ረመዷን መጣ!! ቁጥር 2

ሼር ያድርጉ
406 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

2. የጾም ትርጉምና ጠቀሜታው

ትላንት በአላህ ፈቃድ የመጀመሪያውን ፕሮግራም ‹‹ፈዷኢሉ-ረመዷን›› የረመዷን ወር ክብርና ደረጃዎች የሚለውን በመጠኑ ተመልክተናል አልሐምዱ ሊላሂ ረቢል-ዓለሚን፡፡ ዛሬ ደግሞ አላህ ፈቃዱ ከሆነ የጾምን ትርጓሜና ጠቀሜታዎችን በመጠኑ እንቃኛለን ኢንሻአላህ፡፡
ሀ. ትርጉም፡-
ሰውም የሚለው የዐረብኛ ቃል ቀጥታ ፍቺው ‹‹መቆጠብ›› ማለት ነው፡፡ አንድን ነገር ከመናገር ወይም ከመስራት መቆጠብ ሰውም (ጾም) ተብሎ ይጠራል፡፡ በንግግሩ ያሰለቸንን ሰው፡- ለምን አፍህ አይጾምም! ስንለው፡ የተፈለገው ለምን ዝም አትልም! ለማለት ነው፡፡ ይህንን ትርጉም የሚያመላክተን ቀጣዩ የቁርኣን አንቀጽ ነው፡-
” فَكُلِي وَاشْرَبِي وَقَرِّي عَيْنًا فَإِمَّا تَرَيِنَّ مِنَ الْبَشَرِ أَحَدًا فَقُولِي إِنِّي نَذَرْتُ لِلرَّحْمَنِ صَوْمًا فَلَنْ أُكَلِّمَ الْيَوْمَ إِنْسِيًّا ” سورة مريم 26
“ብይም፣ ጠጭም፤ ተደሰችም፤ ከሰዎችም አንድን ብታይ ፦ እኔ ለአልረሕማን ዝምታን ተስያለሁ፤ ዛሬም ሰዉን በፍጹም አላነጋግርም በይ።” (ሱረቱ መርየም 26)፡፡
መርየም (ዐለይሃ-ሰላም) ሰዎችን ማናገር እንደሌለባትና ዝም እንድትል ትእዛዝ ሲሰጣት፡ ዝምታዋ በዐረብኛው ‹ሰውም› ተብሎ ነው የተጠቀሰው፡፡
የጾም ሃይማኖታዊ ፍቺው ደግሞ፡- ከጎህ መቅደድ (ፈጅር) እስከ ጸሀይ መጥለቅ (መግሪብ) ድረስ ወደ አላህ በመቃረብ ኒያ ከምግብና ከመጠጥ፣ ከባለቤት ጋር ግንኙነት ከመፈጸም፡ ከተቀሩትም ጾምን ከሚያበላሹ ነገራት መቆጠብ ማለት ነው፡፡

ለ. ጠቀሜታው፡-

ጾም ብዙ መንፈሳዊ ጠቀሜታዎችን ለጾመኛው ያስገኛል፡፡ ከነዚህም መካከል፡-
1. ተቅዋ (አላህን መፍራት)፡- አንዱና ዋነኛው ጥቅሙ ነው፡፡ ጾመኛ ሰው በጾም ወቅት ደካማነቱን ይረዳል፡፡ በመጾሙ ሰበብ የሆዱን ፈቃድ ባለሟሟላቱ ምን ያህል እንደተቸገረ ይረዳል፡፡ ሲዘልና ሲጫወት የነበረው አሁን ተጠቅልሎ ሲተኛ የአቅሙን ውስንነት ይረዳል፡፡ በዚህም ሰበብ ለኃያሉ ጌታው አላህ ይተናነሳል፡፡ እሱንም ይፈራል፡፡ የበላና የጠገበ ሰው ግን ፍርሀት ምን እንደሆነ በምን ያውቃል? እንዴትስ ይረዳል? ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-
” يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُتِبَ عَلَيْكُمُ الصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى الَّذِينَ مِنْ قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ ” سورة البقرة 183
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነገገ) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 183)፡፡
‹‹ልትጠነቀቁ ይከጀላልና›› የሚለው የሚያመላክተን፡- አላህን የመፍራት ልብ ታገኙና ትወፈቁ ዘንድ የሚለውን ነው፡፡

2. ከእሳት መከላከያ ጋሻ ነው፡-

ዑሥማን ኢብኑ አቢል-ዓስ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማሁ አለ፡- “ጋሻ ከግድያና ከሰይፍ እንደሚከላከለው፡ ጾምም ከእሳት የሚከላከልላቹሁ ጋሻችሁ ነው” (ነሳኢይ 2231)፡፡

3. ፊትን ከእሳት ያርቃል፡-

አቢ ሰዒድ አል-ኹድሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማሁ አለ፡- “በአላህ መንገድ (በጂሀድ) ላይ ሆኖ አንድን ቀን የጾመ ሰው፡ አላህ ፊቱን ከጀሀነም እሳት የሰባ አመት መንገድ ያርቀዋል” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡ አላህ ይወፍቀን፡፡

4. ከሀራም ይከላከላል፡-

ሰው ስሜት የሚኖረው ሲበላና ሲጠጣ ነው፡፡ ስሜቱን በሐላል መንገድ የሚያስተናግድበትን ካጣ ደግሞ ወደ ሐራም መሄዱ ነው፡፡ ለዚህ በሽታ ፍቱን መድሀኒቱ ደግሞ ጾም ነው፡-
ዐብደላህ ኢብኑ-መስዑድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለው ነገሩን አለ፡- “እናንተ የወጣት ስብስቦች ሆይ! ከናንተ ውስጥ የትዳር ጣጣዎችን መሸፈን የቻለ ሰው ያግባ፡፡ እርሱም (ማግባቱ) አይኑን መስበሪያና ብልቱን መጠበቂያ ነው፡፡ ያልቻለ ሰው ደግሞ ጾምን (በማብዛት) አደራ! እሱ ከዝሙት መከላከያ ነውና” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡

5. ለብቻው የተዘጋጀ የጀነት በር (V.I.P) ያለው መሆኑ፡-

አማኞች በጠቅላላ በምድራዊ ህይወታቸው በኢስላም ላይ ከሞቱ ያለጥርጥር ጀነት ይገባሉ፡፡ አላህ ከነሱ ያድርገን፡፡ ጀነትን ሙስሊም የሆነች ነፍስ እንጂ ሌላው አይገባትምና፡፡ ከነዚህ የጀነት ስምንት በሮች ውስጥ ደግሞ ‹‹አር-ረያን›› ተብሎ የሚጠራ በር አለ፡፡ በዚህ በር በኩል በስም ተጠርተው የሚገቡት ግን ጾመኞች ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ለነሱ የተለየ ክብር ነው፡፡
ሰህል ኢብኑ ሰዕድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “በጀነት ውስጥ አር-ረያን የሚባል በር አለ፡፡ የውሙል ቂያም ጾመኞች ይገቡበታል፡፡ ጾመኞች የታሉ? በመባል ይጠራሉ፡፡ እነሱ ጨርሰው ከገቡ በኋላ በሩ ይዘጋል፡፡ ከነሱም ኋላ ማንም ሰው አይገባም” (ቡኻሪና ሙስሊም እንዲሁም ሌሎች የዘገቡት)፡፡

6. ለጾመኛው አማላጅ መሆኑ፡-

ዐብደላህ ኢብኑ-ዐምሩ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ጾምና ቁርኣን ለሰራባቸው የአላህ ባሪያ የቂያም ቀን ያማልዳሉ፡፡ ጾምም እንዲህ ይላል፡- ጌታዬ ሆይ! ባሪያህን ከምግብና ከስሜት ፍላጎት ከልክዬዋለሁና ዛሬ አማልደኝ (እሱን እንዳማልድ ፍቀድልኝ)፡፡ ቁርኣንም እንዲህ ይላል፡- ጌታዬ ሆይ! እኔን ለማንበብ ከሌሊት እንቅልፍ ከልክዬዋለሁና ዛሬ አማልደኝ (እሱን እንዳማልድ ፍቀድልኝ)፡፡ ሁለቱም እንዲያማልዱ ይፈቀድላቸዋል” (ሶሒሑ ተርጊብ ወት-ተርሂብ 984)፡፡
‹‹ማማለድ›› ማለት፡- ይህ የአላህ ባሪያ የኃጢአት ስርየትን እንዲያገኝና በአላህ ቸርነት ጀነት እንዲገባ አላህን መማጸን ማለት ነው፡፡

7. የአፉ ሽታ ያማረ መሆኑ፡-

የጾመኞች አፍ ጠረኑ በስጋዊ ስሜት ሲሸተት ይከረፋል፡፡ ጥሩ መዓዛም የለውም፡፡ አላህ ዘንድ ግን ከሚስክ ሽታ በላይ እጅግ ያማረ ነው የሚሆነው፡፡
አቢ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡-
“…የጾመኛ ሰው የአፉ ክርፋት አላህ ዘንድ ከሚስክ መዓዛ በላይ ያማረ ነው” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡

8. የማትመለስ ዱዓ ያለበት መሆኑ፡-

አቢ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡-
“ሶስት ሰዎች ዱዓቸው ተመላሽ አትሆንም፡- ፍትሀዊ መሪ፣ ጾመኛ እስኪያፈጥር፣ የተበዳይ ዱዓእ” (ኢብኑ ማጀህ 1752፣ ቲርሚዚይ 3598፣ ሶሒሕ ኢብኑ ማጀህ 2/86)፡፡

9. ደስታን ያመጣል፡-

አቢ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡-
“…ጾመኛ ሰው ሁለት ደስታዎች አሉት፡፡ በሚያፈጥር ጊዜ የሚሰማው ደስታ እና፡ ነጌ ከጌታው ጋር ሲገናኝ የሚሰማው ደስታ ነው” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡

ይቀጥላል

Shortlink http://q.gs/Ewio0