መልክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ያይዋት ሴትና…ከዘይነብ ጋር ያደረጉት???

ሼር ያድርጉ
415 Views

ኢሊያህ ማህሙድ

በኣላህ ስም እጅግ ኣዛኝ እጅግ ሩህሩህ በኾነው እንጀምርና በመቀምቀሚያው ዘመን የመጨረሻ ነብይ ተደርገው በተላኩት ሙሐመድ ላይ የኣላህ ሰላምና እዝነት ይውረድ ብለን ቀጥልን፡፡ ወዳጄ እንደምን ከረሙ? ዛሬ ላወጋዎ የገፈተረኝ ምክንያት ኣንድ ክርስቲያን ግለሰብ ሂጃብ ወንድን ልጅ ከዝሙት ይጠብቃል ካላችኹ ስለምን ነው ነብያችኹ (ሰ.ዐ.ሠ) ሴት ልጅ አይቶ ወዲያው ከዘይነብ ጋር ስጋዊ ተራክቦ የፈጸመው? ሂጃብ የለበሰች ሴት ኣይቶ ስጋዊ ፍላጎት ውስጥ ከገባ፣ የሴቶች ሂጃብ መልበስ ምን ሊረባ? ስጋዊ ፍላጎት የቀሰቀሰው ሙሐመድ (ሰ›ዐ›ወ) ኾኖ እያለ ሴቲቷ በሰይጣን ስለምን ትመሰላለች? የሚል በሙስሊም የተዘገበውን ሐዲስ በመንተራስ ሂጃብን ለማዋደቅ የጻፈውን ጽሑፍ ኣብቤ ነው፡፡

እስኪ ቀጥታ ወደ ሐዲሱ እንዝለቅ፡-
عن أبي الزبير عن جابر أن رسول الله صلى الله عليه وسلم رأى امرأة فأعجبته ، فأتي زينب و هي تمعس منيئة فقضى حاجته ، و قال :
إن المرأة تقبل في صورة شيطان ، و تدبر في صورة شيطان ، فإذا رأى أحدكم امرأة فأعجبته ، فليأت أهله ، فإن ذاك يرد ما في نفسه “
أخرجه مسلم ( 6 / 129 – 130 )

“ አቡ ዙበይር ከጃር ኣንስቶ ባወራው “መልክተኛው ኣዲት የምታምረውን ሴት አየና፣ ቆዳ እያለፋች ወደ ነበረችው ባለቤቱ ዘይነብ ጋር ሄደና ስጋዊ ፍላጎቱን ፈጸመ፡፡ ከዚያም “ ሴት ልጅ በሰይጣን ኣምሳያ ታልፋለች፤ታገድማለችም፡፡ ስለዚህ ካናንተ ውስጥ የምታምረውን ሴት ያየ ወደ ሚስቱ ይሂድና ፍላጎቱን ይፈጽም፡፡ ይህን ማድረጉ በውስጡ የተነሳውን ስጋዊ ፍላጎት ይመልስለታል”
ከሙስሊም ውጪ የተዘገቡት መሰል ሐዲሶች ደካማ በሚባለው የሐዲስ ጎራ የሚመደቡ ሲኾን፣ሙስሊም ይህንን ሐዲስ ሲዘግብ “..ከናንተ ውስጥ የምታምረውን ሴት ያየ..” የሚለውን የሐዲስ ክፍል ለማስተላለፍ ብቻ ነው፡፡ ሼኽ መሐመድ ሳሊህ ሙንጂድ በሚያስተዳድረው islamqa.info በሚል ድረ-ገጽ ላይ እንዲህ እናነባለን፡-
ان الأظهر عدم ثبوت نسبة الحادثة المذكورة إلى النبي صلى الله عليه وسلم, وإخرج الإمام مسلم لها إنما يفيد ثبوت أصل الحديث ولهذا ذكر الوجه الأخر معاها.

ስንገረድፈው፡-
“ በዚህ ዙሪያ የተወሱ ሐዲሶች መልክተኛው እንዳደረጉት ተደርጎ መነገራቸው ስህተት ነው፡፡ ኢማም ሙስሊምም ይህንን ሐዲስ መዘከሩ የሐዲሱ መሰረታዊ ሐሳብን ከማጽናት ኣንጻር ስልኾነ ብቻ ነው፡፡ ለዛም ሲል የሐዲሱን ሌላኛው ክፍል አብሮ ጠቅሷል”
ወዳጄ ልብ ሊሉ የሚገባው ኢማም ሙስሊም ሐዲሶችን ሲዘግብ በኣንድ ሐዲስ ውስጥ የተነሱ ትክክለኛ ጉዳዮች ካሉና በሌሎችም ዘገባዎች የሚጠነካከሩ ከኾነ፣ ምንም እንኳ በሐዲሱ ውስጥ መልክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ያላደረጉት ጉዳይ ቢኖርም ያደረጉትን ለመጠቀም ሲል ሐዲሱን ይዘግበዋል፡፡ ያሳለፍነው ሐዲስ ውስጥ መልክተኛው አዩና..አደረጉ የተባለው በተለያዩ ምክንያቶች ደካማ ዘገባ ሲኾን መጨረሻ ላይ “ካናንተ ውስጥ የምታምረውን ሴት ያየ ወደ ሚስቱ ይሂድና ፍላጎቱን ይፈጽም” የሚለው የሐዲሱ ክፍል ግን በሌሎችም ዘገባዎች የተደገፈ በመኾኑ፣ ይህንን ለማስተላለፍ ሲል ሙሉውን ዘገባ በራሱ መድብል ውስጥ አካቶታል፡፡ ሌላው ከሐዲሱ የምንማረው ኹሉም ሴቶች መልክተኛው ዘመን በዓይነ-ርግብ የሚሸፈኑ እንዳልነበሩ ነው፡፡ እስኪ ደግሞ ወደ ክርስቲያኑ መጽሐፍ ገባ እንበል፡-
[ዳዊት]
…ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር።እንዲህም ሆነ ወደ ማታ ጊዜ ዳዊት ከምንጣፉ ተነሣ፥ በንጉሥም ቤት በሰገነት ላይ ተመላለሰ በሰገነቱ ሳለ አንዲት ሴት ስትታጠብ አየ ሴቲቱም መልከ መልካም ነበረች።…ይህች የኤልያብ ልጅ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን? አለ።…ዳዊትም መልእክተኞች ልኮ አስመጣት ወደ እርሱም ገባች፥ ከርኵሰትዋም ነጽታ ነበርና ከእርስዋ ጋር ተኛ ወደ ቤትዋም ተመለሰች። ሴቲቱም አረገዘች፥ ወደ ዳዊትም፦ አርግዤአለሁ ብላ ላከችበት። ከዚያም “ጠቢቡ” ሰለሞን ተወለደ፡፡ መጽሀፈ ሳሙኤል ካልእ 11 /1-5

ወዳጄ ያስቀደምነው ሐዲስ ውስጥ መልክተኛው አደረጉት የተባለው ትክክል ነው እንኳ ቢባል፣ እዚህ ጋ ዳዊት ካደረገው ጋር በምንም እንደማይነጻጸር ልብ ይሏል፡፡ ዳዊት የሰው ሚስት እርቃኗን ኾና ኣይቶ ወደ ተፈቀዱለት ሚስቶቹ ሳይኾን የሄደው፣እርቃኗን ያለቸውን ሴት ሌሎችም እንዲያይዋት አድርጎና አስጠርቶ …ግልሙትና ሰራ፡፡ ታሪኩን እስከሚቀጥለው ምዕራፍ ድረስ ሄደን ስናነብ፣ ዳዊት የሴትዬዋን ባልም ጭምር አስገድሏል፡፡ ሴቲቱንም ሚስት አድርጎ ወስዷል፡፡ መቀሰፍ የነበረበት ዳዊት ራሱ ኾኖ ሳለ፣ ሕጻኑ ደግሞ ከተወለደ በኋላ እግዚኣብሄር ቀስፎታል፡፡ ይህን ኹሉ ጉድ ይዘው ወገኖቻችን በቁንጽል መረጃ ስለ ኢስላም ማውራታቸው ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ያስብላል – ራስን መሸንገል፡፡

ጉድሽ ለመብዛቱ ስፍር ቁጥር የለው

ደበቅበቅ አድርገሽ መናገርሽ ምነው

ባደባባይ መሐል በክት እየጎተተ፣እየሰለቀጠ

አልታየኹ አይልም ሰው ራሱን ካልሸጠ

 

Shortlink http://q.gs/Eye1o