“ሙሐመዱን ረሱሉሏህ” 9

ሼር ያድርጉ
368 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

4. የመጨረሻ ነቢይ ናቸው!!

ባለፈው ክፍል ስምንት ላይ በቁጥር ሦስት ስር የነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ተልእኮ በተመለከተ፡ የተላኩት ለመላው የሰው ዘር መሆኑን በሰፊው ተመልክተናል፡፡ ዛሬ የምንመለከተው ደግሞ፡ እሳቸው ከነቢያትና ከመልክተኞች የመጨረሻና መደምደሚያ መሆናቸውን ነው፡፡ ከሳቸው በኋላ የሚነሳ የአላህ ነቢይም ሆነ መልክተኛ የለም፡፡ የሚወርድ መለኮታዊ መጽሐፍም የለም፡፡ ነቢይነት በሳቸው እንደተደመደመው ሁሉ፡ መለኮታዊ መጻሕፍትም በቅዱስ ቁርኣን ተደምድመዋል፡፡ ይህን አቋም በተመለከተ የሚናገሩ ቁርኣዊና ነቢያዊ ሐዲሦችን እንመለከታለን ኢንሻአላህ፡-

1. ከቅዱስ ቁርኣን፡-

ሀ. በግልጽ መደምደሚያ ማለቱ፡-

” مَا كَانَ مُحَمَّدٌ أَبَا أَحَدٍ مِنْ رِجَالِكُمْ وَلَكِنْ رَسُولَ اللَّهِ وَخَاتَمَ النَّبِيِّينَ وَكَانَ اللَّهُ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمًا ” سورة الأحزاب 40.
“ሙሐመድ ከወንዶቻችሁ የአንድንም ሰው አባት አይደለም፤ ግን የአላህ መልክተኛና የነቢዮች መደምደሚያ ነው፤ አላህም በነገሩ ሁላ ዐዋቂ ነው።” (ሱረቱል አሕዛብ 40)፡፡
በዚህ አንቀጽ ውስጥ ‹‹የነቢዮች መደምደሚያ›› የሚለው ኃይለ-ቃል፡ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከአላህ ነቢያት የመጨረሻውና መደምደሚያ ነቢይ እንደሆኑ በግልጽ የሚያስረዳ ነው፡፡ በመሆኑም ከሳቸው በኋላ የሚመጣ የአላህ ነቢይ የለም፡፡ የሚወርድ አዲስ መለኮታዊ መጽሐፍም የለም፡፡

ለ. የቁርኣን አስጠንቃቂነት አለመገደቡ፡-

” قُلْ أَيُّ شَيْءٍ أَكْبَرُ شَهَادَةً قُلِ اللَّهُ شَهِيدٌ بَيْنِي وَبَيْنَكُمْ وَأُوحِيَ إِلَيَّ هَذَا الْقُرْآنُ لِأُنْذِرَكُمْ بِهِ وَمَنْ بَلَغَ أَئِنَّكُمْ لَتَشْهَدُونَ أَنَّ مَعَ اللَّهِ آلِهَةً أُخْرَى قُلْ لَا أَشْهَدُ قُلْ إِنَّمَا هُوَ إِلَهٌ وَاحِدٌ وَإِنَّنِي بَرِيءٌ مِمَّا تُشْرِكُونَ ” سورة الأنعام 19.
“«በምስክርነት ከነገሩ ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ማነው» በላቸው፡፡ (ሌላ መልስ የለምና) «አላህ ነው፡፡ በእኔና በእናንተ መካከል መስካሪ ነው፡፡ ይህም ቁርኣን እናንተንና የደረሰውን ሰው ሁሉ በርሱ ላስፈራራበት ወደኔ ተወረደ፡፡ ከአላህ ጋር ሌሎች አማልክት መኖራቸውን እናንተ ትመሰክራላችሁን» በላቸው፡፡ «እኔ አልመሰክርም» በላቸው፡፡ «እርሱ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ እኔም ከምታጋሩት ነገር ንጹሕ ነኝ» በላቸው፡፡” (ሱረቱል አንዓም 19)፡፡
በዚህ አንቀጽ መሰረት፡ ምስክርነቱ ከሁሉም በላጭ የሆነው አላህ፡ ለሳቸው ነቢይነት የሱ ምስክርነት በቂ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በመቀጠልም የቁርኣንን አስጠንቃቂነት ያለ ቦታና ጊዜ ገደብ እስከመጨረሻው ዘመን ቀጣይነት እንዳለው አስረዳ፡፡ በጥቅሱ ውስጥ ‹‹እናንተንና የደረሰውን ሰው ሁሉ›› የሚለው ቃል ትልቅ አስረጂ ነው፡፡
‹‹እናንተን›› ብሎ ሲናገር፡ በወቅቱ የነበሩ ሶሓባዎችን የሚጠቁም ሲሆን፡ ‹‹የደረሰውን ሰው ሁሉ›› የሚለው ደግሞ፡ ከዛ በኋላ የሚመጡ ትውልዶች፡ በየትኛውም ዘመን ይኑሩ በየትኛውም ቦታ፡ የቁርኣን መልክት ከደረሳቸው፡ ቁርኣን ለነሱ አስጠንቃቂ ነው፡፡ ሊያምኑበት ግድ ይላል ማለት ነው፡፡
በዚህ መሰረትም ‹‹የደረሰውን ሰው ሁሉ›› በማለቱ የቁርኣን አስጠንቃቂነት በጊዜም ሆነ በቦታ ካልተገደበ፡ የሳቸው ነቢይነትም የመጨረሻና መደምደሚያ ለመሆኑ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ከሳቸው በኋላ ሌላ ነቢይ ወይም መልክተኛ የሚመጣ ቢሆን ኖሮ፡ የቁርኣን አስጠንቃቂነት እስከዛ ነቢይ ድረስ ብቻ ነበር የሚሆነው፡፡ ከዛ በኋላ አዲስ የመጣውን ነቢይ መከተል ግድ ይሆናል፡፡ አሁን ግን የቁርኣን አስጠንቃቂነት በቦታም ሆነ በዘመን ሳይገደብ ‹‹የደረሰውን ሰው ሁሉ›› የሚመለከት ከሆነ፡ አዲስ ነቢይም ሆነ አዲስ መጽሐፍ አይወርድም ማለት ነው፡፡

ሐ. የመልክቱ ዓለም አቀፋዊነት፡-

” قُلْ يَا أَيُّهَا النَّاسُ إِنِّي رَسُولُ اللَّهِ إِلَيْكُمْ جَمِيعًا الَّذِي لَهُ مُلْكُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ لَا إِلَهَ إِلَّا هُوَ يُحْيِي وَيُمِيتُ فَآمِنُوا بِاللَّهِ وَرَسُولِهِ النَّبِيِّ الْأُمِّيِّ الَّذِي يُؤْمِنُ بِاللَّهِ وَكَلِمَاتِهِ وَاتَّبِعُوهُ لَعَلَّكُمْ تَهْتَدُونَ ” سورة الأعراف 158
“(ሙሐመድ ሆይ!) በላቸው፦ እላንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ወደ እናንተ #ወደሁላችሁም የአላህ መልክተኛ ነኝ፤(እርሱም) ያ የሰማይና የምድር ንግስና ለርሱ ብቻ የሆነ ነው፤ እርሱ እንጂ ሌላ አምላክ የለም፤ ሕያው ያደርጋል፤ ይገድላልም፤ በአላህና በዚያም በአላህና በቃላቶቹ በሚያምነው የማይጽፍ የማያነብ ነብይ በሆነው መልክተኛው እመኑ፤ ቅንንም መንገድ ትመሩ ዘንድ ተከተሉት።” (ሱረቱል አዕራፍ 158)፡፡
ይህ አንቀጽ የነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ተልእኮ ዐለም-አቀፋዊነት ያስረዳል፡፡ ለመላው የሰው ዘር የተላኩ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ በተለይ ‹‹ወደ ሁላችሁም›› የሚለው ቃል፡ በወቅቱ የነበሩትንም ወደፊት የሚመጡትንም ሰዎች ይመለከታል፡፡ በሌላ አነጋጋር እሳቸው የነቢያት መደምደሚ መሆናቸውን ይገልጻል ማለት ነው፡፡

መ. ዲኑ የተሟላ መመሪያን ማቀፉ፡-

“…الْيَوْمَ أَكْمَلْتُ لَكُمْ دِينَكُمْ وَأَتْمَمْتُ عَلَيْكُمْ نِعْمَتِي وَرَضِيتُ لَكُمُ الْإِسْلَامَ دِينًا…” سورة المائدة 3.
“…ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ። ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ…” (ሱረቱል ማኢዳህ 3)፡፡
በዚህ አንቀጽ ስር አላህ በባሪዎቹ ላይ የዋለውን ጸጋ በማውሳት ለጋስነቱን ይገልጻል፡፡ ከጸጋዎቹም አንዱ ለዚህ ኡምማ ዲኑን ከመመሪያ አንጻር የተሟላ አድርጎ መስጠቱን በመግለጽ ነው፡፡ በርግጥም ይህ ዲን ሙሉ ነው፡፡ ለመንፈሳዊ ህይወትም ሆነ ለስጋዊ ኖሮ አስፈላጊውን ህግ በተሟላ መልኩ አቅፏል፡፡ ምንም አይነት ጭማሬን አይቀበልም፡፡ የጎደለው ነገር የለምና፡፡ ህጉ በየትኛውም ቦታና በየትኛውም ዘመን፡ ለየትኛውም አይነት ህዝብ ስራ ላይ መዋል ይችላል፡፡

ታዲያ የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሸሪዓህ ፍጹም የተሟላ መመሪያን ያቀፈ ህግ ከሆነ፡ ሌላ ነቢይ የሚመጣበት፡ ሌላ መለኮታዊ መጽሐፍት የሚወርድበት ምክንያት ምንድነው? በርግጥም ሌላ አዲስ ነቢይ አይመጣም!!

ሠ. መለኮታዊ ጥበቃ መደረጉ፡-

” إِنَّا نَحْنُ نَزَّلْنَا الذِّكْرَ وَإِنَّا لَهُ لَحَافِظُونَ ” سورة الحجر 9
“እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፡፡ እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን፡፡” (ሱረቱል ሒጅር 9)፡፡
ከዚህ በፊት የነበሩ ቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት ጥበቃ የሚደረግላቸው መጽሐፉ በተሰጣቸው ነቢያትና በተከታዮቻቸው አማካይነት ነበር (አል-ማኢዳህ 44)፡፡ አላህ እነዚህን መጽሐፍት ለመጠበቅ ቃል አልገባላቸውም፡፡ በመሆኑም ከነቢያቱ ህልፈትና ከጊዜ መርዘም በኋላ በመጽሐፍቶች ላይ የሰው እጅ ገባ፡፡ የአላህ ቃል ከሰው ሀሳብ ጋር ተቀላለቀለ፡፡ የመጽሐፎቹ ኦሪጂናል ቅርጽ ጠፋ (አል-በቀራህ 75.79፣ አን-ኒሳእ 46፣ አል-ማኢዳህ 41፣ አል-አንዓም 91)፡፡

ወደ ቅዱስ ቁርኣን ስንመጣ ግን የምናገኘው በተቃራኒው ነው፡፡አላህ እራሱ ኃላፊነቱን በመውሰድ መጽሐፉን ለመጠበቅ ቃል ገባለት፡፡ ምክንያቱም፡- ከቁርኣን በኋላ የሚወርድ ሌላ መጽሐፍ ስለሌላ፡ ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በኋላ የሚመጣ ሌላ ነቢይ ባለመኖሩ፡ አላህ ቃሉን ሊጠብቀው እራሱ ቃል ገባ፡፡ ለዚህም ጥበቃው ቁርኣንን በቃላቸው መያዝ (መሐፈዝ) የሚችሉ ባሮቹን በየዘመናቱ በሺዎች የሚቆጠሩትን ይመርጣል፡፡ የቅዱስ ቁርኣን ተጠብቆ መቆየት፡ በመጽሐፍ ላይ ተጽፎ መቆየቱ ብቻ ሳይሆን በአማኞችም አእምሮ በቃል ለመያዝ ገር እንዲሆንም በማድረግ ጭምር ነው፡፡ ቅዱስ ቁርኣን እንደ ቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት የሰው እጅ ቢገባበት ኖሮ ሃይማኖታዊ ማስረጃነቱ ትርጉም አልባ ይሆን ነበር፡፡ ትክክለኛውን የነቢያት አስተምህሮም ማወቅ ባልተቻለ ነበር፡፡

ረ. ሌላ እምነት አለመጠቀሱ፡-

” يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا آمِنُوا بِاللَّهِ وَرَسُولِهِ وَالْكِتَابِ الَّذِي نَزَّلَ عَلَى رَسُولِهِ وَالْكِتَابِ الَّذِي أَنْزَلَ مِنْ قَبْلُ وَمَنْ يَكْفُرْ بِاللَّهِ وَمَلَائِكَتِهِ وَكُتُبِهِ وَرُسُلِهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ فَقَدْ ضَلَّ ضَلَالًا بَعِيدًا ” سورة النساء 136
“እላንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው በዚያም በመልክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍ፣ በዚያም ከበፊቱ ባወረደው መጽሐፍ፣ እመኑ፤ በአላህና በመላክቱም፣ በመጽሐፎቹም፣ በመልክተኞቹም፣ በመጨረሻውም ቀን የካደ ሰው፣ (ከሰውነት) የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ።” (ሱረቱ-ኒሳእ 136)፡፡

በዚህ አንቀጽ መሰረት አላህ ከባሮቹ እምነትን ይፈልጋል፡፡ እሱም፡- በአላህ ብቸኛ ጌትነት፣ በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነቢይነት፣ በሳቸው ላይ በወረደው ቁርኣንና ከቁርኣን በፊት በወረዱት ቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት እንድናምን ነው፡፡ ከቁርኣን በፊት ባሉት እመኑ ብሎ ካዘዘን፡ ከቁርኣን በኋላ በሚመጣውስ ለምን እመኑ ተብለን አልታዘዝንም? እምነት ከተባለ ሁሉንም አምኖ መቀበል አይደለምን?
ይህ የሚያሳየው ከሳቸው በኋላ የሚላክ ነቢይም ሆነ የሚወርድ መለኮታዊ መጽሐፍ አለመኖሩን ነው፡፡ ያ ቢኖር ኖሮ እንድናምን በታዘዝን ነበር፡፡ አንዱን አምኖ ሌላውን መካድ አላህ ዘንድ ተቀባይነት የለውምና፡፡ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-
” إِنَّ الَّذِينَ يَكْفُرُونَ بِاللَّهِ وَرُسُلِهِ وَيُرِيدُونَ أَنْ يُفَرِّقُوا بَيْنَ اللَّهِ وَرُسُلِهِ وَيَقُولُونَ نُؤْمِنُ بِبَعْضٍ وَنَكْفُرُ بِبَعْضٍ وَيُرِيدُونَ أَنْ يَتَّخِذُوا بَيْنَ ذَلِكَ سَبِيلًا * أُولَئِكَ هُمُ الْكَافِرُونَ حَقًّا وَأَعْتَدْنَا لِلْكَافِرِينَ عَذَابًا مُهِينًا ” سورة النساء 151-150
“እነዚያ በአላህና በመልክተኞቹ የሚክዱ፣ በአላህና በመልክተኞቹም መካከል መለየትን የሚፈልጉ፣ በከፊሉም እናምናለን፣ በከፊልም እንክዳለን የሚሉ በዚህም መካከል መንገድን ሊይዙ የሚፈልጉ፤ እነዚያ በውነት ከሐዲዎቹ እነርሱ ናቸው። ለከሐዲዎችም አዋራጅን ቅጣት አዘጋጅተናል።” (ሱረቱ-ኒሳእ 150-151)፡፡

በዚህ መሰረት፡- በፊት በነበሩ ቀደምት ነቢያትና መለኮታዊ መጽሐፍት እንድናምን ታዘን፡ ከኋላ በሚመጣው ግን እመኑ አለማለቱ ከሳቸው በኋላ ሌላ ነቢይ እንደማይመታ፡ ከቁርኣንም በኋላ ሌላ መጽሐፍ እንደማይወርድ በግልጽ ይጠቁማል ማለት ነው፡፡

Shortlink http://q.gs/Ewir6