“ሙሐመዱን ረሱሉሏህ” 3

ሼር ያድርጉ
430 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

1. ስለ ነቢይነታቸው የተነገረ ትንቢት፡-

ከትላንት በስቲያ ስለ ረሱላችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነቢይ ሆኖ መነሳት የተነገረ ትንቢት በሚለው ስር፡ ሁለተኛውን ነጥብ፡ ቀደምት መለኮታዊ መጽሀፍት ስለ እሳቸው ነቢይነት መናገራቸውን ተመልክተናል፡፡ ዛሬም የጌታችን አላህ ፈቃድ ከሆነ ሶሥተኛውን ክፍል፡ ማለትም የመጽሀፉ ባለቤቶች የሆኑት (የአይሁድና የክርስቲያን) ሊቃውንት የሳቸውን ነቢይነት በሚገባ ያውቁ እንደነበር እንመለከታለን ኢንሻአላህ፡-

ሐ. በመጽሀፍቱ ሊቃውንት ዘንድ፡-

የነቢዩ ሙሐመድ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ነቢይነት፡ በቀደምት ነቢያት አንደበትና በመለኮታዊ መጽሐፍት ውስጥ ብቻም የሰፈረ አይደለም፡፡ በተጨማሪም በሃይማኖቱ ሊቃውንት ዘንድ የታወቀ ጉዳይ ነው እንጂ፡፡ የአይሁድና የክርስቲያን ሊቃውንቶች የሳቸውን ነቢይነት በሚገባ ያውቁ ነበር፡፡ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-

“الَّذِينَ آتَيْنَاهُمُ الْكِتَابَ يَعْرِفُونَهُ كَمَا يَعْرِفُونَ أَبْنَاءَهُمْ… ” سورة البقرة 146
“እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ወንዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (ሙሐመድን) ያውቁታል…” (ሱረቱል በቀራህ 146)፡፡

“الَّذِينَ آتَيْنَاهُمُ الْكِتَابَ يَعْرِفُونَهُ كَمَا يَعْرِفُونَ أَبْنَاءَهُمْ… ” سورة الأنعام 20
“እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ወንዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (ሙሐመድን) ያውቁታል…” (ሱረቱል አንዓም 20)፡፡

በነዚህ ሁለት ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾች መሰረት የመጽሀፉ ሊቃውንቶች የነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነቢይነት፡ የገዛ ልጃቸውን የሚያውቁትን ያህል፡ እሳቸውንም እንደሚያውቁ መረዳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በመጽሀፉ ውስጥ ስለ እሳቸው የተነገረውን ያውቃሉና፡፡
በነቢያችን(ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) የነቢይነት ዘመን ኢስላምን ከተቀበሉት ስመ ጥር የአይሁድ ሊቃውንቶች አንዱ የነበረው፡ ዐብዱላህ ኢብኑ ሰላም (ረዲየላሁ ዐንሁ) ይህን አንቀጽ በተመለከተ በዑመር (ረዲየላሁ ዐንሁ) ጥያቄ ቀርቦለት ተከታዩን ምላሽ መስጠቱን ኢብኑ ከሢር በተፍሲር ኪታባቸው ላይ እንዲህ ይገልጹታል፡-

قال القرطبي: ويروى أن عمر قال لعبد الله بن سلام: أتعرف محمدًا صلى الله عليه وسلم كما تعرف ولدك ابنك، قال: نعم وأكثر، نزل الأمين من السماء على الأمين، في الأرض بنعته فعرفته، وإني لا أدري ما كان من أمره. تفسير ابن كثير. سورة البقرة 146
ኢማሙል ቁርጡቢይ (የተፍሲር ሊቅ ናቸው) ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- ዑመር ለዐብደላህ ኢብኑ ሰላም፡- ወንድ ልጅህን የምታውቀውን ያህል መሐመድን ታውቀው ነበርን? ዐብዱላህ ኢብኑ ሰላምም፡- አዎን! እንደውም የበለጠ እንጂ! የሰማዩ ታማኝ (መልአኩ ጅብሪል) በምድር ያለው ታማኝ (ነቢዩ ሙሐመድ ዘንድ) ወሕይን ይዞ ወረደ፡ እኔም በምልክቱ አወቅሁት፡፡ (የልጄ ጉዳይ ግን) ከእኔ ቤት ለቆ መውጣት በኋላ (ሌላ ወንድ ወደ ሚስቴ በመግባት) ሊሆን የሚችለውን ነገር አላውቅም ብሎ መለሰ፡፡ (ተፍሲር ኢብኑ ከሢር፡ ሱረቱል በቀራህ 146)፡፡

ዐብዱላህ ኢብኑ ሰላም (ረዲየላሁ ዐንሁ) እኔ በሌለሁበት ሌላ ወንድ ቤቴ ገብቶ ልጁ የተወለደው ከሌላ ቢሆንስ? እያለ ነው፡፡ ይህ ልጅ ያንተ ነው፣ ካንተው ነው የወለድኩት ያለችኝ ሚስቴ ነች፡፡ የሳቸው ነቢይነት ግን በመጽሀፋችን ውስጥ ምልክቱ ተነግሮ ስለነበር ሳልጠራጠር አውቃቸዋለሁ አለ፡፡
እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ እሱም፡- ታዲያ የሳቸው ነቢይነት ሊቃውንቶቹ ዘንድ ይህን ያህል ግልጽ ከነበረ፡ ለምን ሌሎቹስ አልሰለሙም? የሚል፡፡
ምላሹንም፡- እዛው አንቀጽ ላይ እናገኘዋለን፡፡ አንቀጹ ሙሉው ሲነበብ ሚስጥሩ ይገለጻል፡፡ እንዲህ ይላል ቅዱስ ቁርኣን፡-

“الَّذِينَ آتَيْنَاهُمُ الْكِتَابَ يَعْرِفُونَهُ كَمَا يَعْرِفُونَ أَبْنَاءَهُمْ وَإِنَّ فَرِيقًا مِنْهُمْ لَيَكْتُمُونَ الْحَقَّ وَهُمْ يَعْلَمُونَ ” سورة البقرة 146
“እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ወንዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (ሙሐመድን) ያውቁታል፡፡ ከነሱም የተለዩ ክፍሎች እነርሱ የሚያወቁ ሲኾኑ እውነቱን በእርግጥ ይደብቃሉ፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 146)፡፡

“الَّذِينَ آتَيْنَاهُمُ الْكِتَابَ يَعْرِفُونَهُ كَمَا يَعْرِفُونَ أَبْنَاءَهُمْ الَّذِينَ خَسِرُوا أَنْفُسَهُمْ فَهُمْ لَا يُؤْمِنُونَ ” سورة الأنعام 20
“እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ወንዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (ሙሐመድን) ያውቁታል፡፡ እነዚያ ከእነርሱ ውስጥ ነፍሶቻቸውን ያከሰሩት እነርሱ አያምኑም፡፡ ” (ሱረቱል አንዓም 20)፡፡

በመጀመሪያው አንቀጽ ላይ ያለው የሚገልጸው፡- እውነታውን እያወቁ ለማመን ያልፈለጉ ቡድኖች ይህን እውነት ሰው ሰምቶ እንዳይቀበል የመደበቅ ስራ እንደሚሰሩ ነው፡፡ መደበቅ ሲባል፡- አንድም በመጽሀፉ ላይ እጃቸውን በመክተት የተነገረውን ቃል በማጥፋትና በመሰረዝ በምትኩ ሌላ መጨመር፡ ወይንም ያንን እውነት ለሰዎች ይፋ ሳያደርጉ የተጣመመ ትርጉም መስጠት ነው፡፡ ሁለቱንም መንገዶች በመጽሐፉ ላይ ተጠቅመውበታል፡፡
ሁለተኛው አንቀጽ ደግሞ፡- በነበረባቸው የዐረብ ጥላቻና ምቀኝነት ሳቢያ፡ ነቢይ ከነሱ መነሳቱን በመጥላት ላለማመን ወስነው፡ እራሳቸውን ለክስረት የዳረጉ መሆናቸውን ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ፡- ነቢዩ ሙሐመድ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ነቢይ ሆነው ከመነሳታቸው በፊት፡ የሳቸው የነቢይነት ዘመን ቶሎ ተቃርቦ አላህም በነቢይነት እንዲልካቸው ይማጸኑ የነበሩት እነሱው አይሁዶች መሆናቸው ነው፡፡

ከዐረቦች ጋር በሚገጥሙት ጦርነት እንዲህ ይሏቸው ነበር፡- በመጽሐፋችን ላይ በመጨረሻው ዘመን ይመጣል የተባለ ነቢይ አለና፡ እሱ ሲመጣ ከሱ ጋር በመሆን እናንተን ከምድር ገጽ እናጠፋችኋለን! ‹‹አምላካችን አላህ ሆይ! መጨረሻው ዘመን በሚመጣው መልክተኛ ተማጽነንሀልና፡ እባክህ የዚህን መልክተኛ መምጣት አቃርብልንና ከሱ ኋላ በመሆን እነዚህን ዐረብ ሙሽሪኮችን እናጥፋቸው›› ይሉ ነበር፡፡ ጊዜው ደረሰና የአላህ መልክተኛም ነቢይ ሆነው ሲላኩ፡ አይሁዶቹ ከንግግራቸው 180 ዲግሪ ዞሩና፡- እኛ እኮ የምንፈልገው ከራሳችን ዘር ከአይሁድ የሆነ ነቢይ ነው እንጂ፡ ከጠላታችን ከዐረብ እንዴት ይነሳል! በማለት በማመን ፈንታ ካዱ አስተባበሉ፡፡

ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-

“وَلَمَّا جَاءَهُمْ كِتَابٌ مِنْ عِنْدِ اللَّهِ مُصَدِّقٌ لِمَا مَعَهُمْ وَكَانُوا مِنْ قَبْلُ يَسْتَفْتِحُونَ عَلَى الَّذِينَ كَفَرُوا فَلَمَّا جَاءَهُمْ مَا عَرَفُوا كَفَرُوا بِهِ فَلَعْنَةُ اللَّهِ عَلَى الْكَافِرِينَ “سورة البقرة 89
“ከነሱም ጋር ያለውን (መጽሐፍ) አረጋጋጭ የኾነ መጽሐፍ ከአላህ ዘንድ በመጣላቸው ጊዜ (ከመምጣቱ) በፊት በነዚያ በካዱት ላይ ይረዱበት የነበሩ ሲኾኑ ያወቁት ነገር በመጣላቸው ጊዜ በርሱ ካዱ፡፡ የአላህም ርግማን በከሓዲዎች ላይ ይኹን፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 89)፡፡

“ይረዱበት የነበሩ ሲኾኑ ” የሚለው ትርጉም የሚያመላክተው፡- አይሁዶቹ አላህን እንደሚማጸኑ፡ የመጨረሻውን መልክተኛ ቶሎ እንዲያመጣላቸው የሚጠይቁ እንደነበሩ ነው፡፡

“وَيَقُولُ الَّذِينَ كَفَرُوا لَسْتَ مُرْسَلًا قُلْ كَفَى بِاللَّهِ شَهِيدًا بَيْنِي وَبَيْنَكُمْ وَمَنْ عِنْدَهُ عِلْمُ الْكِتَابِ ” سورة الرعد 43
“እነዚያም የካዱት ሰዎች፥ መልክተኛ አይደለህም ይላሉ፤ በኔና በናንተ መካከል መስካሪ በአላህና እርሱ ዘንድ የመጽሐፉ ዕውቀት ባለው ሰው በቃ፥ በላቸው።” (ሱረቱ-ረዕድ 43)፡፡

በዚህም አንቀጽ በግልጽ የምናየው፡- ምንም ሰዎች የሳቸውን ነቢይነት ቢክዱም፡ በከሀዲዎችና በሳቸው ነቢይ መሆን ጉዳይ ላይ የአላህ ምስክርነት ብቻውን በቂ ነው ብሎ መመስከሩንና፡ እንዲሁም የመጽሀፉ ዕውቀት ያለው ሰው የሚሰጠው ምስክርነት በቃ! ማለቱን ነው፡፡ የመጽሀፉ ሊቃውንቶች የሳቸውን ነቢይነት በሚገባ ያውቁ እንደነበር ይህም ሌላ ማስረጃ ነው፡፡ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ነቢይነታቸውን በተመለከተ የተነገረ ትንቢት፡ በሚለው ስር፡- ከነቢያት፣ ከመጽሐፍቱና ከሊቃውንቱ አንደበት የተመለከትናቸው መረጃዎቻችንን በዚሁ እናበቃና በቀጣዩ ደግሞ ሌላ ነጥብ ላይ እናተኩራለን ኢንሻአላህ፡፡

Shortlink http://q.gs/EwnWv