“ሙሐመዱን ረሱሉሏህ” 1

ሼር ያድርጉ
491 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
የተከበራችሁ ሙስሊም ወንድሞቼና እህቶቼ! ባለፈው ፕሮግራማችን ላይ በአላህ ፈቃድ በ 29 ክፍል በተከታታይ ስለ “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ስንማር ቆይተን ነበር አልሐምዱ ሊላህ፡፡ አሁን ደግሞ የዛው ክፍል አካል የሆነውን ሁለተኛውን ምስክርነት “ሙሐመዱን ረሱሉሏህ” እንጀምራለን ኢንሻአላህ፡፡

1. ስለ ነቢይነታቸው የተነገረ ትንቢት፡-

ይህ ዋናው ጥያቄ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከተቃራኒ እምነት ተከታዮች የምንሰማው ጥያቄ፡፡ እውነት የእናንተ ነቢይ እውነተኛ ነቢይ ከሆኑ ስለሳቸው ነቢይነት ቀደምት ነቢያቶችና መለኮታዊ መጽሐፍቶች ለምን ትንቢትን አልተናገሩላቸውም? የመጽሐፉ ሊቃውንቶችስ ለምን አልተናገሩም? የሚል፡፡
ታዲያ እኛ ሙስሊሞች ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ አለን? ቅዱስ ቁርኣንስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላል? ሙስሊሞች እንደሚያምኑትና ቅዱስ ቁርኣን እንደሚያስተምረው ስለ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ነቢይነት ትንቢትን ያልተናገረ አንድም ነቢይ የለም፡፡ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በአጋጣሚዎች ክስተት፡ በሁኔታዎች መመቻቸት ነቢይ ነኝ ብለው የተነሱ ሰው አይደሉም፡፡ ገና ነቢይ ከመሆናቸውና ከመፈጠራቸው በፊት አስቀድሞ በነቢያት አንደበት ሁሉ ትንቢት የተነገረላቸው፡ ከቅዱስ ቁርኣን በፊት የነበሩ ቀደምት መለኮታዊ መጽሀፍት የተነበዩላቸው፡ የመጽሀፍቶቹ ሊቃውንት የነበሩትም በሚገባ የሚያውቋቸው የነበሩ ነቢይ ናቸው፡፡ ዝርዝሩንም እነሆ፡-

ሀ. በነቢያት በኩል፡-

አላህ የላካቸው 124.000 የሚጠጉ ነቢያት በጠቅላላ ስለሳቸው ነቢይነት ተናግረዋል፡፡ ከጀመሪያው ሰው ከአደም አንስቶ እስከ መጨረሻው የእስራኤል መልክተኛ እስከሆነው እስከ ዒሳ ድረስ ያሉት ነቢያቶች ሁሉ (ዐለይሂሙ-ሰላም) ሲናገሩ የነበሩት ስለ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ነው፡፡ የሳቸውን ነቢይነት ሳይናገሩ፡ ለህዝቦቻቸውም ፡- በህይወት ከደረሳችሁባቸው አደራ ተከተሏቸው! ሳይሉና ሳያስጠነቅቁ የነቢይነት ማዕረግ የተሰጣቸው ነቢያት የሉም፡፡ ለዚህ እምነታችንም ቀጣዩን የቅዱስ ቁርኣን አንቀጽ እንደማስረጃ እናቀርባለን፡-

“وَإِذْ أَخَذَ اللَّهُ مِيثَاقَ النَّبِيِّينَ لَمَا آتَيْتُكُمْ مِنْ كِتَابٍ وَحِكْمَةٍ ثُمَّ جَاءَكُمْ رَسُولٌ مُصَدِّقٌ لِمَا مَعَكُمْ لَتُؤْمِنُنَّ بِهِ وَلَتَنْصُرُنَّهُ قَالَ أَأَقْرَرْتُمْ وَأَخَذْتُمْ عَلَى ذَلِكُمْ إِصْرِي قَالُوا أَقْرَرْنَا قَالَ فَاشْهَدُوا وَأَنَا مَعَكُمْ مِنَ الشَّاهِدِينَ ” سورة آل عمران 81
“አላህ የነቢያትን ቃል ኪዳን፣ ከመጽሐፍና ከጥበብ ሰጥቻችሁ ከዚያም ከእናንተ ጋር ላለዉ (መጽሐፍ) የሚያረጋግጥ መልክተኛ ቢመጣላቸዉ፣ በርሱ በእርግጥ እንደምታምኑበት በእርግጥም እንድትረዱት ሲል በያዘ ጊዜ (አስታዉስ)፤ አረጋገጣችሁን? በይሃችሁ ላይ ኪዳኔን ያዛችሁምን? አላቸዉ፤ አረጋገጥን አሉ እንግዲያስ መስክሩ፤ እኔም ከእናንተ ጋር ከመስካሪዎቹ ነኝ አላቸዉ።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 81)፡፡

ይህ ጥቅስ በግልጽ እንደሚያስረዳው አላህ የላካቸውን ነቢያቶች በጠቅላላ መጽሐፍና ጥበብ እንደሰጣቸው ከገለፀ በኋላ አንድ በመሐላ የጠበቀ ቃል ኪዳን አስገብቶዋቸዋል፡፡ እሱም፡- ወደፊት አንድ መልክተኛ ይመጣል:: እሱም እናንተ ዘንድ ያለውን መጽሀፍ አረጋጋጭ (እውነት መሆኑን መስካሪ) ነው፡፡ ታዲያ ይህ መልክተኛ በሚመጣበት ጊዜ እናንተ በህይወት ሆናችሁ ብታገኙት በዚህ መልክተኛ አምናችሁ ከኋላው ተከትላችሁ ትረዱታላችሁ? በማለት፡፡

እነሱም፡- አዎ ጌታችን ሆይ! በቃል ኪዳኑ ገብተናል አረጋግጠንማል በማለት መለሱ፡፡ ዋናው የሚነሳው ጥያቄ፡- ይህ ይመጣል የተባለው መልክተኛ ማን ነው? የሚለው ነው፡፡ ለዚህም ጥያቄ ምንም ሳንጠራጠር የምንመልሰው መልስ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ናቸው የሚል ነው፡፡ ማረጋገጫችንም ቀጣዩ አሠር (ከሶሐቦች የተገኘ ንግግርና ተግባር) ነው፡-

عن علي قال: “لم يبعث الله له نبيا آدم فمن بعده إلا أخذ عليه العهد في محمد صلى الله عليه وسلم، لئن بعث وهو حي ليؤمنن به ولينصرنه ويأمره فيأخذ العهد على قومه ثم تلا: {وَإِذْ أَخَذَ اللَّهُ مِيثَاقَ النَّبِيِّينَ لَمَا آتَيْتُكُمْ مِنْ كِتَابٍ وَحِكْمَةٍ} الآية، كنز العمال في سنن الأقوال والأفعال 4296
ዐሊይ ኢብኑ አቡ-ጧሊብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላሉ፡- “አላህ አደምንም ሆነ ከሱ በኋላ ያሉትን ነቢያትን በሙሐመድ (ዐለይሂ ሶላቱ ወሰላም) ላይ ቃል ቢያስገባቸው እንጂ እንዲሁ አልላካቸውም፡፡ እሱም፡- እሳቸው ነቢይ ሆነው ሲላኩ ያ የቀደመው ነቢይ በህይወት ቢያገኛቸው ሊያምንባቸውና ከኋላቸው ሆኖ ሊረዳቸው፡ እንዲሁም ህዝቦቹን፡ እሳቸው ላይ በህይወት ከደረሱባቸው አምነው እንዲከተሏቸው እንዲያዛቸው ነው፡፡ ከዛም ዐሊይ ለማረጋገጫነት የቁርኣኑን አንቀጽ አነበቡ” (ከንዙል-ዑምማል ፊ-ሱነኒል አቅዋል 4296)፡፡

አንዳንድ ነቢያትን በስም ጠቅሰን ስለ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) የተናገሩትንም እንመልከት ከተባለ፡ ሶስት ነቢያትን እንመልከት፡-
-ኢብራሂምና ልጁ ኢስማዒል (ዐለይሂማ-ሰላም)፡-

“رَبَّنَا وَابْعَثْ فِيهِمْ رَسُولًا مِنْهُمْ يَتْلُو عَلَيْهِمْ آيَاتِكَ وَيُعَلِّمُهُمُ الْكِتَابَ وَالْحِكْمَةَ وَيُزَكِّيهِمْ إِنَّكَ أَنْتَ الْعَزِيزُ الْحَكِيمُ ” سورة البقرة 129
“ጌታችን ሆይ! በውስጣቸውም ከነሱው የኾነን መልክተኛ በነርሱ ላይ አንቀጾችህን የሚያነብላቸውን መጽሐፍንና ጥበብንም የሚያስተምራቸውን (ከክህደት) የሚያጠራቸውንም ላክ፤ አንተ አሸናፊው ጥበበኛው አንተ ብቻ ነህና» (የሚሉም ሲኾኑ)፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 129)፡፡

ከዚህ የቁርኣን ጥቅስ የምንረዳው ኢብራሂምና ልጁ ኢስማዒል (ሰላም በሁለቱም ላይ ይሁን) የአላህን ቤት ካዕባን ከገነቡ በኋላ ወደ ጌታቸው ዱዓእ አድርገዋል፡፡ ከነሱ ጎሳ የሆነ አንድ መልክተኛ እንዲያስነሳላቸው የጸለዩት ነው፡፡ ያም መልክተኛ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ሆኑና የኢብራሂምና የልጁም ዱዓእ ተቀባይነትን አገኘ፡፡

عَنِ الْعِرْبَاضِ بْنِ سَارِيَةَ الْفَزَارِيِّ، قَالَ: سَمِعْتُ رَسُولَ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ يَقُولُ: ” إِنِّي عِنْدَ اللَّهِ مَكْتُوبٌ بِخَاتَمِ النَّبِيِّينَ، وَإِنَّ آدَمَ لَمُنْجَدِلٌ فِي طِينَتِهِ، وَسَأُخْبِرُكُمْ بِأَوَّلِ ذَلِكَ: دَعْوَةُ أَبِي إِبْرَاهِيمَ، وَبِشَارَةُ عِيسَى، وَرُؤْيَا أُمِّيَ الَّتِي رَأَتْ…”صحيح ابن حبان 6404
ዒርባድ ኢብኑ ሳሪያህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባስተላለፈው ሐዲሥ ውስጥ ነብያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) እንዲህ አሉ፡- “እኔ አላህ ዘንድ የነቢያት መደምደሚያ ሆኜ ተጽፌአለሁ፡፡ አደም ጭቃ ሁኖ ሳለ እንኳ (ነብይነቴ ተወስኖ ነበር) ስለዚህ ጉዳይ እነግራችኋለሁ፡፡ እኔ የኢብራሂም ልመና፡ የዒሳ ብስራት፡ የእናቴም ህልም ነበርኩ፡፡” (ሶሒሕ ኢብኑ ሒባን 6404)፡፡

ከላይ የተጠቀሰውን ቁርኣን ነቢዩ ራሳቸው ተርጉመውታል፡፡ ከእሳቸው በላይ ቁርኣንን ለመተርጎም ስልጣን ያለው ማንም የለም፡፡ የዒሳ ብስራት ነኝ ያሉት ደግሞ ተከታዩን የቁርአን አንቀጽ በማመላከት ነበር፡-

” وَإِذْ قَالَ عِيسَى ابْنُ مَرْيَمَ يَا بَنِي إِسْرَائِيلَ إِنِّي رَسُولُ اللَّهِ إِلَيْكُمْ مُصَدِّقًا لِمَا بَيْنَ يَدَيَّ مِنَ التَّوْرَاةِ وَمُبَشِّرًا بِرَسُولٍ يَأْتِي مِنْ بَعْدِي اسْمُهُ أَحْمَدُ فَلَمَّا جَاءَهُمْ بِالْبَيِّنَاتِ قَالُوا هَذَا سِحْرٌ مُبِينٌ ” سورة الصف 6
“የመርየም ልጅ ኢሳ፡- የእስራኤል ልጆች ሆይ እኔ ከተውራት በፊት ያለውን የማረጋግጥና ከእኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በሆነው የማበስር ስሆን ወደ እናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልክተኛ ነኝ ባለ ጊዜ(አስተውስ)…” (ሱረቱ-ሶፍ 6)፡፡

Shortlink http://q.gs/EwnXf