ሚዛናዊነትን ቁርኣን ያስተምረናል

ሼር ያድርጉ
56 Views
ኤሊያህ ማህሙድ በኣላህ ስም እጅግ ኣዛኝ እጅግ ሩህሩህ በኾነው እንጀምርና በመቀምቀሚያው ዘመን የመጨረሻው ነብይ ኾነው በተላኩ ሙሐመድ (ሠ) ላይ የኣላህ ሰላምና እዝነት ይውረድ ብለን እንቀጥላለን፡፡ ወዳጄ እንደምን ከረሙ?! እኔም የሚዲያው ሸንጎ እስጥልት ኣድርጎኝ ተገልዬ ቆየኹና ከሰሞኑን የነፈሰው ነፋስ ግን ዳግም ኣሽቀንጥሮ መለሰኝ መሰል እነሆ ከማለዳው መሞንጨር ያዝኹ፡፡ ወዳጄ የርሶን ባላውቅም ለኔ ይህ ትውልድ መልህቋን በጣለች ታንኳ ይመሰልብኛል፡፡ መልሕቋን የጣለች ታንኳ ነፋስ በየኣቅጣጫው እያላጋ ይወስዳታል፡፡ እርሷ ምንም ምርጫ የላትም፤ወደየት እንደምትጓዝ የሚመርጥላት ነፋሱ ነው፡፡ ነፋሱን የምትገዳደርበት ጉልበትም ኣቅምም የላትም፡፡ ምክንያቱም ጉልበት የሚኾናትን መልሕቅ ጥላለችና፡፡ ኣንዳንዴ ነፋሱ ጠና ሲል ከቆመ ቋጥኝ ጋር ወይም ከሌላ ኣቅጣጫውን ጠብቆ ከሚጓዝ ታንኳ ጋር ያላትማታል፡፡ ወይም ቁልቁል በኣፍጢሟ ደፍቶ እንክትክቷ እንዲወጣ ያደርጋታል፡፡ መልሕቁን የጠበቀ ታንኳ ከየትኛውም ኣቅጣጫ ለሚነሳ ነፋስም ኾነ ነፋሱ ለሚቀሰቅሰው ሞገድ ሳይበገር ሚዛኑን ጠብቆ ካለበት ይቆማል፡፡ይጸናልም፡፡ ወዳጄ መልሕቁን በእውቀት ብርኃንና በኣሰላስሎ ብስለት መስሉት፤ ነፋሱን ደግሞ በየጊዜው የሚነሱ ውል ኣልባ አጀንዳዎች እንደኾኑ ኣስምሩበት፡፡ ወዳጄ እውነት እውነት እሎታለኹ! ብዙዎች እንደ ጋጋኖ የምንጮኽባቸው አጀንዳዎች በቅጡ ካስተዋልናቸው የጥቂቶች ጉዳይ እንጂ በትክክል እኛ ሐሳብ የምንሰጥባቸው ወይም የምንነታረክባቸው ኾነው ኣይደለም፡፡ ይህን ስል ግን ጉዳዮቹ እኛን ኣይነኩም እያልኹ እንዳኾነ ይሰመርበት፡፡ በተለይ በዚህ ውጥንቅጡ በወጣ የደም ምድር ላይ እኛን በቀጥታም በተዘዋዋሪም የማይነካን ጉዳይ ኣለ ማለት ኣያስደፍርም፡፡ ግና ጉዳዮቹን ተከትለን ስንቃወምም ኾነ ስንደግፍ ኢስላምን መስፈረት ማድረግ ቢሳነን እንኳ በሰላማዊ ኣእምሮ መካከለኛነትን (ሚዛናዊነት) እየያዝን ኣይመስልም፡፡ ወዳጄ ለመኾኑ እዚህች ሐገር ላይ በፖለቲካ ስም ከሚንቀሳቀሱ ኣካላት መካካል ሚዛናዊ በኾነ መስፈሪያ ሰፈረን ፈጽሞ የምናጨበጭብላቸው ሰዎች አሉን ? ወይስ ደግሞ ፈጽሞ የምንቃወማቸውስ ኣሉን ? እውነት ነው ፍትሓዊነት በጎደለው ሚዛን የኛ ነው የምንለው ግለሰብ አደባባይ ላይ መኪናውን ይዞ ቢቆምና መንገድ ኹሉ ቢዘጋ፣ትክክለኛ ነገር ነው ያደረገው፡፡ የኛ ያላልነው ኣካል ደግሞ ስለምነው መንገድ ዘግተህ የቆምኸው ብሎ ቢናገር፣ ያ ሰው ታሪክ የማይረሳው ግዙፍ ጥፋት ሰርቷል፡፡ በፍትሕ ሚዛን እዝህች ምድር ላይ ማንም ፍጹም ኣይደለም፤ፍጹም ታሪክም ኣልሰራም ወደፊቱም ኣይሰራም፡፡ በዝች የኋልዮሽ በምትጋልብ የኣሳር ምድር ወደድንም ጠላንም የኹላችንም እጅ በደም ጠልሽቷል፡፡ ታሪክን እንተርክ ካልን እንእንቶኔ በኛ ተስካር ሰረጉ ማለት ብቻ ሳይኾን፣ ደረጃው ይለያይ እንጂ እኛም በነሱ ሞት መለከት ነፍተናል እምቢልታም ጎስመናል፡፡ ይህች ምድር የኹላችንም የደም አሻራ አለባት፡፡ስለኾነም ድጋፋችንም ኾነ ቅዋሜኣችን ሚዛናዊነት ይኑረው፡፡ “እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ለአላህ ቀጥተኞች በትክክል መስካሪዎች ኹኑ፡፡ ሕዝቦችንም መጥላት ባለማስተካከል ላይ አይገፋፋችሁ፡፡ አስተካክሉ፡፡ እርሱ (ማስተካከል) ለአላህ ፍራቻ በጣም የቀረበ ነው፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡” ኣልማኢዳ/8