“ሙሐመዱን ረሱሉሏህ” 5

ሼር ያድርጉ
323 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

2. ለነቢይነታቸው ከአላህ ዘንድ የተሰጣቸው ማስረጃ

በክፍል አራት ላይ የነቢዩ ሙሐመድን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ነቢይነት ሊያረጋግጡ ከሚችሉ ማስረጃዎች ሁለቱን ተመልክተን ነበር፡፡ እነሱም፡- የጌታ አላህ ምስክርነት እና የቁርኣን ተአምርነት ማለት ነው፡፡ ከዛ የቀጠለውን ማስረጃችንን ዛሬ እንመለከታለን ኢንሻአላህ፡-

ሐ. “ኢስራእ” እና “ሚዕራጅ”

አላህ መልክተኛውን ሙሐመድን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ወደ “ሲድረቱል ሙንተሀ” (የነገሮች ሁሉ ማብቂያ ወደሆነችው ቁርቁራይቱ ዛፍ) ከሰባት ሰማይ በላይ ወዳለችው ሊወስዳቸው ፈለገ፡፡ ነገር ግን ካሉበት መካ በቀጥታ ወደ ሰማያት እንዲያርጉ አልፈለገም፡፡ ከዛ ይልቅ ከነበሩባት መካ ወደ “በይቱል መቅዲስ” (ፈልስጢን) በሌሊት እንዲጓዙ አደረገ፡፡

በዚያም ነቢያትን ሁሉ ተገናኝነተው፡ ኢማም ሁነው ካሰገዱ በኋላ፡ ከበይቱል መቅዲስ ደግሞ ወደ ሰማያት በዛው ሌሊት ውስጥ እንዲያርጉ ተደረገ፡፡ ወደ ሰማያትም ካረጉ በኋላ ከጌታችን ጋር በቀጥታ ተነጋግረው (ያለ መልአክ ጣልቃ ገብነት) የአምስት ወቅት ሶላት ግዳጅነትን ይዘው መጥተዋል፡፡ በአንድ ሌሊት ከ መካ ወደ በይቱል መቅዲድ ያደረጉት ጉዞ “ኢስራእ” ይባላል፡፡

ወራት የሚያስኬደውን ርቀት በአንድ ለሊት መጓዝ መቻላቸው፡ ለነቢይነታቸው በቂ ማስረጃ ነው፡፡ በወቅቱ የነበሩ ከሀዲያኖች የሳቸውን ነቢይነት አልተቀበሉም ነበርና፡ ይህን ወሬ ሲሰሙ ወደ አቡበከር-ሲዲቅ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ዘንድ በመምጣት፡- ወዳጅህ በአንድ ሌሊት በይቱል መቅዲስ ሄድኩ ይላል! ሲሉት፡ አቡበክርም፡- እሱ ካለ እውነቱን ነው፡ አይዋሽም በማለት የእምነት ምስክርነት ቃሉን ሰጣቸው፡፡

አይሁዶችም ለምን ስለ በይቱል መቅዲስ አንዳንድ ነገር በመጠየቅ መሄድ አለመሄዳቸውን አናጣራም? በማለት፡ ወደሳቸው በመምጣት ስለ ሀገሩ ሁኔታ ጠየቋቸው፡፡ እሳቸውም የበይቱል መቅዲስን አቀማመጥ፡ የነጋዴዎቹን ሁኔታ፡ ከየትኛው ጎሳ እንደሆኑ ሁሉ በመጨመር ዘርዝረው አስረዷቸው፡፡ እሳቸው ከዚህ በፊት ወደዚያ ሀገር እንዳልሄዱ ሁሉም ያውቃል፡፡ ታዲያ ይህን ሁሉ መናገራቸው በአላህ ፈቃድ በአንድ ሌሊት መጓዛቸውን አመላካች ነው ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ቁርኣንም እንዲህ ይላል፡-

“سُبْحَانَ الَّذِي أَسْرَى بِعَبْدِهِ لَيْلًا مِنَ الْمَسْجِدِ الْحَرَامِ إِلَى الْمَسْجِدِ الْأَقْصَى الَّذِي بَارَكْنَا حَوْلَهُ لِنُرِيَهُ مِنْ آيَاتِنَا إِنَّهُ هُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ ” سورة الإسراء 1
“ያ ባሪያውን ከተከበረው መስጊድ ወደዚያ ዙሪያውን ወደ ባረክነው ወደ ሩቁ መስጊድ በሌሊት ውስጥ ያስኼደው (ጌታ) ጥራት ይገባው፤ ከታምራቶቻችን ልናሳየው (አስኼድነው)፤ እነሆ እርሱ (አላህ) ሰሚው ተመልካቺው ነው።” (ሱረቱል ኢስራእ 1)፡፡

ከበይቱል መቅዲስ ደግሞ ወደ ሰማያት ማረጋቸው “ሚዕራጅ” ይባላል፡፡ ይህን ጉዳይ ደግሞ ቁርኣን በሌላ ክፍል ላይ እንዲህ ይገልጸዋል፡-
“مَا كَذَبَ الْفُؤَادُ مَا رَأَى * أَفَتُمَارُونَهُ عَلَى مَا يَرَى * وَلَقَدْ رَآهُ نَزْلَةً أُخْرَى * عِنْدَ سِدْرَةِ الْمُنْتَهَى * عِنْدَهَا جَنَّةُ الْمَأْوَى * إِذْ يَغْشَى السِّدْرَةَ مَا يَغْشَى * مَا زَاغَ الْبَصَرُ وَمَا طَغَى * لَقَدْ رَأَى مِنْ آيَاتِ رَبِّهِ الْكُبْرَى ” سورة النجم 18-11
“(ነቢዩ በዓይኑ) ያየውን ልቡ አልዋሸም። ታዲያ በሚያየው ላይ ትከራከሩታላችሁን? በሌላይቱም መውረድ ጊዜ በእርግጥ አይቶታል። በመጨረሻይቱ ቁርቁራ አጠገብ፤ እርሷ ዘንድ መኖሪያይቱ ገነት ያለች ስትሆን። ቁርቁራይቱን የሚሸፍን ነገር በሚሸፍናት ጊዜ (አየው)።ዓይኑ (ካየው) አልተዘነበለም፤ ወሰንም አላለፈም። ከጌታው ታምራቶች ታላላቆቹን በእርግጥ አየ።” (ሱረቱ-ነጅም 11-18)፡፡

የአላህ መልክተኛም በዚህ የሰማይ እርገታቸው ላይ ጌታችንን ባይመለከቱትም፡ መለኮታዊ ቃሉን ግን ያለ መልአክ አማካኝነት ሰምተዋል፡፡ ጀነትና ጀሀነምንም ተመልክተዋል፡፡

መ. የጨረቃ ለሁለት መከፈል፡-

የተፈጥሮ ስርኣት ሁሌም የጸና፡ ቋሚና የማይቀያየር ህግ ነው፡፡ አላህ ሲፈልግና ሲፈቅድ ግን ሁሉም ለርሱ ታዛዥ ነው፡፡ ጨረቃ አንድ አካል ነው፡፡ ማንም ሰው ለሁለት ሊከፍለው አይችልም፡፡ ታዲያ የመካ ሙሽሪኮች ወደ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) በመምጣት፡- እርሶ እውነተኛ ነቢይ ከሆኑ፡ ለማስረጃነት ጨረቃ ለሁለት ተከፍላ ማየት እንፈልጋለን! አሉ፡፡ አላህ ለሳቸው ማስረጃ ይሆን ዘንድ ጨረቃን ለሁለት ከፈለላቸው፡፡ እሳቸውም፡- በሉ እንግዲህ አሁን በአይናችሁ አይታችኋልና መስክሩ አሏቸው፡፡ እነሱም፡- ሙሐመድ አይናችን ላይ ደግሞብን ነው አሉ፡፡ ያዩትን ነገር ማስተባበል አልቻሉም፡፡ ላለማመን ግን አይናችን ላይ ተደገመብን! አሉ፡፡ ከመሐከላቸው አንዱም፡- እውነት ይህ ነገር ተደግሞብን ከሆነ፡ ድግምቱ ሌላ ቦታ አይሰራምና፡ ነጋዴዎች ወደዚህ ሀገር ሲገቡ በዚህ ቀን ምን ተከስቶ እንደነበር እንጠይቃቸው የሚል ሀሳብ አቀረበ፡፡ እነሱም በሀሳቡ ተስማሙ፡፡ በሌላ ቀን ነጋዴዎች ወደ ሀገሩ ሲገቡ፡- በዚህ ቀን በሀገራችሁ ምን ተከስቶ ነበር? ብለው ቢጠይቋቸው፡ የእነሱም ምላሽ፡- ጨረቃ ለሁለት ተከፍላ ተመልክተን ነበር አሉ፡፡ አሁንም ሰዎቹ በነጋዴዎቹ ምስክርነት ከማመን ይልቅ፡- ድግምቱ ቀጣይና ሁሉን ያካበበ ነው! ብለው እርፍ!!፡፡ ጌታ አላህም እንዲህ አለ፡-

“اقْتَرَبَتِ السَّاعَةُ وَانْشَقَّ الْقَمَرُ * وَإِنْ يَرَوْا آيَةً يُعْرِضُوا وَيَقُولُوا سِحْرٌ مُسْتَمِرٌّ * وَكَذَّبُوا وَاتَّبَعُوا أَهْوَاءَهُمْ وَكُلُّ أَمْرٍ مُسْتَقِرٌّ ” سورة القمر 3-1
“ስዓቲቱ (የትንሣኤ ቀን) ተቃረበች፤ ጨረቃም ተገመሰ፤ ታምርንም ቢያዩ (ከአምነት) ይዞራሉ (ይህ) ዘውታሪ ደግመት ነውም ይላሉ፡፡ አስተባበሉም፤ ዝንባሌዎቻቸውንም ተከተሉ፤ ነገርም ሁሉ ( ወሰን አለው)፤ ረጊ ነው::” (ሱረቱል ቀመር 1-3)፡፡

Shortlink http://q.gs/Ewlub