ማስገንዘቢያ ፍትህ ለተዛባበት ማሕበር

ሼር ያድርጉ
412 Views

ኢሊያህ ማህሙድ

በኣላህ ስም እጅግ አዛኝ እጅግ ሩህሩህ በኾነው እንጀምርና በመቀምቀሚያው ዘመን የመጨረሻ ነብይ ኾነው በተላኩት ሙሐመድ ላይ የኣላህ ሰላምና እዝነት ይውረድ ብለን ቀጠልን፡፡ ወዳጄ እንደምን ከረሙ? የዛሬው ወጋችን ማሕበሩ ያስተላለፈውን መግለጫ መሰል የክተት አዋጅ በመንተራስ እንዲኾን ወደድኹ፡፡

[ፍትሕ ኹሌም ሚዛናዊ ናት]

ወዳጄ ጥፋትን ማንም ይስራው ጥፋት ነው፡፡ መላዕክት ወርደው ኣንድ ክፉ ነገር ቢፈጽሙ፣ ኣጋንነት ተደራጅተው ከፈጸሙት እኩይ ስራ ጋር እኩል ነው፡፡ ጥፋትን ቅቤ ቀብተን ማጣፈጥ ኣይቻልምና፣ ጥፋት እንደ ግለሰቦች ቅርጹን አይቀያይርምና ጥፋትን በጥፋትነቱ የሚቀበል ኣዕምሮ ሊኖረን የግድ ነው፡፡ በዚህ ከተግባባን ዘንዳ፣ሙስሊሙ ቤተክርስቲያን አቃጥሎ ከነበር፣ በሕግ ሊጠየቅና አስፈላጊውም ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ በተመሳሳይ ክርስቲያኑም ጥፋተኛ ሲኾን ተመሳሳይ ሕግ ሊያልፍበት ይገባል፡፡ ጉራጌ፣አዲስ አበባ፣ጎንደርና ጎጃም መስጂዶች ሲቃጠሉና ሲፈርሱ አፉን በልጓም የተበተበ አካል፣ቤቴ ተቃጠልብኝ ብሎ ጣት መቀሰር፣ የናንት ቢቃጠል እንዳሻው የኔን ግን አትንኩብኝ እንደማለት ነው፡፡ በዛ ላይ ማን እንዳቃጠለው እንኳ ገና በቂ መረጃ በሌለበት ኹኔታ፣ነገሮችን ጠቅልሎ ለኣንድ ወገን በመስጠት መኮነን ኢሚዛናዊነት ነው፡፡

እኛ ሙስሊሞች ኣዕምሮኣችን ውስጥ ማሕበሩን አዝለን አንኖርማና መስጂዶች በተቃጠሉና በፈረሱ ቁጥር ማሕበሩን ኣንረግምም፡፡ ወገኖቻችን ግን በልቦናቸውና ሕሊናቸው ሚመላሰው በኢስላማዊ መገለጫዎች የተሞላው ምልዓተ-ሙስሊሙ ስለኾነ፣ ከቤተክርስቲያን አጥር ኣንድስ እንኳ ተነቅሎ ቢገኝ፣ ሙስሊሙን ከመውቀስ አይመለሱም፡፡ በራሳቸው ካህናትና ምዕምናን ንዋዬቻቸው ሲዘረፉ ቁብ ያልሰጣቸው፣አጥር በተነቃነቀ ቁጥር ሙስሊሙን መዘመሩ፣ ይበልጥ ያስተዛዝባል፤ያስገምታልም፡፡

የኣዛዚል (ኢብሊስ) ጓዶች ኹሌም የተረገሙ ይኹኑ!!! የብዔል ዜቡል ወታደሮችና የጥፋት መካሪዎች ኹሌም የተወገዙ ይኹኑ!!! ክፋትን እንጂ ቅንን የማታስብ ልብ እርሷ ትሙት!!! ይህ እርግማን ግን ለኹሉም እንደኾነ ይሰመርበት-ለሙስሊሙም፣ ላልኾነውም፡፡

[ሌላው ታሪክ የለውምን?]

ወዳጄ ታሪክ በተፈጥሮዋ ሚዛናዊ የኾኑ ልቦችን እንደምትፈልግ ልብ ይሏል፡፡ ታሪክ የሚዘግብም ኾነ የሚያነብ፣ መሐል መንገድ ላይ ኾኖ ካልመረመረ፣ እንደ ወገኖቻችን አነባብሮውን ለራሴ፣ ድርቆሽን ግን ኣንተ ውሰድ፤ የሚል ያጋደለ እይታ ይኖረዋል፡፡ ስለ ኢትዬጵያ ታሪክ ስናወራ ስለ ኹሉም ብሔሮችና እምነቶች ታሪክ ካልኾነ፣ የጥቂት አካላት ታሪክ የኢትዬጵያ ሊባል ኣይችልም፡፡ ሊሰመርበት የሚገባው እዝች ምድር ላይ ኹሉም ኃይማኖቶች ከውጭ ገቡ እንጂ እዚኹ ኣልተወለዱም፡፡ ኣይሁዳዊነት ሲመጣ እምነት ያልነበራቸው ኣያቶቻችን ተቀበሉት፤ክርስትናም ሲመጣ ኣይሁድ የነበሩና ኃይማኖትም ያልነበራቸው ኢትዬጵያውያን ተቀበሉት፤ ኢስላምም ሲመጣ በተመሳሳይ መልኩ በዝች ምድር ላይ ጥንቱንም ነዋሪ የነበሩ ኣባቶቻችን ተቀብለውታል፡፡ ኃይማኖት ስነ-መለኮታዊ አስተሳሰብና እምነት እንጂ ብሔር ኣይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ክርስቲያን የሚባል ጥንታዊ ነዋሪና የይዞታ ባለቤት የኾነ ብሔር ኖሮ፣ ከውጭ ተሰደው የመጡ ኢስላም የሚባል ብሔረሰብ ኣባላት የነበሩ ግለሰቦችን ቦታና ይዞታ ሰጥቶ አልተቀበለም፡፡ኣላኖረምም፡፡ ይልቁንም ክርስትና ራሱ በገባበት መንገድ ሰዎች ኃይማኖቱን ይዘው መጡ፤ኃይማኖቱን የተቀበሉ ኢትዬጵያውያን ኣሉ ያልተቀበሉም ኣሉ፡፡ ኃይማኖቱን ይዘው የመጡ ግለሰቦች እዚሁ ምድር ላይ ኖረው የሞቱ ኣሉ፤ወደመጡበትም የተመለሱ ኣሉ፡፡ ኃይማኖቶቹን ግን ተቀብለው ሲኖሩ የነበሩ እስከ ኣኹንም ድረስ ያሉ ኹሉም ኢትዬጵያውያን ናቸው እንጂ መጤና ትርፍ ሕዝቦች ኣይደሉም፡፡
ኹኔታው ከላይ የዘረዘርነው ኾኖ እያለ፣ ታሪክን ወደ ራስ ብቻ እየጎተቱ በዝች ምድር እኛ ብቻ ነን የነበርነው፣ምናስፈልገውም እኛ ብቻ ነን ማለት በቀጥታ በሌላው ሕልውና ላይ መፍረድ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ለዘመናት እንደ ውዳሴ ማርያም ስትደጋግሙት፣ በየቅኔዎቻችሁ በበገና ስትዘርፉትና ስትደረድሩት ኖራችኋል፡፡ እውነት ይህች ምድር የናንት ብቻ ከነበረች፣ታሪክም እናንተን ብቻ ከኾነ የሚያውቀው፣ እንግዲያውስ ከናንት የወረስነው ድሕነት እንጂ ሌላ ኣይደለም፡፡ በበዓላት ድባብ ውስጥ ኾኖ በባዶ ሆዱ ኣምቡላ ሚጋት፣በባዶ እግሩ እየሄደ ተባርኬኣለኹ፣ ውስጡ በጥላቻና ክፋት ተሞልቶ ተቀድሻለኹ የሚል ሕዝብ ነው የፈጠራችኹት፡፡ አቧራ በሚቦንበት ምድር ላይ ኾኖ በገነት አትክልት ውስጥ እንዳለ ሚያስብ ሕዝብ ነው የሰራችኹት፡፡ ፈጣሪ ኣዳምን ለመፍጠር መላዕክትን “ንግበረ” ብሎ በግዕዝ ቋንቋ ኣናግሯል፤ ቋንቋህ የፈጣሪም ጭምር ነው ብላችኹ የሰበካችኹት ሕዝብ እንኳ ቅድመ-ታሪክና ቅድመ-ስልጣኔ ሊኖረው ይቅርና በቀን ሦስቴ እንኳ በልቶ የማያድር ነው፡፡ የኣዳም እግር አሻራ ናት የተባለላት፣ የዓለም የመጨረሻ ድሐ ሐገር መኾኗ፣ የጊዮን መፍሰሻ ናት የተባለች ምድር፣ የጠኔና ርሐብ ምሳሌ ኾና ማየት፣ ከአየር ላይ እያፈሳችኹ የፈጠራችኹት ትርክት በምልዓት ተረት እንደኾነ ያሳብቃል፡፡

[እውነተኞች ከኾናችኹ ኑ ወደ መድረክ]

እናንት ፊኛ እየነፋችኹ ትንፋሻችኹን የምትጨርሱ ወገኖች ሆይ! ሐቅና እውነታ ላይ ነን ካላችኹ ኑ መድረኩን አብረን ሰርተን በመረጃ እናውራ፡፡ ኑ ትንፋሻችኹን ሰብሰብ አድርጋችኹ፣ መጽሐፉን ፈራጅ አድረገን እንወያይ፡፡ እለት እለት ውፍረታችኹ ሲቀጭጭ፣ መረጃ ኣምጡ! ካልኾነ ተረታችኹ በቃን ብሎ ጉባኤው ከስራችኹ ሲበተን፣ በመካከላችኹ የናንተው ልጆች ተነስተው የናንተው ቀበኛ ሲኾኑ፣ ገሚሱ ወደ ኢስላም ሲመጣ ስታዩ፣ ያኔ ኣብሾው ተነስቶ በየጎዳናው አቀባዠራችኹ፡፡ የጥላ ወጊ ዛርና ኣባዜኣችኹ ተጋግዘው ሲያሳብዱዋችኹ ከነጎፈሬኣቻኹ “ማጓራት” ያዛችኹ፡፡
የኃይማኖት ኣባት በተለይም “ስለ ኃይማኖቴ ሞታለኹ እንጂ ኣልጋደልም” በሚል ትርጉም ኣልባ ፍልስፍና የተቀነበበ፣ ብትሩን ኣንስቶ ኣምቡላ እንደ ገፋው ወጠምሻ “Aረ ጥራኝ ዱሩ… Aረ ጥራኝ ጫካው” እያለ ኣይፎክርም፤ኣያቅራራምም ከንቱ ዛቻና ማስፈራሪያ የገደል ላይ ጩኸት ነው፤ የራስን ጆሮ ከማደንቆር በዘለለ አየር ላይ መክኖ ቀሪ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ የመንደር ውሻ እንኳ በጩኸት ኣልደነግጥ ብሏል!!!

ሆዱን በጎመን የደለለ ዳገት መውጣት ኣይደለም ለውጣት ማሰብ እንኳ ይሳነዋል፡፡ ሆዳችኹ ውስጥ ባሰገባችኹት እርግጠኞች ከኾናችኹ፣ ሰላማዊውን የውይይት ዳገት መውጣት እንዳለባችኹ እመኑ፡፡ ጊዜውን ባልጠበቀ ቀረርቶና ሽለላ ግን የምናቡ የሰብለ ወንጌል ኣባትም ከነአበጀ በለው ጡንቻ አልዳኑም፡፡ አራት ነጥብ፡፡

ልብሽ እያወቀ  ድድ ባወጣ ውሽት ሐቅ ተገምብሮ ገደል አልወደቀ
ልብሽ እያወቀ  በምቀኝነት ዛር “ጨለማው” ተገፎ “ድል” አልፈነጠቀ
ልብሽ እያወቀ  ቀረርቶም ሽለላም በበላይነት ድምጽ አታሞ አልደለቀ
ልብሽ እያወቀ  በተሰበረ ነፍጥ የተኮሰ የለም ገድሎም የጸደቀ
ልብሽ እያወቀ  ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ እንደጮኸ፣እየበጠረቀ
ልብሽ እያወቀ  መቁጠር የማትችይው “የባሕር አሸዋ” ትግስቱ እንዳለቀ

 

Shortlink http://q.gs/Eye0y