“ሙሐመዱን ረሱሉሏህ” 8

ሼር ያድርጉ
388 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

3. የተላኩት ለመላው የዓለም ህዝብ ነው!!

በቁጥር አንድ ትምሕርታችን ላይ ስለ ነቢይነታቸው በቀደምት ነቢያት፣ መለኮታዊ መጽሐፍትና ሊቃውንት አንደበት የተነገረ ትንቢት በሚለው ስር፡ ለሶስት ተከታታይ ክፍሎች የተነገረላቸውን ትንቢት አይተናል፡፡
በቁጥር ሁለት ላይ ደግሞ፡- ለነቢይነታቸው ከአላህ ዘንድ የተሰጣቸው ማስረጃ (ሙዕጂዛ) የሚለውን፡ ለአራት ተከታታይ ክፍሎች ስንመለከት ቆይተናል፡፡ ዛሬ ደግሞ አላህ ፈቃዱ ከሆነ የተላኩት ለነማነው? የሚለውን እንመለከታለን ኢንሻአላህ፡፡
ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከቀደምት ነቢያትና መልክተኞች ከሚለያቸው አንዱ ለሁሉም የሰው ዘር መልክተኛ ሆነው መላካቸው ነው፡፡ ከሳቸው በፊት የነበሩት በጠቅላላ የተላኩት ለህዝቦቻቸው ነው፡፡
አላህ በየጊዜው ነቢያትን በተከታታይ ያስነሳ ስለነበር፡ ነቢይ በሞተ ቁጥርም ሌላ ነቢይ ይተካው ስለነበር፡ ለሁሉም ህዝቦች መልክተኛ ከራሳቸው ህዝብ ተልኮላቸዋል (አን-ነሕል 36)፡፡ ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በኋላ ግን የሚላክ ነቢይም ሆነ መልክተኛ ባለመኖሩ አላህ የሳቸውን መልክተኝነት ለመላው ህዝብ በማድረግ ነቢይነትን በሳቸው ደመደመው (ሱረቱል አሕዛብ 40)፡፡
عَنْ جَابِرِ بْنِ عَبْدِ اللَّهِ قَالَ: قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: ” أُعْطِيتُ خَمْسًا لَمْ يُعْطَهُنَّ أَحَدٌ قَبْلِي: …، وَبُعِثْتُ إِلَى النَّاسِ كَافَّةً، وَكَانَ النَّبِيُّ يُبْعَثُ إِلَى قَوْمِهِ خَاصَّةً ” رواه البخاري.
ጃቢር ኢብኒ ዐብዲላህ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ከኔ በፊት ለነበሩት (ነቢያት) ያልተሰጣቸው አምስት ነገር ተሰጠኝ፡፡….ለሰዎች ሁሉ መልክተኛ ሆኜ ተላክሁ፡፡ (ከኔ በፊት የነበረ) ነቢይ ግን ለህዝቦቹ ብቻ ይላክ ነበር” (ቡኻሪይ 335)፡፡
ከዚህ በመቀጠል የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ተልእኮ ለመላው ህዝብ መሆኑን የሚያመላክቱ ማስረጃዎችን እናቀርባለን፡-

ሀ. በቀጥታ ለዓለማት እንደተላኩ መነገሩ፡-

ቅዱስ ቁርኣን ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ለዓለማት መላካቸውን በቀጥታ ቋንቋ እንዲህ በማለት ይገልጻል፡-
” وَمَا أَرْسَلْنَاكَ إِلَّا رَحْمَةً لِلْعَالَمِينَ * قُلْ إِنَّمَا يُوحَى إِلَيَّ أَنَّمَا إِلَهُكُمْ إِلَهٌ وَاحِدٌ فَهَلْ أَنْتُمْ مُسْلِمُونَ * فَإِنْ تَوَلَّوْا فَقُلْ آذَنْتُكُمْ عَلَى سَوَاءٍ وَإِنْ أَدْرِي أَقَرِيبٌ أَمْ بَعِيدٌ مَا تُوعَدُونَ ” سورة الأنبياء 109-107
“(ሙሐመድ ሆይ!) #ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም። ያ ወደኔ የሚወረደው፣ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት ነው፤ ታዲያ እናንተ ፍጹም ታዛዦች ናችሁን? በላቸው። እምቢም ቢሉ (በማወቅ) በእኩልነት ላይ ሆነን (የታዘዝኩትን) አስታወቅኋችሁ፤ የምትስፈራሩበትም ነገር ቅርብ፣ ወይም ሩቅ፣ መሆኑን አላውቅም፤ በላቸው።” (ሱረቱል አንቢያእ 107-109)፡፡

ለ. ለሰዎች ሁሉ በማለት መናገሩ፡-

ሌላው ማስረጃችን፡- አላህ እሳቸውን የላከው ለሰዎች ሁሉ ነው በማለት መናገሩ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው፡- በየትኛውም ቦታ ሆነ በየትኛውም ጊዜ የሚኖር የሰው ዘር በጠቅላላ የሳቸው ነቢይነት ይመለከተዋል፡ ሊያምንባቸውም ግድ ይላል ማለት ነው፡፡ ቀጣዮቹ ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾች ይህን ይበልጥ ያስረዳሉ፡-
” مَا أَصَابَكَ مِنْ حَسَنَةٍ فَمِنَ اللَّهِ وَمَا أَصَابَكَ مِنْ سَيِّئَةٍ فَمِنْ نَفْسِكَ وَأَرْسَلْنَاكَ لِلنَّاسِ رَسُولًا وَكَفَى بِاللَّهِ شَهِيدًا ” سورة النساء 79
“ከደግ ነገር የሚያገኝህ ከአላህ (ችሮታ) ነው፤ ከመከራም የሚደርስብህ ከራስህ (ጥፋት የተነሳ) ነው፤ #ለሰዎችም ሁሉ መልክተኛ ኾነህ ላክንህ መስካሪም በአላህ በቃ።” (ሱረቱ-ኒሳእ 79)፡፡
” قُلْ يَا أَيُّهَا النَّاسُ إِنِّي رَسُولُ اللَّهِ إِلَيْكُمْ جَمِيعًا الَّذِي لَهُ مُلْكُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ لَا إِلَهَ إِلَّا هُوَ يُحْيِي وَيُمِيتُ فَآمِنُوا بِاللَّهِ وَرَسُولِهِ النَّبِيِّ الْأُمِّيِّ الَّذِي يُؤْمِنُ بِاللَّهِ وَكَلِمَاتِهِ وَاتَّبِعُوهُ لَعَلَّكُمْ تَهْتَدُونَ ” سورة الأعراف 158
“(ሙሐመድ ሆይ!) በላቸው፦ እላንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ወደ እናንተ #ወደሁላችሁም የአላህ መልክተኛ ነኝ፤(እርሱም) ያ የሰማይና የምድር ንግስና ለርሱ ብቻ የሆነ ነው፤ እርሱ እንጂ ሌላ አምላክ የለም፤ ሕያው ያደርጋል፤ ይገድላልም፤ በአላህና በዚያም በአላህና በቃላቶቹ በሚያምነው የማይጽፍ የማያነብ ነብይ በሆነው መልክተኛው እመኑ፤ ቅንንም መንገድ ትመሩ ዘንድ ተከተሉት።” (ሱረቱል አዕራፍ 158)፡፡
” وَمَا أَرْسَلْنَاكَ إِلَّا كَافَّةً لِلنَّاسِ بَشِيرًا وَنَذِيرًا وَلَكِنَّ أَكْثَرَ النَّاسِ لَا يَعْلَمُونَ ” سورة سبأ 28
“አንተንም #ለሰዎች ሁሉ በመላ፣ አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን ቢሆን እንጂ አልላክንህም፤ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም።” (ሱረቱ ሰበእ 28)፡፡

ሐ. ከዐረቦች ውጪ ያሉትን መጣራታቸው፡-

የነቢዩ ሙሐመድ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ሃይማኖታዊ ጥርሪ ዐረቦቹ ላይ ብቻ የተገደበ አልነበረም፡፡ የመጽሐፉ ሰዎችን (አይሁዶችንና ክርስቲያኖችንም) ያቀፈ ነበር፡፡ እነሱንም ወደ ኢስላም ጥርሪ እንዲያደርጉላቸው ታዘዋል፡፡ ይህም ተልእኮአቸው ለመላው የሰው ዘር ለመሆኑ ሌላ አስረጂ ነው፡፡

ማረጋገጫውን ከቁርኣን እንመልከት፡-
” إِنَّ الدِّينَ عِنْدَ اللَّهِ الْإِسْلَامُ وَمَا اخْتَلَفَ الَّذِينَ أُوتُوا الْكِتَابَ إِلَّا مِنْ بَعْدِ مَا جَاءَهُمُ الْعِلْمُ بَغْيًا بَيْنَهُمْ وَمَنْ يَكْفُرْ بِآيَاتِ اللَّهِ فَإِنَّ اللَّهَ سَرِيعُ الْحِسَابِ * فَإِنْ حَاجُّوكَ فَقُلْ أَسْلَمْتُ وَجْهِيَ لِلَّهِ وَمَنِ اتَّبَعَنِ وَقُلْ لِلَّذِينَ أُوتُوا الْكِتَابَ وَالْأُمِّيِّينَ أَأَسْلَمْتُمْ فَإِنْ أَسْلَمُوا فَقَدِ اهْتَدَوْا وَإِنْ تَوَلَّوْا فَإِنَّمَا عَلَيْكَ الْبَلَاغُ وَاللَّهُ بَصِيرٌ بِالْعِبَادِ ” سورة آل عمران 20-19
“አላህ ዘንድ (የተወደደ) ሃይማኖት ኢስላም ብቻ ነዉ፣ እነዚያም መጽሐፉን የተሰጡት ሰዎች በመካከላቸዉ ላለዉ ምቀኝነት እዉቀቱ ከመጣላቸዉ በኋላ እንጅ አልተለያዩም፤ በአላህም አንቀጾች የሚክድ አላህ ምርመራዉ ፈጣን ነዉ:: ቢከራከሩህም :- ፊቴን ለአላህ ሰጠሁ፤ የተከተሉኝም ሰዎች (እንደዚሁ ለአላህ ሰጡ) በላቸዉ፤ ለእነዚያም #መጽሐፍን ለተሰጡት ሰዎችና ለመሀይሞቹ፦ ሰለማችሁን? በላቸዉ፤ ቢሰልሙም በእርገጥ ተመሩ እምቢ ቢሉም በአንተ ላይ ያለበህ ማድረስ ብቻ ነዉ:: አላህም ባሮቹን ተመልካች ነው::” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 19-20)፡፡
” قُلْ يَا أَهْلَ الْكِتَابِ تَعَالَوْا إِلَى كَلِمَةٍ سَوَاءٍ بَيْنَنَا وَبَيْنَكُمْ أَلَّا نَعْبُدَ إِلَّا اللَّهَ وَلَا نُشْرِكَ بِهِ شَيْئًا وَلَا يَتَّخِذَ بَعْضُنَا بَعْضًا أَرْبَابًا مِنْ دُونِ اللَّهِ فَإِنْ تَوَلَّوْا فَقُولُوا اشْهَدُوا بِأَنَّا مُسْلِمُونَ ” سورة آل عمران 64
“#የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በኛና በናንተ መካከል ትክክል ወደሆነች ቃል ኑ፤ (እርሷም) አላህን እንጅ ሌላን ላንገዛ በርሱም ምንንም ላናጋራ፣ ከፊላችንም ከፊሉን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርጐ ላይይዝ ነዉ፤ በላቸዉ። እምቢ ቢሉም ፡- እኛ ሙስሊሞች መሆናችንን መስክሩ በሏቸው” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 64)፡፡
” يَا أَهْلَ الْكِتَابِ قَدْ جَاءَكُمْ رَسُولُنَا يُبَيِّنُ لَكُمْ كَثِيرًا مِمَّا كُنْتُمْ تُخْفُونَ مِنَ الْكِتَابِ وَيَعْفُو عَنْ كَثِيرٍ قَدْ جَاءَكُمْ مِنَ اللَّهِ نُورٌ وَكِتَابٌ مُبِينٌ * يَهْدِي بِهِ اللَّهُ مَنِ اتَّبَعَ رِضْوَانَهُ سُبُلَ السَّلَامِ وَيُخْرِجُهُمْ مِنَ الظُّلُمَاتِ إِلَى النُّورِ بِإِذْنِهِ وَيَهْدِيهِمْ إِلَى صِرَاطٍ مُسْتَقِيمٍ ” سورة المائدة 16-15
“#የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! ከመጽሐፉ ትሸሽጉት ከነበራችሁት ነገር ብዙውን ለእናንተ የሚገልጽ ከብዙውም የሚተው ሲሆን መልክተኛችን (ሙሐመድ) በእርግጥ መጣላችሁ። ከአላህ ዘንድ ብርሃንና ገላጭ መጽሐፍ በእርግጥ መጣላችሁ። አላህ ውዴታውን የተከተሉትን ሰዎች የሰላምን መንገዶች በርሱ ይመራቸዋል። በፈቃዱም ከጨለማዎች ወደ ብርሃን ያወጣቸዋል። ወደ ቀጥተኛም መንገድ ይመራቸዋል።” (ሱረቱል ማኢዳህ 15-16)፡፡

መ. ቁርኣን ለዓለማት የመጣ መሆኑ፡-

ቅዱስ ቁርኣን መመሪያነቱ ለዓለማት ህዝብ እንዲያገለግል ሆኖ ነው የወረደው፡፡ ቃሉ የወረደው ደግሞ በመልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) አማካኝነት ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነው፡፡ ስለዚህ ቁርኣን ለዓለም ህዝቦች መመሪያ ሆኖ መጣ ማለት እሳቸውም የተላኩት ለዓለም ህዝብ ነው ማለት ነው፡፡ ይህንን የሚያስረዱ እጅግ በርካታ ጥቅሶች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ፡-
” أُولَئِكَ الَّذِينَ هَدَى اللَّهُ فَبِهُدَاهُمُ اقْتَدِهْ قُلْ لَا أَسْأَلُكُمْ عَلَيْهِ أَجْرًا إِنْ هُوَ إِلَّا ذِكْرَى لِلْعَالَمِينَ ” سورة الأنعام 90
“እነዚህ (ነቢያት)፤ እነዚያ አላህ የመራቸው ናቸው፡፡ በመንገዳቸውም ተከተል፡፡ «በእርሱ (በቁርአን) ላይ ምንም ዋጋ አልጠይቃችሁም፡፡ እርሱ #ለዓለማት ግሣጼ እንጅ ሌላ አይደለም» በላቸው፡፡” (ሱረቱል አንዓም 90)፡፡
” وَمَا تَسْأَلُهُمْ عَلَيْهِ مِنْ أَجْرٍ إِنْ هُوَ إِلَّا ذِكْرٌ لِلْعَالَمِينَ ” سورة يوسف 104
“በርሱም (በቁርአን) ላይ ምንም ዋጋ አትጠይቃቸውም፤ እርሱ #ለዓለማት ግሣጼ እንጂ ሌላ አይደለም።” (ሱረቱ ዩሱፍ 104)፡፡
” تَبَارَكَ الَّذِي نَزَّلَ الْفُرْقَانَ عَلَى عَبْدِهِ لِيَكُونَ لِلْعَالَمِينَ نَذِيرًا ” سورة الفرقان 1
“ያ ፉርቃንን በባሪያው ላይ፣ #ለዓለማት አስፈራሪ ይሆን ዘንድ፣ ያወረደው (አምላክ)፣ ክብርና ጥራት ተገባው።” (ሱረቱል ፉርቃን 1)፡፡
ሌሎችም ብዙ ብዙ…

Shortlink http://q.gs/EwltS