ሙስሊም ካልኾነ ሰው ጋር በትዳር መጣመር!

ሼር ያድርጉ
769 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምሥጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን(አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

1ኛ/ ጋብቻ የጌታ አላህ ትእዛዝ፣ የነቢያት ሱንና እና የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የሕይወት ፈለግ ነው፡፡ አላህ ትዳር የሌላቸውን ሰዎች እንድናጋባቸው ትእዛዝን ሰጥቷል፡፡ ለጊዜው ችግረኞች ቢኾኑ፡ ከሱ በኾነ ቸርነት እንደሚያብቃቃቸውም ቃልን ገብቶላቸዋል፡፡ ቀደምት ነቢያትንም በትዳር እንዲጣመሩ በማድረግ የነቢያት ሱንና መኾኑንንም አበክሮ ነግሮናል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-

“ከናንተም ትዳር የሌላቸውን አጋቡ፡፡ ከወንዶች ባሮቻችሁና ከሴቶች ባሮቻችሁም ለጋብቻ ብቁ የኾኑትን (አጋቡ)…” (ሱረቱ-ኑር 24፡32)፡፡

“ከአንተ በፊትም መልክተኞችን በእርግጥ ልከናል፡፡ ለእነርሱም ሚስቶችንና ልጆችን አድርገናል…” (ሱረቱ-ረዕድ 13፡38)፡፡

2ኛ/ የጋብቻ ዓላማው፡- እራስን ሐራም ከኾነው ዝሙት በመከላከል፡ በህጋዊ መንገድ ትዳርን መስርቶ የነፍሲያን እርካታ ለመጎናጸፍ፣ በምድር ላይ ቀጣይነት ያለው አላህን የሚያመልክ ትውልድ ለመተካት ነው፡፡ በተለይ ዝሙትን ለመሸሽ እና ለመራቅ ብሎ ትዳርን የሚፈልግ ሰው፡ ችግረኛም ቢኾን እንኳ አላህ እንደሚያብቃቃው በቁርኣኑ፡ ረሱላችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ደግሞ በሐዲሣቸው ነግረውናል፡፡ በተቃራኒው ያለ ምንም ሸሪዓዊ ምክንያት እራስን ከትዳር ዓለም ማግለል ከነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሱንና ማፈንገጥ እንደኾነ ተገልጾአል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-

“ለእናንተም ከነፍሶቻችሁ (ከጎሶቻችሁ) ሚስቶችን ወደእነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ፣ በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ለሚያስተውሉ ሕዝቦች ተዓምራቶች አልሉ፡፡” (ሱረቱ-ሩም 30፡22)፡፡

“ከናንተም ትዳር የሌላቸውን አጋቡ፡፡ ከወንዶች ባሮቻችሁና ከሴቶች ባሮቻችሁም ለጋብቻ ብቁ የኾኑትን (አጋቡ)፡፡ ድኾች ቢኾኑ አላህ ከችሮታው ያከብራቸዋል፡፡ አላህም ስጦታው ሰፊ ዐዋቂ ነው፡፡” (ሱረቱ-ኑር 24፡32)፡፡

ከአቢ ሁረይራህ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ሶስት ሰዎች አላህ ሊያግዛቸው የተገባ ነው…..ከዝሙት መጥጠበቅን ፈልጎ ትዳር የመሰረተን” (ሶሒሑ ቲርሚዚ 1655)፡፡

አነስ ኢብኑ ማሊክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- ሶስት ሰዎች ወደ አላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሚስቶች ቤት፡ ስለ መልክተኛው ዒባዳህ አፈጻጸም ለመጠየቅ መጡ፡፡ በተነገራቸውም ጊዜ፡ ‹‹እሳቸው ያለፈውም የሚመጣውም ስህተት ተምሮላቸው ሳለ እንዲህ ከኾኑ፡ እኛ ከሳቸው አንጻር ታዲያ የት ነው ያለነው!›› በማለት ሥራቸውን አቅለው ተመለከቱት፡፡ ከዚያም ከሶስቱ አንደኛው፡- ‹‹ከአሁን በኋላ ሁሌም ለሊት ተነስቼ እሰግዳለሁ በፍጹም አላርፍም›› አለ፡፡ ሌላኛውም፡- ‹‹ሁሌም ቀኑን እጾማለሁ በፍጹም አላፈጥርም!›› ሲል፡ ሶስተኛውም በበኩሉ፡- ‹‹እኔም ሴቶችን እርቃለሁ መቼም አላገባም!›› ይላል፡፡ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) መጡና፡- ‹‹እንደዚህ እንደዚህ ያላችሁት እናንተ ናችሁን? በጌታዬ ይሁንብኝ! አላህን በመፍራትና እሱን በመጠንቀቅ እኔ በላጫችሁ ነኝ፡፡ ኾኖም አንዳንዴ እጾማለሁ ደግሞም አፈጥራለሁ፣ ከለሊቱ ክፍል ተነስቼ ለጌታዬ እሰግዳለሁ ደግሞም አርፋለሁ፣ አላህ የፈቀደልኝንም ሚስቶችን አገባለሁ፡፡ ከኔ ሱንና የጠላ ሰው ከኔ አይደለም!›› አሏቸው›› (ቡኻሪይ 5063፣ ሙስሊም 1401)፡፡

3ኛ/ ጋብቻ ሃይማኖታዊ ብይኑ ሱንና ሙአከድ (እጅግ ተወዳጅ የኾነ) ነው፡፡ ዋጂብ አይደለም፡፡ የትዳር ጣጣዎችን መሸፈን እየቻለ፡ ስሜት የሚያስቸግረው በኾነ ሰው ላይ ግን ዋጂብ እንደኾነ የኢስላም ሊቃውንት ይገልጻሉ፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዱ፡ ‹‹በስሜት መቸገር ምክንያት ሐራም ላይ የሚወድቅ ከኾነ፡ እራሱን ከሐራም መጠበቅ ግዳጅ ስለሚኾንበት፡ አማራጩ ደግሞ ቶሎ ትዳር መመስረት ከኾነ፡ ለዚህ ሰው ትዳር ዋጂብ ይኾናል ማለት ነው›› በማለት ይገልጻሉ፡፡ ትዳር በመሠረቱ ግን የተወደደ ተግባር እንጂ ግዳጅ አይደለም፡፡ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ይላሉ፡- “እናንተ የወጣት ስብስቦች ሆይ! ከናንተ ውስጥ የትዳርን ጣጣ የሚችል ካለ ቶሎ ያግባ፡፡ እሱ (ትዳሩ) አይንን ለመስበር፡ ብልትንም ከዝሙት ለመከላከል ይረዳልና፡፡ ጣጣውን መሸፈን ያልቻለ ደግሞ በፆም ላይ ይበርታ፡፡ እሱ (ፆሙ) ስሜቱን ያቀዘቅዝለታልና” (ቡኻሪይ 5066፣ ሙስሊም 1400)፡፡

4ኛ/ አንድ ሙስሊም የኾነ ወንድ ለትዳር የሚፈልጋት ሴት ሙስሊም መኾኗ፡ በተለይም ኢማኗ ጠንካራ የኾነ ዲነኛ ሴት ማግባቱ እጅግ ተወዳጅ ነው፡፡ ቤቱንም ሆነ ልጆቹን በአላህ ዲን ላይ ሰበብ በመኾን ትጠብቅለታለችና፡፡ በተጨማሪም አላህና መልክተኛው ባዘዙት መሠረት የባሏን ሐቅ ለመወጣት ትጥራለች፡፡ በተጨማሪም ብዙ ወላድ እና ተወዳጅ የኾነችውን ማግባት ተመራጭ ነው፡፡ የቤተሰቧን እና የዘመዶቿን ሁኔታ በመጠየቅ፡ እናቷ ብዙ የወለዱ ከኾነ፡ ወይም ከታላላቅ እሕቶቿ መውለድ በመነሳት ወላድ መኾነዋን በአመዛኙ ማወቅ ይቻላል፡፡ ወይንም ከዚህ በፊት ትዳር ይዛ ከነበር በዛ ማወቅ ይቻላል፡፡ ዋናው የአላህ ፈቃድና ውሳኔ ከመኾኑ ጋር ማለት ነው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-

“(በአላህ) አጋሪ የሆኑ ሴቶች እስከሚያምኑ ድረስ አታግቡዋቸው፡፡ ከአጋሪይቱ ምንም ብትደንቃችሁም እንኳ ያመነችው ባሪያ በእርግጥ በላጭ ናት፡፡ ለአጋሪዎቹም እስከሚያምኑ ድረስ አትዳሩላቸው፡፡ ከአጋሪው (ጌታ) ምንም ቢደንቃችሁ ምእምኑ ባሪያ በላጭ ነው፡፡ እነዚያ (አጋሪዎች) ወደ እሳት ይጣራሉ፡፡ አላህም በፈቃዱ ወደ ገነትና ወደ ምሕረት ይጠራል፡፡ ሕግጋቱንም ለሰዎች ይገልጻል እነርሱ ሊገሰጹ ይከጀላልና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡220)፡፡

“…የከሓዲዎቹንም ሴቶች የጋብቻ ቃል ኪዳኖች አትያዙ…” (ሱረቱል ሙምተሒናህ 60፡10)፡፡

መዕቀል ኢብኑ የሳር (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተናገረው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ባሏን ወዳድና ልጆችን ወልላድ የኾነችዋን አግቡ፡፡ እኔ በናንተ ሰበብ ብዛት ያለው ተከታይ ይኖረኛልና ” (አቡ ዳዉድ 2050፣ ነሳኢ 3227)፡፡

በነዚህ አንቀጽ መሠረት፡ በአላህ የሚጋሩ የኾኑ ሙሽሪኮች እንዲሁም ከሀዲያኖች ጋር ሴቶቻቸውን ማግባትም ኾነ የጋብቻ ቃል-ኪዳን መያዝ፡ ሴቶቻችንን ለነሱ መዳር ሐራም መኾኑን በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡ አያይዞም በአላህ ያመነች ሙስሊም ሴት በባርነት ቀንበር ውስጥ እንኳ ብትኾን፡ በአላህ ካጋራችው ውብና ቆንጆዋ ሙሽሪክ ሴት እጅግ የምትበልጥ እንደኾነች በጌታ አላህ ተመስክሮላታል፡፡ ምክንያቱም ሙሽሪኮች የሚጣሩት ወደ ጀሀነም እሳት ነውና፡፡ አላህ ይጠብቀን፡፡ በዚህ ሙሽሪክ በሚለው ጥቅላዊ ቃል ውስጥ ጣኦት አምላኪዎች ብቻ ሳይሆኑ አይሁዶችና ክርስቲያችም ይካተታሉ፡፡ እነሱም ዑዘይርን እና የመርየምን ልጅ ዒሳን (ዐለይሂማ-ሰላም) የአላህ ልጅ ናቸው በማለት ስለሚያሻርኩ ማለት ነው፡፡ ኾኖም በሌላ አንቀጽ ላይ የአህሉል ኪታብ (አይሁድና ክርስቲያን) ሴቶችን ከሙሽሪኮቹ በመነጠል፡ እነሱ ለሙስሊም ወንድ

የተፈቀዱ መኾኑን ኻስ አድርጎ (ነጥሎ አውጥቶ) በመስፈርት ነግሮናል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-

“…ከምእመናት ጥብቆቹም ከእነዚያ ከእናንተ በፊት መጽሐፍን ከተሰጡት ሴቶች ጥብቆቹም፤ ዘማዊዎችና (ዝሙተኞች) የምስጢር ወዳጅ ያዢዎች ሳትኾኑ ጥብቆች ኾናችሁ መህሮቻቸውን በሰጣችኋቸው ጊዜ (ልታገቡዋቸው የተፈቀዱ ናቸው)፡፡ ከእምነትም የሚመለስ ሰው በእርግጥ ሥራው ተበላሸ፡፡ በመጨረሻም ቀን እርሱ ከከሳሪዎቹ ነው፡፡” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡5)፡፡

በዚህ አንቀጽ መሠረት፡ መጽሐፍ ከተሰጣቸው ሴቶች (አሕሉል ኪታብ) መካከል ዝሙተኛ ያልኾነችውን ማግባት እንደሚቻል የአላህ ቃል ይገልጻል፡፡ ‹‹ጥብቆቹም›› የሚለው ከዚና የተጠበቁ መኾናቸውን የሚገልጽ ነው፡፡

የሐንበሊያው መዝሀብ ሊቅ የኾኑት ኢብኑ-ቁዳማህ (541-620 ሂጅ) ረሒመሁላህ ሲናገሩ፡- ‹‹በባርነት ቀንበር ውስጥ ያልኾኑ፡ በነጻነት የሚኖሩ የአህሉል ኪታብ ሴቶች ለትዳር ሐላል በመኾናቸው ጉዳይ ላይ በዑለሞች መሐል ምንም ልዩነት የለም›› ይላሉ፡፡ (አል-ሙግኒ 7/500)፡፡

5ኛ/ እነዚሁ የኢስላም ሊቃውንት የመጽሐፉ ባለቤት የኾኑ ሴቶችን ማግባት የተፈቀደ መኾኑን ሲገልጹ፡ እግረ መንገዱንም መሟላት ያለበትንም መስፈርት አብረው አስቀምጠዋል፡፡ እነዚህም መስፈርቶች፡-

ሀ/ ከዝሙት ጥብቅ የኾነች፡-
ለ/ ኢስላምን በሚዋጉ፡ ከሀዲያን በሚገዙት ሀገር ነዋሪ ያልኾነች ከኾነ የሚለው ነው፡፡

ከዚሁም ጋር አያይዘው በዘመናችን እራሷን ከዝሙት የጠበቀች አህሉል ኪታብ ማግኘት አስቸጋሪ መኾኑን በመጥቀስ፡ ደግሞም በትዳር ዓለም ፍቺ ቢከሰት፡ በምድራዊ ህግና ስርአት መሠረት፡ ልጆቹ ለሷ ተወስኖላት እሷም የሱን ልጆች ወደ ኩፍር ልትወስዳቸው ስለምትችል፣ ደግሞም ከአጅነቢ ወንዶች መቀላቀልና መሰል ሐራም ነገራትን ሃይማኖቷ ስለማይከለክላት በዚህ ሰበብ ከባለቤቷ አለመስማማቷን፣ ሃይማኖታዊ በዐል በሚደርስበት ጊዜ በቤቷ ከኢስላም ጋር የሚጻረሩ ሃይማኖታዊ ስርአቶችን ለመፈጸም ደፋ ቀና ስለምትል፡ ሙስሊም ደግሞ በቤቱ ከአላህ ውጭ ማንም ሊመለክ መፍቀድ ስለሌለበት ይህ ሁሉ ችግር ባለበት ሁኔታ ላይ እነሱን ለትዳር አስቦ መሄዱ አግባብ እንዳልኾነ ይገልጻሉ፡፡ ሙስሊሙ ወደነሱ ከሄደ የኛዎቹንስ ማን ያግባቸው? የሚለው በራሱ ሌላ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ ስለዚህም ዲን ያላትን ይምረጥ የሚለው የሁሉም ስምምነት ነው፡፡

ሐሰን ኢብኑ ዐሊይ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ይላል፡- “ከአላህ መልክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ‹‹የሚያጠራጥርህን ነገር ትተህ ወደማያጠራጥርህ ነገር ሂድ፡፡ እውነት መረጋጋት ሲኾን፡ ሀሰት መጠራጠር ነውና›› የሚለውን ምክር ያዝኩኝ” (ቲርሚዚይ 2442፣ አሕመድ 1630፣ ኢብኑ ሒባን 722)፡፡
ኢማሙል-መናዊ ረሒመሁላህ ይህን ሐዲሥ ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹መልካም ይሁን መጥፎ፣ ሐራም ይሁን ሐላል ለይተህ የማታውቀውን ነገር በመተው በመልካምነቱና በሐላልነቱ የማትጠራጠርበት ወደኾነው ነገር አዘንብል፡፡ ምክንያቱም እውነት የኾነን ነገር ልብ ይረጋጋበታል፡፡ ሐሰት ላይ ግን ልብ በጥርጣሬ ይዋልላል፡፡ ስለዚህም ነፍሲያህ በኾነ ጉዳይ ላይ ከተጠራጠረች ተወው፡ የሙእሚን ነፍስ በእውነት ነገር ላይ ትረጋጋለች በሀሰት ላይ ደግሞ ትጠራጠራለችና፡፡›› (ፈይዱል ቀዲር 3/529)፡፡

6ኛ/ ሙስሊሟ እሕት ግን፡ ከአህሉል ኪታብም ሆነ ከሙሽሪኮች (ጣኦታውያን) ወንዶችን ማግባት ያልተፈቀደላትን ሚስጥር ሲያብራሩ የኢስላም ሊቃውንቶች እንዲህ ይላሉ፡-

ሙስሊሞች በአላህና በመልክተኞቹ እንዲሁም በመጻሕፍቱ ሲያምኑ፡ በተለይም በሙሳና በዒሳ ነቢይነት፡ በተውራትና በኢንጂል የአላህ ቃልነት ባመኑ ጊዜ፡ ጌታ አላህ ደግሞ የተውራትና ኢንጂል ተከታይ ነን የሚሉ የአህሉል-ኪታብ ከዝሙት ጥብቅ ሴቶችን ለትዳር ፈቀደላቸው፡፡ አሕሉል ኪታብ የኾኑ ወንዶች ግን በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነቢይነት እና በቁርኣን አምላካዊ ቃልነት በካዱ ጊዜ፡ እስኪምኑ ድረስ የሙስሊም ሴቶችን በትዳር መጣመር እርም አደረገባቸው፡፡ ያመኑ ጌዜ ግን፡ ሴቶቻቸው ለኛ ሐላል እንደኾኑት፡ ሴቶቻችንም ለነሱ ሐላል ይኾናሉ ማለት ነው፡፡ ደግሞም በተጨማሪ ሌላው ምክንያት፡- በአብዝሐኛው ሴት በድክመቷ ሰበብ በባሏ ሥር ሆና ስትምመራ እንጂ ባሏን ስትመራ አይታይም፡፡ ስለዚህም ሙስሊሟ ሴት ለአህሉል ኪታብ ወንድ የተፈቀደች ብትኾን ኖሮ፡ በዲኗ ተፈትና በባሏ የክህደት ዲን ውስጥ በወደቀች ነበር፡፡ (ኢብኑ ባዝ ረሒመሁላህ፡ http://www.binbaz.org.sa/fatawa/1587 )፡፡

ከአቢ ሁረይራህ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ሴት ልጅ ለአራት ነገራት ለትዳር ትፈለጋለች፡፡ ለንብረቷ፣ ለዘሯ፣ ለውበቷና ለዲኗ፡፡ አንተ ግን ዲን ያላትን ምረጥ፡፡ እንቢ ካልክም እጅህ አፈር አፋሽ ይሁን” (ቡኻሪይ 4802፣ ሙስሊም 1466)፡፡

አላህ ሙስሊም ወንዶችን በሙስሊሟ ሴት የሚብቃቁ፣ ሙስሊም ሴቶችንም በሙስሊሙ ወንድ የሚብቃቁ ያድርጋቸው፡፡
ወላሁ አዕለም (አላህ የበለጠውን እውነታ ዐዋቂ ነው)

Shortlink http://q.gs/Ey5z0