅት መሟላት ያለባቸው ግዴታ ተግባራትና ተወዳጅ የሆኑ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ፡ በዚያው መልክም ጾሙን የሚያፈርሱ ተግባራትም አሉ፡፡ ለጥንቃቄ ይረዳን ዘንድ ቀጥለን እንመለከታቸዋለን፡-

1. አውቆ መብላትና መጠጣት፡-

በቀኑ ክፍል ጾመኛ መሆኑን እያወቀና እያስታወሰ ወደ ሆዱ ምግብና ውሀ ወይም እነሱን የሚተካ ነገር እንዲገባ ከፈቀደ የሰውየው ጾም ተበላሽቷል፡፡ ቀዷውንም በሌላ ጊዜ ይከፍላል፡፡ ይህን ነገር የፈጸመው ግን ረስቶና ዘንግቶ ከሆነ ጾሙ አይበላሽም፡፡ ይህ አላህ ወደሱ የላከው ሲሳይ ነውና፡፡
“…ከጎህ የኾነው ነጩ ክርም ከጥቁሩ ክር (ከሌሊት ጨለማ) ለእናንተ እስከሚገልጽላችሁ ድረስ ብሉ፤ ጠጡም፡፡ ከዚያም ጾምን እስከ ሌሊቱ ድረስ ሙሉ…” (ሱረቱል በቀራህ 187)፡፡
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ጾመኛ መሆኑን ረስቶ የበላ ሰው ባስታወሰ ጊዜ ጾሙን ይቀጥል፡፡ ያበላውና ያጠጣው አላህ ነውና” (ቡኻሪይ)፡፡

2. ከባለቤቱ ጋር መገናኘት፡-

በቀኑ ክፍል ላይ ከባለቤቱ ጋር የተገናኘ ሰው የሁለቱም ጾም ይፈርሳል፡፡ ትልቅም ኃጢአት ፈጽመዋል፡፡ ከፍፋራህ (ካሳ) መክፈልም ይጠበቅባቸዋል፡፡ እሱም፡- በባርነት ቀንበር ያለ ሰው ካለ በገንዘብ ገዝተው ነጻ ማውጣት፣ አቅሙ ከሌላቸው ወይም በባርነት ቀንበር ውስጥ ያለ ሰው ከሌለ 2 ወር በተከታታይ መጾም፣ እሱንም የማይችሉ ከሆነ 60ምስኪኖችን ማብላት ነው፡፡ 60 ምስኪን የማብላት አቅሙ ከሌላቸው ዲኑ ገር ነውና ከአቅም በላይ አይገደዱም፡፡ ከዚህ የካሳ ክፍያ ጋር በተጨማሪ ተውበት መግባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ግኑኝነት የተፈጸመው በባል አስገዳጅነት ሆኖ፡ ሚስት ራሷን ለመከላከል ጥረት አድርጋ ከአቅሟ በላይ ሆኖ ባል ቢፈጽምባት፡ እሷ ካሳ መክፈልም የለባትም ጾሟም አልተበላሸም፡፡ ጉዳዩ ከአቅሟ በላይ የማትቋቋመው ነገር ነውና፡፡ ስሜት አሸነፈኝ ማለት ግን ከአቅም በላይ ሆነብኝ ለማለት ምክንያት እንደማይሆን መረዳት ይገባናል፡፡ በለሊቱ ክፍል ግን ከሚስቱ ጋር መገናኘት ይፈቀዳል፡፡ እንደውም ኢፍጣር ላይ በሷ ማፍጠር እፈልጋለሁ ካለ መብቱ ነው፡፡ ሱናው ተምርና ውሀ ቢሆንም፡፡
“በጾም ሌሊት ወደ ሴቶቻችሁ መድረስ ለናንተ ተፈቀደላችሁ፡፡ እነርሱ ለናንተ ልብሶች ናቸው፤ እናንተም ለነርሱ ልብሶች ናችሁ…” (ሱረቱል በቀራህ 187)፡፡

አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “የአላህ ነቢይ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ዘንድ ተቀምጠን ሳለ፡ አንድ ሰው መጣና፡- ‹‹አንቱ የአላህ መልክተኛ ሆይ! ጠፋሁኝ›› አላቸው፡፡ እሳቸውም፡- ‹‹ምን አጠፋህ?›› ሲሉት፡ እሱም፡- ‹‹እኔ ጾመኛ ሆኜ ባለቤቴን ተገናኘኋት›› ብሎ መለሰ፡፡ እሳቸውም፡- ‹‹ባሪያን ነጻ ማውጣት ትችላለህን?›› አሉት፡፡ እሱም፡- ‹‹አልችልም›› አለ፡፡ ‹‹ሁለት ወር በተከታታይ መጾምስ?›› ሲሉት፡ በድጋሚ ‹‹አልችልም›› ብሎ መለሰ፡፡ ‹‹60 ምስኪኖችን ማብላትስ?›› ሲሉት፡ አሁንም ‹‹አልችልም›› ብሎ መለሰ፡፡ እሳቸውም ትንሽ በቦታው ቆዩና በተምር የተሞላ ዘንቢል እንዲመጣላቸው አደረጉ፡፡ ከዛም ‹‹የታለ ጠያቂው?›› ሲሉ፡ ሰውየውም አቤት! ብሎ መጣ፡፡ ከዛም- ‹‹በል እንካ ይሄን ውሰድና ሶደቃ አውጣበት›› ሲሉት፡ ሰውየውም፡- ‹‹አንቱ የአላህ መልክተኛ ሆይ! በዚህ በሁለቱ ጋራዎች መካከል (በመዲና ድንበሮች) ከኛ ቤተሰብ የባሰ ችግረኛ ማን አለና!›› ሲላቸው፡ እሳቸውም ክራንቻ ጥረሳቸው እስኪታይ ድረስ ሳቁና፡- ‹‹እሺ ውሰድና ቤተሰብህን መግብበት›› አሉት” (ቡኻሪይ)፡፡

3. የዘር ፈሳሽን ማውጣት፡-

በጾም ወቅት በገዛ ፈቃድ ብልትን በመነካካት ወይንም ወደ ባለቤት ገላ በመመልከት የዘር ፈሳሽ (መኒይ) እንዲወጣ ሰበብ ከሆነ የሰውየው ጾም ይፈርሳል፡፡ ቀዷውንም ያወጣል፡፡ ሆኖም ይህ ሁኔታ የተከሰተው እሱ በተኛበት ወይም በህልሙ ሳያውቅ ከሆነ ጾሙ አይፈርስም፡፡ ከቁጥጥሩ ውጪ ነውና፡፡
በሐዲሡል ቁድሲይ ላይ እንደተቀመጠው፡ ጌታችን አላህ ስለ መልካም ባሪያው ጾም ሲናገር፡- “እሱ የምግብና የስሜት ፍላጎቱን ለኔ ብሎ ይተዋልና” ብሏል፡፡ (ኢብኑ ማጀህ)፡፡ የስሜት ፍላጎት የሚለው ውስጥ ይህ ተግባር ይካተታል፡፡ ስሜታችንን ከተውን ይህንንም ለአላህ ብለን ልንተው ይገባናል፡፡

4. አውቆ ማስታወክ፡-

የእጅ ጣትን ወደ ጉሮሮ በመላክ ወይም በሌላ መንገድ የግድ ከሆድ የሆነ ነገር እንዲወጣ የታገለ ሰው ቢያስታውከው ጾሙ ይፈርሳል፡፡ ያለ ፍላጎቱ ግን ከሆነ የወጣው ጾሙ አይፈርስም፡-
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “አውቆ ያስታወከ ሰው ቀዷውን ያውጣ፡፡ ትውከቱ ያሸነፈው (ያለ ፈቃዱ የወጣበት) ግን ቀዷ የለበትም” (አቡ ዳዉድና ቲርሚዚይ)፡፡

5. የምግብ መርፌ መጠቀም፡-

በጾም ወቅት ምግብን ሊተካ የሚችል የምግብ መርፌ (ጉሉኮስ..) መጠቀም ጾምን ያፈርሳል፡፡ ለመጠነኛ ህመም የሚወሰድ ደረቅ መርፌ ከሆነ ግን ጾምን አያበላሽም፡፡

6. የወር አበባና የወሊድ ደም መከሰት፡-

በእህቶች ላይ በጾም ወቅት ይህ ነገር ከተከሰተ ጾማቸው ይፈርሳል፡፡ ሌላው ይቅርና መግሪብ አዛን ሊወጣ (ጸሀይ ልትጠልቅ) 3 ደቂቃ ቀረው በተባለበት ሰዓት እንኳ ደሙ ቢታይ ጾሟ ይፈርሳል ማለት ነው፡፡ ልክ እንደዛው የፈጅር አዛን ሊወጣ 3 ደቂቃ በቀረው ጊዜ ውስጥ ደሟ ቢቆምላት፡ ጾሙን መጾም ይኖርባታል፡፡ ትጥበቱን ከፈጅር አዛን በኋላ ማድረግም ትችላለችና፡፡ ዋናው ከአዛኑ በፊት ለዛሬው ጾም በማለት ኒያን በልቧ ማሳደሯ ነው፡፡
አቢ ሰዒድ አል-ኹድሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ሴት ልጅ ሐይድ ካየች አትሰግድም አትጾምም አይደል!…” (ቡኻሪይ 1951)፡፡

7. ለማፍረስ መነየት፡-

የሚያስጎመጅ ምግብን ወይም መጠጥን ተመልክቶ ለማግኘት በመመኘት፡- ምነው ዛሬ ባልጾምኩ ኖሮ! ብሎ በልቡ ቢያስብ፡ ይህ ሰው በኒያው ብቻ እንዳፈጠረ ይቆጠራል፡፡ ስራ ትርጉም የሚኖረው በኒያ ነውና (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡ ስለዚህም በኒያ ሰበብ ጾማችንን ከማበላሸት ጥንቃቄ እናድርግ፡፡
ሌላው ልናውቅ የሚገባን ነጥብ፡- ከላይ የተጠቀሱት ሰባት አፍራሽ ተግባራትና ሌሎችም አፍራሽ ነገሮች ካሉ፡ ህጉ የሚሰራው ከዚህ በታች የሚጠቀሱትን ሶስት መስፈርቶች ባሟላ ሰው ላይ መሆኑን ነው፡፡ እነሱም፡-

1. ዕውቀቱ ያለው፡-

ይህን የማያውቅ ሰው ይኖራል ብሎ በድፍረት መናገር ቢከብድም ህጉ ግን አስቀምጦታል፡፡ እሱም ከላይ የተጠቀሱ አፍራሽ ተግባራቶች ጾምን እንደሚያፈርሱ ያላወቀና የሚያስተምረው ያላገኘን ሰው አይመለከቱም፡፡ ባለማወቅ አንዳቸውን ቢፈጽም ጾሙ እንዳይበላሽ ጅህልና ለዚህ ሰው ዑዝር ይሆነዋል፡፡

2. አስታውሶ ከሆነ፡-

ከላይ እንዳየነው መርሳት ዑዝር ነው፡፡ ረስቶ በበላውና በጠጣው ነገር አይያዝም፡፡ እኛም ጌታችን አላህ በረሳነው ነገር እንዳይዘን እንድንለምነው ታዘናል፡፡ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-
“…(በሉ)፡- ጌታችን ሆይ! ብንረሳ ወይም ብንስት አትያዘን፤ (አትቅጣን)…” (ሱረቱል በቀራህ 286)፡፡

3. በምርጫው ያለ ሆኖ፡-

ማንም ሰው ያለ ራሱ ምርጫ ተገዶ በሚሰራው ላይ ተጠያቂ አይደለም፡፡ ጥያቄ የሚመረኮዘው ባለቤቱ ፈቅዶ በተገበረው ነገር ላይ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ቀጣዩ የቁርኣን አንቀጽ ማስረጃ ነው፡-
“ከእምነቱ በኋላ በአላህ የካደ ሰው (ብርቱ ቅጣት አለው)፤ ልቡ በእምነት የረጋ ሆኖ (በክሕደት ቃል በመናገር) የተገደደ ሰው ብቻ ሲቀር…” (ሱረቱ-ነሕል 106)፡፡

Shortlink http://q.gs/Ewimy