ረመዷን መጣ!! ቁጥር 4

ሼር ያድርጉ
512 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

4. የጾም ማእዘናትና ተወዳጅ ተግባራት

የረመዷን ጾማችን የተሟላና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን በጾሙ ውስጥ መሟላት ያለባቸው ሁለት መስፈርቶች አሉ፡፡ እነሱም፡-
ሀ. ኒያ ፡- ይህ ማለት ግለሰቡ በእያንዳንዱ የረመዷን ለሊት ላይ የነገውን የረመዷንን ቀን ጾም ለአላህ ብሎ በኢኽላስ እንደሚጾም ከልቡ መወሰን ማለት ነው፡፡ ኒያ የሚለው ቃል ፍቺው፡- አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ለመናገር ከልብ ወስኖ መቁረጥ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሰውየው ባይናገረውም ባይሰራውም በኒያው ሰበብ እንደሰራው ይቆጠርለታልና፡፡ ስራ በጠቅላላ (ኸይርም ሆነ ሸር) ዋጋው የሚገኘው በኒያ ነውና (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡ የኒያ ቦታው ደግሞ ልብ ነው፡፡ በአንደበት መናገር ከሱና አይደለም፡፡ ሰውየው ነገን ለመጾም በዛሬው ለሊት ላይ ልቡን ሰብሰብ አድርጎ ይወስናል እንጂ በምላሱ፡- ‹‹ነወይቱ ሰውመ ገዲን አን-አዳኢ ፈርዲ ሸህሪ ረመዷነ ሀዚሂ-ሰነቲ ኢማነን-ወሕቲሳበን ሊላሂ-ተዓላ›› የሚለውን መናገር አይጠበቅብንም፡፡ እንደውም ቢድዓ ነው፡፡ ኒያ ግዳጅ ለመሆኑ በተጨማሪ ቀጣዩ ሐዲሥ ያስረዳል፡-

ሐፍሷ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንደነገረችን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ከፈጅር በፊት የጾምን ኒያ (በልቡ) ያላሳደረ ሰው ጾም የለውም” (አቡ ዳዉድ 2456፣ ቲርሚዚይ 730)፡፡

ለ. መቆጠብ፡- ይህ ማለት በረመዷን የጾም ወቅት ከማንኛውም ጾምን አፍራሽ ከሆኑ (የሆድና የብልት ስሜቶችን) ነገራት መቆጠብ ማለት ነው፡፡ እሱም ከእውነተኛው ጎህ መቅደድ (ፈጅሩ-ሷዲቅ) አንስቶ እስከ ጸሀይ መጥለቅ (መግሪብ) ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ማለት ነው፡፡
እነዚህ ዋና የጾም ማእዘናት ሲሆኑ፡ ተወዳጅ ተግባራቱ ደግሞ ቀጥሎ ባለው መልኩ ይቀርባሉ፡-

1. ሰሑርን መመገብ፡- ‹‹ሰሐር›› ማለት፡- ከሌሉቱ የመጨረሻው ክፍል ማለት ነው፡፡ በዛ ወቅት የምንመገበው ሲሳይ ሰሑር ተብሎ ይጠራል፡፡ ሰሑርን መመገብ ግዳጅ (ዋጂብ) ያልሆነ ተወዳጅ (ሙስተሐብ) ተግባር ነው፡፡ ቀጣዩም ሐዲሥ ይህን ይገልጻል፡-
አነስ ኢብኑ-ማሊክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ሰሑርን ተመገቡ፡ ሰሑርን በመመገብ በረካ ይገኛልና!” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡

አንዳንድ ሰው ማታ እራቱን ግጥም አድርጎ ይበላና፡ ለቤተሰቡ ሰሑር ማንም ሰው እንዳይቀሰቅሰኝ ብሎ ተጠቅልሎ ይተኛል፡፡ ይህ ተግባር ስህተት ነው፡፡ ምንም ሰሑርን መብላት ዋጂብ ባይሆንም የተወደደ ተግባር ነው፡፡ በረካም ያስገኛል፡፡ ስለዚህ ተነስተን ለሱናው ተምርም ሆነ ወተት እንኳ ቢሆን እንጠቀም፡፡ በተጨማሪም ሰሁርን መመገብ ከአህሉል ኪታቦች ጾም የሚለየን ነገር ነው፡፡ እነሱ ሰሑርን አይመገቡም፡-
ዐብዱላህ ኢብኑ-ዐምር ኢብኑል-ዓስ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “በኛና በአህሉል ኪታቦች ጾም መካከል ያለው ልዩነት ሰሑር መመገባችን ነው” (ሙስሊም 2604)፡፡

2. ሰሑርን ማዘግየት፡- ሰሑርን የሚመገብ ሰው ከቻለ ወደ መጨረሻው ሰዓት አዘግይቶ ከፈጅር በፊት መመገቡ ሱና ነው፡፡ ፈጅር ይወጣብኛል ብሎ የማይሰጋ እስከሆነ ድረስ ማለት ነው፡፡
አቢ ዘር (ረዲየላሁ ዐንሁ) (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ኡመቶቼ…ሰሑርን እስካዘገዩ ድረስ በመልካም ነገር ላይ ከመሆን አይወገዱም” (አሕመድ 21312)፡፡

3. ኢፍጣርን ማቻኮል፡- የጸሀይ መግባት ከተረጋገጠ ወይም የመግሪብን አዛን እንደሰማን ወዲያውኑ ማፍጠር ተወዳጅ ተግባር ነው፡፡
አቢ ዘር (ረዲየላሁ ዐንሁ) (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ኡመቶቼ ኢፍጣርን እስካፋጠኑ…ድረስ በመልካም ነገር ላይ ከመሆን አይወገዱም” (አሕመድ 21312)፡፡

4. በተምርና በውሀ ማፍጠር፡- ወደ ሆዳችን የሚገባው የማፍጠሪያ ሪዝቅ ከተገኘ የተምር እሸት (ሩጠባት) እሱ ከሌለ ተምርን እሱም ካልተገኘ ውሀ መጎንጨት ተወዳጅ ተግባር ነው፡፡ በሳንቡሳና በሾርባ ማፍጠር ቢቻልም ሱንና አይደለም፡፡
አነስ ኢብኑ-ማሊክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) መግሪብን ከመስገዳቸው በፊት በተምር እሸት ያፈጥሩ ነበር፡፡ የተምር እሸት ከሌለም በተምር፣ እሱም ከሌለ ውሀን ይጎነጩ ነበር” (አቡ ዳዉድ 2358፣ አሕመድ 12705)፡፡

5. በኢፍጣር ጊዜ የሚባል ዱዓ፡- ሰውየው በሚያፈጥርበት ወቅት ይህንን ዱዓ ማለቱ ተወዳጅ ነው፡፡ ‹ዘሀበ-ዘመኡ፣ ወብተለቲል ዑሩቁ፣ ወሠበተል-አጅሩ ኢንሻአላሁ ተዓላ›፡-
ዐብዱላህ ኢብኑ-ዑመር (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በሚያፈጥሩ ጊዜ እንዲህ ይሉ ነበር፡- “ዘሀበ-ዘመኡ፣ ወብተለቲል ዑሩቁ፣ ወሠበተል-አጅሩ ኢንሻአላሁ ተዓላ” (አቡ ዳዉድ 2359)፡፡
ትርጉሙም፡- ጥሙም ተወገደ፣ የደም ስሮችም ረጠቡ፣ በአላህ ፈቃድም ምንዳ ጸደቀ ማለት ነው ወላሁ አዕለም፡፡

ይቀጥላል

Shortlink http://q.gs/EwinA