ልፋት ለምኔ? ክፍል አንድ በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
55 Views

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
አንድም ትክክለኛውን የቀዷ ወል-ቀደር ጽንሰ-ሀሳብ ባለመገንዘብ፡ አልያም ራስ ግራ ተጋብቶ ሌላውንም ግራ ለማጋባት በተደጋጋሚ የሚነሳ ጥያቄ አልለ፡፡ እሱም፡- እኛ የምንሰራው ስራ በጠቅላላ አስቀድሞ የታወቀ፣ የተጻፈና የተወሰነ ከሆነ ለምን እንለፋለን ታዲያ? ደግሞስ የኛ ነጻ-ፈቃድ ትርጉሙ ምኑ ላይ ነው? በመጨረሻው ቀንስ ጌታችን ለምን ይተሳሰበናል? የሚል ነው፡፡ ለነዚህ ጥያቄዎች በአላህ ፈቃድ የቻልኩትን ያህል ምላሹን ለማብራራት እሞክራለሁ ኢንሻአላህ፡-

1ኛ፡- ቀጥታ መደ መልሱ ገብተን ዝርዝር ነጥቡን ከማየታችን በፊት እነዚህን ነጥቦች ከልብ እናስተውላቸው፡-

ሀ/ ስንናገር የፈለግነውን ቃላት በምንችለው ቋንቋ መርጠን ሀሳባችንን እንገልጻለን፡፡ ምላሳችን ሰውን መመረቅና ዱዓእ ማድረግ እንደሚችለው ሁሉ፡ መራገምና መሳደብም ይችላል፡፡ ማንኛችንም ብንሆን በንግግር ወቅት የሆነ የማናውቀው ውጪያዊ ኃይል፡ መናገር የማንፈልገውን ነገር እንድንናገር እንዳስገደደንና ላያችን ላይ እንደተጫነብን አይሰማንም፡፡ ለመልካሙም ሆነ ለመጥፎው ንግግር ተናጋሪው እኛው መሆናችንን ውስጣችን ያምናል፡፡

ለ/ መስሚያችን ሲፈጠር የመስማት ባህሪ ተሰጥቶት ነው የተፈጠረው፡፡ ምን እንሰማለን? የሚለው ግን በኛ ምርጫ ላይ የተመረኮዘ ነው የሚሆነው፡፡ የቁርኣን ጣቢያዎችን ከፍተን የአላህን ቃል የሰማንበት ጆሮ፡ የሙዚቃ ጣቢያ ብንከፍትለት ይህንን እንኳ አልሰማም ብሎ ራሱን አይደፍንም፡፡ የወንድሞችንና የእህቶችን ምክርና ዳዕዋ ለመስማት ያዘጋጀነው ጆሮአችን፡ በዛው መልኩ ሐሜትንና አለ ተባለ ወሬን በደንብ መስማት ይችላል፡፡ የአየር ሞገድ የሚያመጣው ተባራሪ ድምጽ ጆሮአችን ካልገባ በቀር፡ ከዛ ውጪ ማንኛውንም ነገር ለመስማት ያለ ፍላጎታችን የተገደድንበት ምንም አይነት ሁኔታ የለም፡፡

ሐ/ አይናችን አላህ ተመልካች አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ ማየት መቻሉ ተፈጥሮአዊ ባህሪው እንጂ የኛ ነጻ ፈቃድ ውጤት አይደለም፡፡ እንግዲያውስ በዚህ አይን ምን ታይበታለህ? የሚለው ነገር በኛ ምርጫ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ይህን አይናችንን ሰበር አድርገን የቀኝ መንገዳችንን ይዘን መጓዝ እንደምንችለው ሁሉ፡ ቀና በማድረግም ያልተፈቀደልን እይታ ላይ ማተኮርና ማፍጠጥ እንችላለን፡፡ አፍሪካ ቲቪ ላይ ያረፈው አይናችን፡ ቃና ቲቪ ላይ (ውስጤ አይደለም) ለማረፍም የሚያግደው የለም (የአላህ ተውፊቅ የገጠመው ሲቀር)፡፡ ለምን አየህ? ተብለን ብንወቀስ፡ እኔ ምን ላድርግ? አይኔ እኮ ነው! ብለን ማመካኘት እንችላለንን? ወይንስ ማየት ያልፈለግነውን ነገር የመጀመሪያው የአይን ግጭት ካልሆነ በስተቀር ከዛ በኋላ ያለውን በግድ እንድናይ ተደርገን ነው ማለት እንችላለንን? በፍጹም!

መ/ ልቦናችን ማሰብና ማሰላሰል እንዲችል ሆኖ የተዘጋጀ አንድ የሰውነት ዋነኛ ብልት ነው፡፡ በሱ ሰበብ ለሰዎች የሚጠቅምን ነገር ለማምጣት መልካምን ማሰብ፣ ጥሩን መመኘት፣ ሰዎችን መውደድና ማፍቀር እንችልበታለን፡፡ በዛው ተቃራኒ ክፋትን ማሰብ፣ ምቀኝነትን፣ ጥላቻን ማስተማርና በልብ ቦታ እንዲይዝ ማድረግ እንችላለን፡፡ ማንም ሰው ተገዶ የማይወደውን አካል በልቡ እንዲወደው፣ መልካም ያሰበለትን ክፉ እንዲሆንበት አልተደረገም፡፡ ይህ የነጻ ፈቃድና የልምድ ውጤት ነው፡፡

ሠ/ እጃችን በተፈጥሮው መያዝ የሚችል አንድ አካል ነው፡፡ በዚህ እጃችን ከኪሳችን ገብተን ሳንቲም በማውጣት ለአላህ ብለን ሶደቃ እንደምናደርገው ሁሉ፡ ከሰው ኪስና ቦርሳ በመግባት ለስሜታችን ስንል መስረቅና መዝረፍ እንችልበታለን፡፡ በዚሁ እጃችን አደጋን ሰበብ ሁነን መከላከል እንደምንችለው ሁሉ፡ በተቃራኒውም ሰበብ በመሆን በሰው ላይ አደጋ ልናደርስ እንችላለን፡፡ ግን በኛ እጅ ማንም ሰው ሊገለገልበትና ሊጠቀምበት አይችልም፡፡ ያ አይነት ስሜትም ተሰምቶንም አያውቅም፡፡ ይህንን የምትቃወሙ ካላችሁ ደግሞ፡- እኔም ፖስት ያደረግሁት፣ እናንተም ላይክና ሼር ያደረጋችሁትና እንዲሁም ኮመንት የሰጣችሁት፡ በገዛ እጃችን አልነበረም ማለት ነውን?

ረ/ እግራችንን ጌታ አላህ መንቀሳቀስና መራመድ እንዲችል አድርጎ ነው የፈጠረው፡፡ ታዲያ በዚሁ እግር የአላህ ቤት በመጓዝ ለውዱ አምላካችን እንደምንቆምለት (እንደምንሰግድለት) ሁሉ፡ ሲኒማ ቤት በመሄድም ለነፍሲያችን ቋሚ ተሰላፊ እንሆናለን፡፡ ቀበሌ ሄዶ ወረፋ በመያዝም ለስጋዊ ህይወታችን ቀለብን እንሸምትበታለን፡፡ በኛ እግር ወደ መስጂድም ሆነ ወደ ሲኒማ ወይም ወደ ቀበሌ የተራመደ የለም፡፡ ምናልባት እንደ መኪና የእግር ኪራይ ተጀምሮ ከሆነ እንጂ (ለፈገግታ)፡፡

ሰ/ ኢራዳህ (ፈቃድና ፍላጎት) የሚባለውም ነገር ከኛው ጋር አብሮ የተፈጠረ ነው፡፡ ወደ ሆቴል እንደገባን ምግብ እሲኪመጣ አንጠብቅም፡፡ ቅድሚያ ሜኑ (ቃኢማህ) እንመለከታለን፡፡ ለምን? ተብለን ብንጠየቅ፡ የምፈልገውን ምግብ ለመምረጥ ነዋ! የሚል ይሆናል ምላሻችን፡፡ ሞባይል መሸጫ ገብተን መጀመሪያ ረድፍ ላይ የተቀመጠውን ሞባይል ገዝተን አንወጣም፡፡ ምክንያቱም፡- ጥሩና ለዋጋ ተስማሚ የሆነውን ሞባይል መምረጥ ስላለብን ነዋ! እንላለን፡፡ ልብስ ቤት ገብተን ማንኛውንም ጨርቅ አንስተን አንለብስም፡፡ ከሰውነታችን ጋር በውበትም ሆነ በልክ አብሮ የሚሄደውን እንመርጣለን (ለዚህ ሴቶች ትልቅ ምስክር ናቸው)፡፡

ታዲያ ከዚህ በኋላ እውን እኛ ነጻ-ፈቃድ የሌለን የአላህ ፍጡሮች ነን ማለት እንችላለን? እፍረት አይዘንምን? የፈለግነውን ነገር መርጠን መናገር፣ መስማትና ማየት ከቻልን ለምንፈልገው ሰው የፈለግነውን መጠን መስጠት ከቻልን፣ ወደፈለግነው ቦታ መሄድ ከቻልን ለምንድነው በቀዷ ወል-ቀደር የምናሳብበው? “ሐያእ ማድረግ ከኢማን ነው!” በማለት ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) አልመከሩንምን? ኧረ እንፈር ሼም ነው፡፡
ጌታችን አላህስ በነዚህ በሰጠን ኒዕማ ‹ጸጋ› ምን ሰራችሁበት ብሎ እኛን ቢጠይቀን አግባብነት የለውምን? በማዳም ቤት ለሰበርሽው ብርጭቆና በካውያ ላበላሸሽው ከንዱራ የጥፋተኝነት ስሜት ከተሰማሽ፡ እንዴት በአላህ መሬት ላይ ለፈጸምሺው ኃጢአት የጸጸት ስሜት አይሰማሽም? ኃጢአቱ የቀደር ውጤት እንጂ ያንቺ ፈቃድ የታከለበት ካልሆነ፡ የማዳም ንብረቶች ሲበላሹም የቀደር ውጤት ነው እንጂ የኔ ስህተት አይደለም ብለሽ ለመብትሽ ተካረከሪያ! (ልብ ሲኖርሽ አይደል!)
” ثُمَّ لَتُسْأَلُنَّ يَوْمَئِذٍ عَنِ النَّعِيمِ ” سورة التكاثر 8
“ከዚያም ከድሎታችሁ ሁሉ፣ በዚያ ቀን ትጠየቃላችሁ።” (ሱረቱ-ተካሡር 102፡8)፡፡

2ኛ/ አሁን ደግሞ ወደ ጥያቄው እንመለስና፡- ሁሉም ነገር ቀድሞ የተጻፈና የተወሰነ ከሆነ ለምን እንለፋለን ታዲያ? የሚለውን እንየው፡-

ሀ/ የምንለፋውና የምንሰራው፡- ጌታችን አላህ ስሩ ብሎ ስላዘዘን ነው፡፡ አላህ የኛ ጌታ ነው፡፡ እኛ ደግሞ የርሱ ባሮች ነን፡፡ ጌታ በባሪያው ላይ ሙሉ ስልጣን አለው፡፡ ባሪያ ግን ነጻነቱ የጌታውን ፈቃድ መፈጸም እንጂ፡ ከጌታው ትእዛዝ ወጥቶ የራሱን ነጻነት በራሱ ማወጅ አይደለም፡፡ እኛ የአላህ ጥገኞች ነን፡፡ እኛነታችንእራሱ የአላህ ነው፡፡ የኔ የምንለው ማንነት የለንም፡፡ ካልነበርንበት ዓለም በችሎታው አስገኘን፡፡ ከዛም ቀጥሎ በህይወት መኖር እስከፈቀደልን ጊዜ ድረስ ሲሳያችንንም ኃላፊነቱን ወስዶ ይቀልበናል፡፡ በመጨረሻም የሰጠንን ህይወት ሩሓችንን ከውስጣችን በማውጣት ይገድለናል፡፡ ቀጥሎም ሬሳችን በክብር ከአፈር በታች እንዲቀበር ያደርጋል፡፡ ከዛም እሱ በፈለገው ቀን በቀንዱ (በጥሩንባው) መልአኩን እንዲነፋ በማዘዝ ዳግም ይቀሰቅሰናል፡፡ በመቀስቀስም በፊቱ አቁሞ ለፍርድ ይተሳሰበናል፡፡ እንደ ስራችን መጠንም በፍትሐዊነቱ ዋጋችንን ይከፍለናል፡፡
” قُتِلَ الْإِنْسَانُ مَا أَكْفَرَهُ * مِنْ أَيِّ شَيْءٍ خَلَقَهُ * مِنْ نُطْفَةٍ خَلَقَهُ فَقَدَّرَهُ * ثُمَّ السَّبِيلَ يَسَّرَهُ * ثُمَّ أَمَاتَهُ فَأَقْبَرَهُ * ثُمَّ إِذَا شَاءَ أَنْشَرَهُ * كَلَّا لَمَّا يَقْضِ مَا أَمَرَهُ * فَلْيَنْظُرِ الْإِنْسَانُ إِلَى طَعَامِهِ * أَنَّا صَبَبْنَا الْمَاءَ صَبًّا * ثُمَّ شَقَقْنَا الْأَرْضَ شَقًّا * فَأَنْبَتْنَا فِيهَا حَبًّا * وَعِنَبًا وَقَضْبًا * وَزَيْتُونًا وَنَخْلًا * وَحَدَائِقَ غُلْبًا * وَفَاكِهَةً وَأَبًّا * مَتَاعًا لَكُمْ وَلِأَنْعَامِكُمْ ” سورة عبس 32-17
“ሰው ተረገመ፤ ምን ከሐዲ አደረገው? (ጌታው) ከምን ነገር ፈጠረው?( አያስብምን?) ከፍትወት ጠብታ ፈጠረው መጠነውም። ከዚያም (መውጫ) መንገዱን አገራው። ከዚያም ገደለው፤ እንዲቀበርም አደረገው፤ ከዚያም (ማንሳቱን) በሻ ጊዜ ያስነሳዋል። በውነት ያንን (ጌታው) ያዘዘውን ገና አልፈጸመም። ሰውም ወደ ምግቡ ይመልከት፤ እኛ ውሃን ማንቧቧትን ያንቧቧን መሆናችንን፤ ከዚያም ምድርን (በደካማ ቡቃያ) መሰንጠቅን የሰነጠቅን፤ በውስጧም እኽልን ያበቀልን፤ ወይንንም፤ እርጥብ ሳርንም፤ የዘይት ወይራንም ዘንባባንም፤ ጭፍቆች አትክልቶችንም፤ ፍራፍሬንም ገለባንም፤ (ያበቀልን መሆናችንን ይመልከት)። ለናንተም ለእንሰሶቻችሁም መጠቀሚያ ይሆን ዘንድ (ይህን ሰራን)።” (ሱረቱ ዐበሰ 80፡17-32)፡፡
እናም የዚህን ጌታ ትእዛዝ ያልፈጸምን የማንን ትእዛዝ እንፈጽም? አዎ! የምንለፋው የምንሰራው፡- አምላካችን አላህ እኔ ያዘዝኳችሁን ነገር ስሩ ብሎ ስላዘዘን ነው፡፡
” وَقَضَى رَبُّكَ أَلَّا تَعْبُدُوا إِلَّا إِيَّاهُ وَبِالْوَالِدَيْنِ إِحْسَانًا إِمَّا يَبْلُغَنَّ عِنْدَكَ الْكِبَرَ أَحَدُهُمَا أَوْ كِلَاهُمَا فَلَا تَقُلْ لَهُمَا أُفٍّ وَلَا تَنْهَرْهُمَا وَقُلْ لَهُمَا قَوْلًا كَرِيمًا * وَاخْفِضْ لَهُمَا جَنَاحَ الذُّلِّ مِنَ الرَّحْمَةِ وَقُلْ رَبِّ ارْحَمْهُمَا كَمَا رَبَّيَانِي صَغِيرًا ” سورة الإسراء 24-23
“ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ፦ እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ፤ በወላጆቻችሁም መልካምን ሥሩ፤ በአንተ ዘንድ ሆነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ ፎህ አትበላቸው፤ አትገላምጣቸውም፤ ለነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው። ለሁለቱም ከእዝነትህ የመዋረድን ክንፍ ዝቅ አድርግላቸው፤ ጌታዬ ሆይ በሕጻንነቴ (በርኅራኄ) እንዳሳደጉኝ፣ እዘንላቸውም በል።” (ሱረቱል ኢስራእ 17፡23-24)፡፡

ለ/ የምንለፋውና የምንሰራው፡ ስራችን አላህ ዘንድ በራሕመቱ ሰበብ ተቀባይነትን ካገኘ፡ የልፋታችንን ዋጋ ለመቀበል ነው፡፡ እሱም፡- የአላህን መለኮታዊ ፊት ለማየት፣ የጀነትን ዘላለማዊ ህይወት ለማግኘት፣ የነቢያችንን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የጀነት ጉርብትናን ለማግኘትና፡ ከምንፈራው የጀሀነም እሳት ለመጠበቅ ነው፡፡
አላህ ትእዛዙን ያከበሩ ምእመናን ባሮቹን ጀነትን ሊሸልማቸው ቃል ገብቷልና፡-
“وَالَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ سَنُدْخِلُهُمْ جَنَّاتٍ تَجْرِي مِنْ تَحْتِهَا الْأَنْهَارُ خَالِدِينَ فِيهَا أَبَدًا وَعْدَ اللَّهِ حَقًّا وَمَنْ أَصْدَقُ مِنَ اللَّهِ قِيلًا ” سورة النساء 122
“እነዚያም ያመኑና በጎ ስራዎችን የሠሩ፣ በስራቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች ዘላለም በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲሆኑ እናገባዋቸዋለን፤ አላህ እውነተኛን ተስፋ ሰጣቸው። በንገገርም ከአላህ ይበልጥ እውነተኛ ማን ነው?” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡122)፡፡
” وَعَدَ اللَّهُ الْمُؤْمِنِينَ وَالْمُؤْمِنَاتِ جَنَّاتٍ تَجْرِي مِنْ تَحْتِهَا الْأَنْهَارُ خَالِدِينَ فِيهَا وَمَسَاكِنَ طَيِّبَةً فِي جَنَّاتِ عَدْنٍ وَرِضْوَانٌ مِنَ اللَّهِ أَكْبَرُ ذَلِكَ هُوَ الْفَوْزُ الْعَظِيمُ ” سورة التوبة 72
“አላህ ምእምናንንና ምእምናትን ከስሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶችም ዉስጥ መልካም መኖሪያ ቤቶችን ቃል ገብቶላቸዋል፤ ከአላህም የሆነዉ ዉዴታ ከሁሉ የበለጠ ነው፤ ይህ እርሱ ታላቅ ዕድል ነው።” (ሱረቱ-ተውባህ 9፡72)፡፡

3ኛ/ አሁን የሚነሳው ጥያቄ ደግሞ፡- እንግዲያውስ እኛም ነጻ ፈቃድና ምርጫ ያለን ፍጡሮች ከሆንን፣ ፈቃዳችንን ተጠቅመን የፈለግነውን ነገር መስራት ከቻልንና፡ በስራችን ልክ ደሞዛችንንም ከፍትሐዊው አምላክ ከአላህ ዘንድ የምንቀበል ከሆነ፡ ነገራት ሁሉ አስቀድሞ ተወስነው አልቀዋል፡፡ ሁሉ ነገር ተጽፎ ተጠናቆአል ማለት ምንድነው ታዲያ? እኛስ ይህን የተወሰነውን ነገር ጥሰን መውጣት እንችላለንን? ይህ የተወሰነው ነገርስ ከኛ ጋር ያለው ግኑኝነት ምንድነው? የሚለው ነው፡፡
የዚህን ጥቄ ምላሽ ከነ-ማብራሪያው በክፍል ሁለት ፕሮግራማችን ላይ አቀርበዋለሁ ኢንሻአላህ፡፡ አላህ እውነቱን እውነት አድርጎ ይግለጽልን፡፡ እንከተለውም ዘንድ እርዳታው አይለየን፡፡ ሀሰትን ሀሰት መሆኑን ለይቶ ይግለጽልን፡፡ እንርቀውም ዘንድ ጥበቃው አይለየን፡፡
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡