“ሙሐመዱን ረሱሉሏህ” 6

ሼር ያድርጉ
449 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

2. ለነቢይነታቸው ከአላህ ዘንድ የተሰጣቸው ማስረጃ

ሠ. የንፋስና የመላእክት ሰራዊት፡-

በአምስተኛው አመተ ሒጅራህ በኸንደቅ ዘመቻ (የአሕዛብ ዘመቻ) ላይ የተከሰተ ክስተት ነው፡፡ ሰበቡም፡- ከበኒ-ነዲር ጎሳ የሆኑ አይሁዶች ከመልክተኛው ጋር ገብተው የነበረውን ቃል-ኪዳን አፈረሱ፡፡ እሳቸውንም ለመግደል ሞከሩ፡፡ መልክተኛው ሰራዊታቸውን በመያዝ ሰዎቹ እጃቸውን እስኪሰጡ (እስኪማረኩ) ድረስ ከበቧቸው፡፡ ከዛም ከከተማው አባረሯቸው፡፡ በኒ-ነዲሮችም ቂምን በልባቸው በመያዝ፡ ዳግም ለመበቀል በማሰብ፡ የዐረብ ጎሳዎችን መዲናን በመውረር ላይ አነሳሷቸው፡፡ ከዐረቦቹም ቁረይሾች፣ ገጥፋን፣ በኑ-ሙርራህ፣ በኒ ሰሊም፣ በኒ አሰድ፣ የአይሁዶቹ በኒ ቁረይዟ ጎሳዎች ለወረራው ተስማሙ፡፡ የአላህ መልክተኛም (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ለአሕዛብ ዘመቻ ተዘጋጁ፡፡ በሰልማኑል ፋርሲይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ሃሳብ ሰጪነት፡ ሶሓባዎች ከነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ጋር በመሆን፡ በመዲና ዙሪያ፡ ሙሽሪኮች (አሕዛቦች) እንዳይገቡ ለመከላከል በሰሜን አቅጣጫ አንድ ምሽግን ቆፍረው መሽገው ነበር፡፡ አሕዛቦቹ መዲና ድንበር ሲደርሱ ለመግባት አቃታቸው፡፡ ግን ሶሐባዎቹ ተከበዋል፡፡ ረሀቡም ጠናባቸው፡፡ የአላህ መልክተኛም፡- “አላሁመ ኢነል-ዐይሸ ዐይሹል አኺራህ፣ ፈግፊር ሊል-አንሷሪ ወል-ሙሃጂራህ” ሲሉ፡ ሶሐባዎቹም ቀበል አደረጉና፡- “ነሕኑ-ለዚ ባየዕና ሙሐመዳ ዐለል-ጂሃዲ ማ-በቂና አበዳ” በማለት መለሱ፡፡ የመልክተኛው ንግግር ትርጉሙም፡- አላህ ሆይ! ኑሮ ማለት የአኼራ ነው፡፡ አንሷሮችንና ሙሃጂሮችን ይቅር በላቸው (ማራቸው) ሲሆን፡ የሶሐቦቹ ምላሽ ደግሞ፡- ከመልክተኛው ሙሐመድ (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ጋር በህይወት እስካለን ድረስ በጂሃድ ላይ ቃል የገባነው እኛው ነን! የሚል ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ወቅት በድንገት ከየት እንደመጣ ያልታወቀ ብርቱ ንፋስ እና የመላእክት ሰራዊት፡ የከሀዲያንን ችቦ ማጥፋት ጀመረ፣ ሃይላቸውን መከተ፣ ግንባታዎቻቸውን አፈራረሰ፣ ሴራዎቻቸውን በጣጠሰ፣ ፈረሶቻቸውንና ግመሎቻቸውን ደንብረው እንዲጠፉ አደረገ፡፡ እነዛም ከሩቅ ስፍራ ተጉዘው የመጡና ሙስሊሞችን ለረጅም ቀናት ከብበው የነበሩ የአሕዛብ ሰራዊት፡ የተዋረዱና የከሰሩ ሆነው ተመለሱ፡፡ የአላህ መልክተኛና ሶሐቦችም ይህን ቃል መደጋገም ጀመሩ፡- “አልሐምዱ ሊላሂ ወሕደህ፣ ሰደቀ ወዕደህ፣ ወነሰረ ዐብደህ፣ ወአዐዘ ጁንደህ፣ ወሀዘመል አሕዛበ ወሕደህ”፡፡ ትርጉሙም፡- ‹‹ምስጋና ለአንዱ አላህ ብቻ የተገባ ይሁን፣ ያ ቃሉን የፈጸመ ጌታ ለሆነው፣ ባሪያውንም ለረዳ፣ ሰራዊቱንም ላጠናከረ፣ የአሕዛብ ሰራዊትንም ብቻውን ላዋረደው ጌታ ምስጋና ይገባው›› ማለት ነው፡፡ ይህን በማስመልከትም ቀጣዩ አንቀጽ ወረደ፡-
“يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اذْكُرُوا نِعْمَةَ اللَّهِ عَلَيْكُمْ إِذْ جَاءَتْكُمْ جُنُودٌ فَأَرْسَلْنَا عَلَيْهِمْ رِيحًا وَجُنُودًا لَمْ تَرَوْهَا وَكَانَ اللَّهُ بِمَا تَعْمَلُونَ بَصِيرًا * إِذْ جَاءُوكُمْ مِنْ فَوْقِكُمْ وَمِنْ أَسْفَلَ مِنْكُمْ وَإِذْ زَاغَتِ الْأَبْصَارُ وَبَلَغَتِ الْقُلُوبُ الْحَنَاجِرَ وَتَظُنُّونَ بِاللَّهِ الظُّنُونَا ” سورة الأحزاب 10-9
“እላንተ ያመናችሁ ሆይ! ብዙ ሰራዊት በመጣችባችሁና በነሱ ላይ ነፋስንና ያላያችኋትን ሰራዊት በላክን ጊዜ፣ በናንተ ላይ (ያደረገላችሁን) የአላህ ጸጋ አስታውሱ፤ አላህም የምሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነው። ከበላያችሁም፣ ከናንተ በታችም፣ በመጡባችሁ ጊዜ ፣ዓይኖችም በቃበዙ፣ ልቦችም እላንቃዎች በደረሱና በአላህም ጥርጣሬዎችን በጠረጠራችሁ ጊዜ፤ (ያረገላችሁን አስታውሱ)” (ሱረቱል አሕዛብ 9-10)፡፡

ረ. የበድር ዘመቻ ክስተት፡-

ሶሓባዎች ከሙሽሪኮች ጋር ለመፋለም በመዘጋጀት ሁሉም ቦታውን ይዟል፡፡ በቁጥራቸው አናሳ (የጠላትን 1/3)፣ በኃይልም ደካማ በመሆናቸው ግን ስጋት ገብቷቸዋል፡፡ ይባስ ብሎም አላህ እንቅልፍን ለቀቀባቸው፡፡ ከፊሎቻቸው ደግሞ ኢሕቲላም (ጀናባ) ሆኑ፡፡ ሸይጧንም አጋጣሚውን በመጠቀም፡ እነሱን ከትግል ሜዳ ለመመለስ ጉትጎታና ከሞት ማስፈራራት ጀመረ፡፡ አላህም እንዲታጠቡበት፣ እንዲጠጡና ወደ ትግሉ ሜዳ ሲጓዙም መንገዱ ምቹ ይሆን ዘንድ ከላይ ዝናብን አወረደላቸው፡፡ የሙስሊሙ ሰራዊትና የጠላት ሰራዊትም ገና ሲገናኙ ከላይ የመላእክት ሰራዊት ወረደ፡፡ ገና በመጀመሪያው የትግል ሰዓት ከሀዲያን አስቀያሚ የሆነ ውርደትን ተከናነቡ፡፡ ይህን በተመለከተም ቀጣዩ አንቀጽ ወረደ፡-
“إِذْ يُغَشِّيكُمُ النُّعَاسَ أَمَنَةً مِنْهُ وَيُنَزِّلُ عَلَيْكُمْ مِنَ السَّمَاءِ مَاءً لِيُطَهِّرَكُمْ بِهِ وَيُذْهِبَ عَنْكُمْ رِجْزَ الشَّيْطَانِ وَلِيَرْبِطَ عَلَى قُلُوبِكُمْ وَيُثَبِّتَ بِهِ الْأَقْدَامَ * إِذْ يُوحِي رَبُّكَ إِلَى الْمَلَائِكَةِ أَنِّي مَعَكُمْ فَثَبِّتُوا الَّذِينَ آمَنُوا سَأُلْقِي فِي قُلُوبِ الَّذِينَ كَفَرُوا الرُّعْبَ فَاضْرِبُوا فَوْقَ الْأَعْنَاقِ وَاضْرِبُوا مِنْهُمْ كُلَّ بَنَانٍ ” سورة الأنفال 12-11
“ከርሱ በሆነው ጸጥታ (በጦር ግንባር) በእንቅልፍ በሸፈናችሁና ውሃንም በርሱ ሊያጠራችሁ፣ የሰይጣንን ጉትጎታ ከናንተ ሊያስወግድላችሁ ልቦቻችሁንም (በት ዕግሥት) ሊያጠነክርላችሁ፣ በርሱም ጫሞችን “(በአሸዋው ላይ) ሊያደላድልላችሁ፣ በናንተ ላይ ከሰማይ ባወረደላችሁ ጊዜ (አስታውሱ)።ጌታህ ወደ መላእክቱ፦ እኔ (በርዳታዬ) ከናንተ ጋር ነኝና፣ እነዚያን ያመኑትን አጥናኑ፤ በነዚያ በካዱት ልቦች ውስጥ ፍርሃትን በእርግጥ እጥላለሁ፤ ከአንገቶችም በላይ (ራሶችን) ምቱ፤ ከነሱም የቅርንጫፎችን መለያልይ ሁሉ ምቱ፤ ሲል ያወረደውን (አስታውስ)።” (ሱረቱል አንፋል 11-12)፡፡

ሰ. በሂጅራ መሀል የተከሰተ፡-

ቁረይሽ ነቢዩን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ለመግደል ወሰኑ፡፡ ወጣቱም ከተማይቱን ከብቦ ይጠባበቅ ጀመር፡፡ የአላህ መልክተኛ ግን በመሀከላቸው አልፈው ወጡ፡፡ አላህ አይናቸውን ሸፍኖት ነበርና፡፡ ከዛም በሒራእ ዋሻ ውስጥ ከባልደረባቸው አቡ-በከር ሲዲቅ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ጋር ተደበቁ፡፡ ጠላትም እሳቸውን ፍለጋ በዋሻው ጫፍ ላይ ቆሞ ይጠባበቅ ነበር፡፡ አይናቸውን ወደ ዋሻው ዝቅ ቢያረጉ እንኳ ማየት በሚችሉበት ቅርበት ያህል ተጠግተው ነበር፡፡ ግን አላህ አይናቸው ወደ ዋሻው ስር እንዳይመለከት አደረገ፡፡ ከዛም ኋላ ላይ ከዋሻው ወጥተው ሲጓዙ፡ ስልጡኑ የፋርስ ጦረኛ ሱራቀተ-ኢብኑ ማሊክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተመለከታቸው፡፡ በፈረሱ ላይ ሆኖ እሳቸውንና አባ በክርን ማሳደድ ጀመረ፡፡ መጨረሻም ላይ ደረሰባቸውና ልክ መልክተኛው ጋር ሲጠጋ፡ አራቱም የፈረሱ እግሮች አሸዋው ስር ሰመጡ፡ እሱም ከፈረሱ ላይ ወደቀ፡፡ እሳቸውን ለመግደል ሲፈልግና ሲቋምጥ የነበረውም ሰውዬ አሁን በተቃራኒው መልክተኛውን እንዳይገሉት በመስጋት መማጸን ጀመረ፡፡ ይህን በተመለከተ ደግሞ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-
“إِلَّا تَنْصُرُوهُ فَقَدْ نَصَرَهُ اللَّهُ إِذْ أَخْرَجَهُ الَّذِينَ كَفَرُوا ثَانِيَ اثْنَيْنِ إِذْ هُمَا فِي الْغَارِ إِذْ يَقُولُ لِصَاحِبِهِ لَا تَحْزَنْ إِنَّ اللَّهَ مَعَنَا فَأَنْزَلَ اللَّهُ سَكِينَتَهُ عَلَيْهِ وَأَيَّدَهُ بِجُنُودٍ لَمْ تَرَوْهَا وَجَعَلَ كَلِمَةَ الَّذِينَ كَفَرُوا السُّفْلَى وَكَلِمَةُ اللَّهِ هِيَ الْعُلْيَا وَاللَّهُ عَزِيزٌ حَكِيمٌ ” سورة التوبة 40
“(ነቢዩን) ባትረዱት እነዚያ የካዱት ሕዝቦች የሁለት (ሰዎች) ሁለተኛ ሆኖ (ከመካ) ባወጡት ጊዜ አላህ በእርግጥ ረድቶታል ሁለቱም በዋሻዉ ሳሉ ለጓደኛዉ ነዉና ባለ ጊዜ አላህ እርካታዉን በርሱ ላይ አወረደ፤ ባላያችኋቸዉም ሰራዊት አበረታው፤ የነዚያንም የካዱትን ሰዎች ቃል ዝቅተኛ አደረገ፤ የአላህም ቃል እርሷ ከፍተኛ ናት፤ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው።” (ሱረቱ-ተውባህ 40)፡፡

ሰ. የአቡ ጀህል መሐላና ውጤቱ፡-

አቡ ጀህል ነቢዩን (ዐለይሂ ሶላቱ ወስ-ሰላም) ሲሰግዱ ካያቸው፡ ከኋላ ጫንቃቸውን እረግጣለሁ ብሎ በላትና በዑዝዛ በመማል ለራሱ ቃል ገባ፡፡ አንድ ቀን ሲሰግዱ ያገኛቸውና፡ ለራሱ የገባውን ቃል ሊፈጽም ወደሳቸው ሄደ፡፡ አጠገባቸው እንደደረሰም በድንገት በእጁ እየተከላከለ ወደ ኋላው መመለስ ጀመረ፡፡ ምን ሆንክ? ሲሉት፡- በኔና በሱ መሀል የእሳት ጉድጓድ ይታየኛል፡ የሚያስፈራ ክንፍም አለ አላቸው፡፡ የአላህ መልክተኛም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- ወደ እኔ ትንሽ ጠጋ ቢል ኖሮ፡ መላእክት ሰውነቱን በብልት በብልት በቆራረጡት ነበር (ሙስሊም)፡፡ እንዲህ የሚለው የቁርኣን አንቀጽም ወረደ፡-
“أَرَأَيْتَ الَّذِي يَنْهَى * عَبْدًا إِذَا صَلَّى * أَرَأَيْتَ إِنْ كَانَ عَلَى الْهُدَى * أَوْ أَمَرَ بِالتَّقْوَى * أَرَأَيْتَ إِنْ كَذَّبَ وَتَوَلَّى * أَلَمْ يَعْلَمْ بِأَنَّ اللَّهَ يَرَى * كَلَّا لَئِنْ لَمْ يَنْتَهِ لَنَسْفَعًا بِالنَّاصِيَةِ * نَاصِيَةٍ كَاذِبَةٍ خَاطِئَةٍ * فَلْيَدْعُ نَادِيَهُ * سَنَدْعُ الزَّبَانِيَةَ * كَلَّا لَا تُطِعْهُ وَاسْجُدْ وَاقْتَرِبْ ” سورة العلق 19-9
“አየህን? ያንን የሚከለክለውን፣ ባሪያን በሰገደ ጊዜ፤ አየህን ንገረኝ (ተከልካዩ) በትክክለኛ መንገድ ላይ ቢሆን፣ ወይም (ፈጣሪውን) በመፍራት ቢያዝ፤ አየህን? ንገረኝ (ከልካዩ) ቢያስተባብልና (ከእምነት) ቢሸሽ፤ አላህ የሚያይ መሆኑን አያውቅምን? ይተው ባከለከል አናቱን ይዘን እንጎትተዋለን። ውሸታም ስሕተተኛ የሆነችውን አናቱን። ሸንጎውንም ይጥራ፤ (እኛም) ዘበኞቻችንን እንጠራለን። ይከልከል፤ አትታዘዘው፤ ስገድም፤ (ወደ አላህ) ተቃረብም።” (ሱረቱል ዐለቅ 9-19)

ታዲያ ይህ ሁሉ ነቢይ ለመሆናቸው በቂ ማስረጃ አይሆንምን?

Shortlink http://q.gs/EwluC