“ሙሐመዱን ረሱሉሏህ” 4

ሼር ያድርጉ
488 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

2. ለነቢይነታቸው ከአላህ ዘንድ የተሰጣቸው ማስረጃ

በቁጥር አንድ ትምሕርታችን ስለ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነቢይነት በቀደምት ነቢያት፣ መለኮታዊ መጽሐፍትና በመጽሐፍቱ ሊቃውንት አንደበት የተነገረ ትንቢት በሚለው ስር ለሶስት ተከታታይ ክፍሎች መረጃዎቹን ስንማር ቆይተናል አልሐምዱ ሊላህ፡፡
አሁን ደግሞ ጌታ አላህ ፈቃዱ ከሆነ በሁለተኛው ነጥብ ስር፡ ነቢይነታቸውን የሚጠቁሙ ማስረጃዎች ምን ምን እንደሆኑ በመጠኑ እንቃኛለን ኢንሻአላህ፡፡ መልካም ንባብ፡-

” لَقَدْ أَرْسَلْنَا رُسُلَنَا بِالْبَيِّنَاتِ وَأَنْزَلْنَا مَعَهُمُ الْكِتَابَ وَالْمِيزَانَ لِيَقُومَ النَّاسُ بِالْقِسْطِ…” سورة الحديد 25
“መልክተኞቻችንን በግልጽ ማስረጃዎች በእርግጥ ላክን፤ ሰዎችም በትክክል ቀጥ እንዲሉ መጽሐፎችንና ሚዛንን ወደነርሱ አወረድን…” (ሱረቱል ሐዲድ 25)፡፡

በዚህ የአላህ ቃል መሰረት፡ ጌታ አላህ ወደ ህዝቦቻቸው የሚላኩ መልክተኞች በጠቅላላ፡ የአላህ መልክተኛና ነቢይ መሆናቸውን ሊያሳይ የሚችል ማስረጃ እንደሚሰጣቸው መረዳት ይቻላል፡፡

ምክንያቱም፡- ነቢይም ሆነ ረሱል የሚመረጠው ከሰዎች ውስጥ በመሆኑ፡ አንድ ሰው ከሰዎች መካከል ተነስቶ፡- እኔ ከናንተ ውስጥ በአላህ ተመርጬ ወደናንተ የተላክሁ የአላህ መልክተኛ ነኝ! ብሎ ቢናገር፡ ማንም በቀላሉ አይቀበለውም፡፡ ሰዎች እሱን የሚያውቁት ከዚህ በፊት እንደነሱ የሚበላና የሚጠጣ፡ የእለት ጉሮሮውን ለመዝጋት በስራ ላይ ደፋ ቀና የሚል፡ ትዳርን መስርቶ ልጆችን የወለደ መሆኑን ነው፡፡
አሁን ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው እሱ ነቢይ ነኝ ሊል የቻለው? ከማኃበረሰቡስ በተለየ መንገድ እሱን ከአላህ ጋር ሊያገናኘው የሚችል የነቢይነት ማዕረግ እንደተሰጠው በምን ማወቅ ይቻላል? ለዚህ ሁሉ ግልጽ ማስረጃ ያስፈልጋል፡፡ ያለ ማስረጃ ከሆነማ፡ በአቋራጭ በህዝቦቻቸው ላይ ለመክበር ሲሉ ሀሰተኞችም ነቢይ ነን ማለታቸው አይቀርምና፡፡ ታዲያ የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነቢይነትን የሚጠቁሙ ማስረጃዎች ምን ነበሩ? በመጠኑ እንዳስሰው፡-

ሀ. የአላህ ምስክርነት፡-

ከመረጃዎች ሁሉ በላጩና ዋነኛው ማስረጃችን ነው፡፡ እራሱ ነቢይና መልክተኛ አድርጎ ከላካቸው አላህ የበለጠ ምስክርነት የትም የለም፡፡ ጌታ አላህ አንተ መልክተኛዬ ነህ በማለት መስክሯል፡፡ ይህ ምስክርነትም በቂ እንደሆነ ገልጾአል፡-
” وَيَقُولُ الَّذِينَ كَفَرُوا لَسْتَ مُرْسَلًا قُلْ كَفَى بِاللَّهِ شَهِيدًا بَيْنِي وَبَيْنَكُمْ وَمَنْ عِنْدَهُ عِلْمُ الْكِتَابِ ” سورة الرعد 43
“እነዚያም የካዱት ሰዎች፥ መልክተኛ አይደለህም ይላሉ፤ በኔና በናንተ መካከል መስካሪ በአላህና እርሱ ዘንድ የመጽሐፉ ዕውቀት ባለው ሰው በቃ በላቸው።” (ሱረቱ-ረዕድ 43)፡፡

በዚህ ቅዱስ ቃል ውስጥ አላህ ለመልክተኛው ትእዛዝን ያስተላልፋል፡፡ ትእዛዙም፡- በእኔ እውነተኛነትና በናንተ ማስተባበል መሀል የአላህ ምስክርነት እንዲሁም የመጽሐፉ ዕውቀት የነበራቸው (ኢስላምን የተቀበሉ የአይሁድና የክርስቲያን ሊቃውንት) ምስክርነት በቂ ነው፡፡ የናንተ ማስተባበል እኔን ነቢይነቴን ወይም የአላህ መልክተኛ መሆኔን አይቀይረውም በላቸው የሚል ነው፡፡ መስካሪነትም በአላህ በቃ!!!!

” إِذَا جَاءَكَ الْمُنَافِقُونَ قَالُوا نَشْهَدُ إِنَّكَ لَرَسُولُ اللَّهِ وَاللَّهُ يَعْلَمُ إِنَّكَ لَرَسُولُهُ وَاللَّهُ يَشْهَدُ إِنَّ الْمُنَافِقِينَ لَكَاذِبُونَ ” سورة المنافقون 1
“መናፍቃን በመጡህ ጊዜ አንተ የአላህ መልክተኛው መሆንህን በእርግጥ (ምለን) እንመሰክራለን ይላሉ፤ አላህም አንተ በእርግጥ መልዕክተኛ መሆንህን ያውቃል፤ አላህም መናፍቃን (ከልብ እንመሰክራለን በማለታቸው) ውሸታሞች መኾናቸውን ይመሰክራል።” (ሱረቱል ሙናፊቁን 1)፡፡

በዚህ አንቀጽ ውስጥም፡- ሙናፊቆች በልባቸው ያላመኑበትን በአንደበታቸው እሳቸው የአላህ መልክተኛ መሆናቸውን ሲመሰክሩ፡ ጌታ አላህ ደግሞ፡- ሙናፊቆች ምስክርነታቸው በልባቸው የሌለና ያላመኑበት ነገር በመሆኑ ውሸታም ናቸው፡፡ አንተ መልክተኛዬ እንደሆንክ እኔ አውቃለሁ በማለት ለሳቸው የመልክተኛነት ምስክርን ሰጠ፡፡ መስካሪነትም በአላህ በቃ!!!

” تِلْكَ آيَاتُ اللَّهِ نَتْلُوهَا عَلَيْكَ بِالْحَقِّ وَإِنَّكَ لَمِنَ الْمُرْسَلِينَ ” سورة البقرة 252
“እነዚህ (አንቀጾች) በውነት በአንተ ላይ የምናነባቸው ሲኾኑ የአላህ አንቀጾች ናቸው፤ አንተም በእርግጥ ከመልክተኞቹ ነህ፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 252)፡፡

በዚህ አንቀጽ መሰረትም፡- ጌታ አላህ ለነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከሙሳ በኃላ ስላሉት ህዝቦች፡ በተለይ ስለ ነቢዩ ሳሙዔል (ዐለይሂ-ሰላም)፣ ንጉሱ ጣሉት (ሳኦል) (ዐለይሂ-ሰላም)፣ ነቢዩ ዳዉድ (ዐለይሂ-ሰላም)፣ እና የካፊሩ ጃሉትን (ጎልያድ) ታሪክ ከነገራቸውና ከዘረዘረ በኋላ፡- ይህ ሁሉ በአንተ ላይ የምናነበው ከሩቅ (ገይብ ከሆኑ) ዜናዎች ነው፡፡ አንተ በወቅቱ ባትኖርም እኔ እተርክልሀለሁ፡ ምክንያቱም አንተ ከመልክተኞቼ አንዱ ነህና! ማለቱን እናገኛለን፡፡ መስካሪነትም በአላህ በቃ!!!

ለ. ቅዱስ ቁርኣን፡-

ቅዱስ ቁርኣን ለነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ነቢይነት ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ ከተሰጣቸው ተአምራት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ አላህ ቁርኣንን በሳቸው ላይ ማውረዱ ብቻ ለነቢይነታቸው በቂ ማስረጃ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ቃሉም እንዲህ ይላል፡-
” أَوَلَمْ يَكْفِهِمْ أَنَّا أَنْزَلْنَا عَلَيْكَ الْكِتَابَ يُتْلَى عَلَيْهِمْ إِنَّ فِي ذَلِكَ لَرَحْمَةً وَذِكْرَى لِقَوْمٍ يُؤْمِنُونَ ” سورة العنكبوت 51
“እኛ መጽሐፉን በነሱ ላይ የሚነበብ ሆኖ ባንተ ላይ ማውረዳችን አይበቃቸውምን? በዚህ ውስጥ ለሚያምኑ ሕዝቦች ችሮታና ግሣጼ አለበት።” (ሱረቱል ዐንከቡት 51)፡፡

የቅዱስ ቁርኣን ተአምራዊነት፡ ከቀደምት ነቢያት ተአምራት በሁለት መልኩ ይለያል፡-
– ‹‹መዕነዊይ›› መሆኑ፡- የቀደምት ነቢያት ተአምራት ‹‹ሒስሲይ›› ይባላል፡፡
‹‹ሒስሲይ›› ማለት፡- በአይን የሚታይ፣ በእጅ የሚዳሰስ ማለት ነው፡፡ በሙሳ በኩል፡- በትር ወደ እባብ ሲቀየር፣ ባህሩ ደርቆ መሻገሪያ መንገድ ሲሆን፣ እጅ መልኩ ተቀይሮ የሚያበራ ነጭ ሲሆን የሚታይና የሚዳሰስ ይባላል፡፡ በዒሳ በኩል፡- የሞቱት ሲነሱ፣ የዕውሮች አይን ሲበራ፣ ለምጽ የነበረባቸው ሲሽሩ የሚታይና የሚዳሰስ ተአምር ይባላል፡፡ ለነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ነቢይነት እንደ ማስረጃ የተሰጣቸው ቁርኣን ግን ‹‹መዕነዊይ›› ነው፡፡

‹‹መዕነዊይ›› ማለት፡- ህሊናን የሚያናግር፡ አእምሮን የሚቆጣጠርና ልብን የሚገዛ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ቀርኣን ሲቀራ በመስማት ብቻ የሰውን ልብ ይገዛል፡፡ በሚያስተላልፋቸው መልእክቱ፡ ሰዎችን ለለውጥ ይዳርጋል፡፡

– ‹‹አበዲይ›› መሆኑ፡- የቀደምት ነቢያት ተአምር ከነቢይነት ዘመናቸው ጋር ብቻ የተቆራኘ ነው፡፡ ከነሱ ሞት በኋላ ያበቃል፡፡ ሙሳ ከሞተ በኋላ በትር ወደ እባብ አይቀየርም፡ ባህር ደርቆ መንገድ አይሆንም፡፡ ዒሳ አላህ ወደ ራሱ ከወሰደው በኋላ፡ የሞተ አልተነሳም፡ የእውር አይን አልበራም፡፡ ቅዱስ ቁርኣን ግን ከነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ሞት በኋላ እንኳ ተአምራዊነቱ አላከተመም፡፡ እስከ ቂያማ ድረስ ድሮ በነበረው ተአምራዊነቱ ይቀጥላል፡፡ ስለዚህም ‹‹አበዲይ›› (ዘውታሪ) ይሰኛል፡፡ ከቅዱስ ቁርኣን ተአምራቶች መካከል የተወሰኑትን እንመልከት፡-

1. አምሳያው ፈጽሞ አለመገኘቱ፡-

በቅዱስ ቁርኣን አምላካዊ ቃልነት ላይ ጥርጣሬ ያደረባቸው ሰዎች ካሉ፡ ጌታ አላህ አንድ ማጣሪያ ሰጣቸው፡፡ እሱም፡- ይህ ቁርኣን የሰው ድርሰት ነው፡ ብላችሁ ከተጠራጠራችሁ፡ እናንተም ሰው ናችሁና ያ ሰው የተጠቀመውን መንገድ በመጠቀም ቁርኣንን የሚመስል ነገር ጽፋችሁ አምጡ!! አላቸው፡፡ ቅዱስ ቁርኣን በአነጋገሩ ጠቅላላነት፡ በአረፍተ ነገሮቹ አሰካክ፡ ስድም ቅኔም ሳይሆን ለየአንቀጾቹ ዜማዊ ማሳረፊያዎች ያሉት፡ ትርጉሙን የተረዳውንም ሆነ ያልተረዳውን ሰው ቀልብ የሚገዛ በመሆኑ፡ እርሱን የሚመስል አነጋገርና አጻጻፍ ማን ማምጣት ይችላል? እያለ ነው፡፡ ቅዱስ ቁርኣን አምሳያዬን አምጡ ብሎ ሰዎችን በቀጣዮቹ መንገድ ተፎካክሯል፡-

1. ሙሉውን ቁርኣን ማምጣት፡-

“أَمْ يَقُولُونَ تَقَوَّلَهُ بَلْ لَا يُؤْمِنُونَ * فَلْيَأْتُوا بِحَدِيثٍ مِثْلِهِ إِنْ كَانُوا صَادِقِينَ ” سورة الطور 34-33
“ወይም ቀጠፈው ይላሉን? አይደለም በውነቱ አያምኑም፡፡ እውነተኞችም ቢሆኑ መሰሉ የሆነን ንግግር ያምጡ” (ሱረቱ-ጡር 33-34)፡፡
2. ሙሉውን ካልቻሉ 10 ሱራ ብቻ
“أَمْ يَقُولُونَ افْتَرَاهُ قُلْ فَأْتُوا بِعَشْرِ سُوَرٍ مِثْلِهِ مُفْتَرَيَاتٍ وَادْعُوا مَنِ اسْتَطَعْتُمْ مِنْ دُونِ اللَّهِ إِنْ كُنْتُمْ صَادِقِينَ ” سورة هود 13

“ይልቁንም (ቁርአንን) ቀጣጠፈው ይላሉን?፡- እውነተኞች እንደሆናችሁ ብጤው የሆኑን አስር የተቀጣጠፉ ሱራዎች አምጡ ከአላህም ሌላ የቻላችሁትን (ረዳት) ጥሩ በላቸው፡፡” (ሱረቱ ሁድ 13)፡፡
3. 10ሩን ካልቻሉ ደግሞ አንዲትን ሱራ ብቻ
“أَمْ يَقُولُونَ افْتَرَاهُ قُلْ فَأْتُوا بِسُورَةٍ مِثْلِهِ وَادْعُوا مَنِ اسْتَطَعْتُمْ مِنْ دُونِ اللَّهِ إِنْ كُنْتُمْ صَادِقِينَ ” سورة يونس 38
“በውነትም (ሙሐመድ) ቀጣጠፈው ይላሉን? ይህ ከሆነ መሰሉን (አንዲት) ሱራ አምጡ ከአላህም ሌላ የቻላችሁትን ሁሉ (ረዳት) ጥሩ እውነተኞች እንደሆናችሁም (ተጋግዛችሁ አምጡ) በላቸው፡፡” (ሱረቱ ዩኑስ 38)፡፡
“وَإِنْ كُنْتُمْ فِي رَيْبٍ مِمَّا نَزَّلْنَا عَلَى عَبْدِنَا فَأْتُوا بِسُورَةٍ مِنْ مِثْلِهِ وَادْعُوا شُهَدَاءَكُمْ مِنْ دُونِ اللَّهِ إِنْ كُنْتُمْ صَادِقِينَ * فَإِنْ لَمْ تَفْعَلُوا وَلَنْ تَفْعَلُوا فَاتَّقُوا النَّارَ الَّتِي وَقُودُهَا النَّاسُ وَالْحِجَارَةُ أُعِدَّتْ لِلْكَافِرِينَ ” سورة البقرة 24-23
“በባሪያችንም ላይ ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትሆኑ ከቢጤው አንዲትን ምዕራፍ አምጡ እውነተኞችም እንደሆናችሁም ከአላህ ሌላ መስካሪዎቻችሁን ጥሩ፡፡ (ይህንን) ባትሠሩ ፈጽሞም አትሠሩትምና ያችን መቀጣጠያዋ ሰዎችና ደንጊያዎች የሆነችውን እሳት ተጠበቁ ለከሓዲዎች ተደግሳለችና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 23-24)፡፡
በመጨረሻም ሰዎችም ጋኔኖችም በጋራ ቢሰባሰቡ፡ ቁርኣንን የሚመስል ለማምጣት ቢጥሩ፡ ፈጽሞ እንደማይሳካላቸው በመግለጽ ቁርጡን ነገራቸው፡-
“قُلْ لَئِنِ اجْتَمَعَتِ الْإِنْسُ وَالْجِنُّ عَلَى أَنْ يَأْتُوا بِمِثْلِ هَذَا الْقُرْآنِ لَا يَأْتُونَ بِمِثْلِهِ وَلَوْ كَانَ بَعْضُهُمْ لِبَعْضٍ ظَهِيرًا ” سورة الإسراء 88
“ሰዎችም ጋኔኖችም የዚህን ቁርአን ቢጤ በማምጣት ላይ ቢሰበሰቡ ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳት ቢሆንም እንኳ ብጤውን አያመጡም በላቸው፡፡” (ሱረቱል ኢስራዕ 88)፡፡

2. እርስ በርሱ ባለመጋጨቱ፡-

ሌላው ቅዱስ ቁርኣን ከአላህ ዘንድ የመጣ የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ተአምር መሆኑን የሚያመላክተው፡ በውስጡ የሰፈሩ ሀሳቦችና ቃላቶች ምንም አይነት መፋለስ፡ እርስ በርስ መጋጨት የማይታይባቸው መሆኑ ነው፡፡ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-
“أَفَلَا يَتَدَبَّرُونَ الْقُرْآنَ وَلَوْ كَانَ مِنْ عِنْدِ غَيْرِ اللَّهِ لَوَجَدُوا فِيهِ اخْتِلَافًا كَثِيرًا ” سورة النساء 82
“ቁርአንን አያስተነትኑምን? ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙን መለያየት ባገኙ ነበር፡፡” (ሱረቱ-ኒሳእ 82)፡፡
“الْحَمْدُ لِلَّهِ الَّذِي أَنْزَلَ عَلَى عَبْدِهِ الْكِتَابَ وَلَمْ يَجْعَلْ لَهُ عِوَجًا ” سزرة الكهف 1
“ምስጋና ለአላህ ለዚያ መጽሐፉን በውስጡ መጣመምን ያላደረገበት ሲሆን በባሪያው ላይ ላወረደው ይገባው፡፡” (ሱረቱል ከህፍ1)፡፡

3. አምላካዊ ጥበቃው፡-

ይህ ደግሞ ሌላው ማስረጃ ነው፡፡ ከወረደበት ማግስት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በመጀመሪያው ቅርጽና ይዘቱ ተጠብቆ የቆየ ብቸኛው መለኮታዊ መጽሐፍ ቅዱስ ቁርኣን ነው፡፡ አንድም ፊደል ሳይጨመርበትና ሳይቀነስበት ዛሬም ድረስ አለ፡፡ ቅዱስ ቁርኣን በመጽሐፍ መልክ ብቻ ሳይሆን ተጠብቆ የቆየው፡ በአማኞች ልቦና ውስጥም በቃል የተያዘ ሆኖም ጭምር ነው፡፡
“إِنَّا نَحْنُ نَزَّلْنَا الذِّكْرَ وَإِنَّا لَهُ لَحَافِظُونَ ” سورة الحجر 9
“እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፡፡ እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን፡፡” (ሱረቱል ሒጅር 9)፡፡
“إِنَّ الَّذِينَ كَفَرُوا بِالذِّكْرِ لَمَّا جَاءَهُمْ وَإِنَّهُ لَكِتَابٌ عَزِيزٌ * لَا يَأْتِيهِ الْبَاطِلُ مِنْ بَيْنِ يَدَيْهِ وَلَا مِنْ خَلْفِهِ تَنْزِيلٌ مِنْ حَكِيمٍ حَمِيدٍ ” سورة فصلت 42-41
“እነዚያ በቁርአን፣ እርሱ አሸናፊ መጽሐፍ ሲሆን፣ በመጣላቸው ጊዜ የካዱት (ጠፊዎች ናቸው)። ከኋላውም ከፊቱም ውሸት አይመጣበትም፤ ጥበበኛ ምስጉን ከሆነውጌታ የተወረደ ነው።“ (ሱረቱ ፉሲለት 41-42)፡፡

4. በንባብም ሆነ በመስማት ብዛት የማይሰለች መሆኑ፡-

እጅግም የሚደንቅ ተአምር ነው፡፡ እኛ በጣም የምንወዳቸው ዳዒዎችና ዐሊሞች በአንድ ርእሰ-ጉዳይ ዳዕዋ ሲሰጡ፡ ምናልባትም ያንን ዳዕዋ እስከ ሶስት አራት ጊዜ ደጋግመን ልንሰማው እንችል ይሆናል፡፡ ከዛ በኋላ ግን ይሰለቻል፡፡ ሌላ አዲስ የዳዕዋ ስራ እንፈልጋለን፡፡ የማንም ሰው ንግግር ሲደጋገም ይሰለቻልና፡፡ ሙስሊሞች ሱረቱል ፋቲሓን በቀን ስንቴ ነው ሚደጋግሙት? አጫጭር ሱራዎችን ስንቴ ነው የሚቀሩት? የቁርኣን ሒፍዝ ማእከሎች ተማሪዎችን በመቀበል፡ ተማሪዎች ቁርኣንን በቃል ለመሐፈዝ ብቻ በየቀኑ አንዱን ሱራ ስንቴ ነው የሚቀሩት? እንደዛም ሆኖ ግን የመዳከም እንጂ የመሰላቸት ስሜት አይታይባቸውም፡፡ ይህ ብቻ የአላህ ቃል ለመሆኑ በቂ አይሆንምን?

Shortlink http://q.gs/Ewlv7