ልፋት ለምኔ? ክፍል አሥራ አንድ በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
322 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56)፡ ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181)፡ የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
በክፍል አሥር ትምሕርት ላይ አንድ ሰው ለሚሰራው ኃጢአት ተውበት ከማድረግ ይልቅ በቀደር ማሳበቡ ስህተት እንደሆነና፡ ይልቁኑ በተጨማሪ ጥፋት ሊያስቀጣው እንደሚችል አይተናል፡፡ አሁን የምንመለከተው ደግሞ ለጥፋታችን ቀደርን ማሳበብ እንችላለን የሚል ከተሳሳተ ግንዛቤ የመነጨውን ማሥረጃ ነው፡፡ ይህ ማሥረጃ የተወሰደው ከሐዲሥ ላይ ነው፡፡ ሐዲሡ እንዲህ ይነበባል፡-
عن أبي هريرة رضي الله عنه قال: قال رسول الله صلى الله عليه وسلم: “احتج آدم وموسى فقال موسى يا آدم أنت أبونا خيبتنا وأخرجتنا من الجنة فقال له آدم أنت موسى اصطفاك الله بكلامه وخط لك التوراة بيده أتلومني على أمر قدره الله علي قبل أن يخلقني بأربعين سنة فقال النبي صلى الله عليه وسلم فحج آدم موسى فحج آدم موسى فحج آدم موسى” رواه أبو داود.
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባስተላለፈው ሐዲሥ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “አደምና ሙሳ (ዐለይሂማ-ሰላም) ተከራከሩ፡፡ ሙሳም፡- አደም ሆይ! አንተ አባታችን ነህ፡፡ አዋረድከን ከጀነትም አስወጣኸን አለው፡፡ አደምም፡- ሙሳ ሆይ! አላህ አንተን በቀጥታ በማናገሩ መርጦሀል፡፡ ተውራትንም በመለኮታዊ እጁ ጽፎ ሰጥቶሀል፡፡ ታዲያ አላህ እኔን ከመፍጠሩ ከአርባ ዓመት በፊት ቀድሞ በወሰነብኝ ነገር ትወቅሰኛለህን? አለው፡፡ ነቢያችንም (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) አደም ሙሳን ረታው (አሸነፈው)፣ አደም ሙሳን ረታው፣ አደም ሙሳን ረታው አሉ” (አቡ ዳዉድ)፡፡
ይህን ሐዲሥ ቡኻሪና ሙስሊም እንዲሁም ሌሎች የሐዲሥ መዛግብት በውስጣቸው ያሰፈሩት የሆነ ታላቅ ሐዲሥ ነው፡፡ መልእክቱንም በደንብ ላስተዋለው ሰው በውስጡ፡- ለሚሰራ ጥፋት ቀደርን (ቅድመ ውሳኔን) ማሳበብ ይበቃል የሚል ሽታም እንኳ አያገኝበትም፡፡ እንዴት የሚባልም ከሆነ ቀጥለን እንየው፡-
1ኛ. በሙሳና በአደም (ዐለይሂማ-ሰላም) መካከል የተካሄደው ክርክር ከጀነት መውጣትን የተመለከተ እንጂ፡ በጀነት ውስጥ ከተከለከሉት ዛፍ ስለመብላት አልነበረም፡፡ ሙሳም አደምን፡- አንተንም እኛንም ለምን ከጀነት አስወጣኸን? በማለት ጠየቀው እንጂ፡ ከተከለከልከው ከዛፍ ፍሬ ወስደህ ለምን በላህ? አላለውም፡፡ አደም በጀነት እያለ ከተከለከለው የዛፍ ፍሬ ወስዶ መብላቱ ‹መዕሲያህ› (አመጽ) ሲሆን፡ ከጀነት መውጣቱ ደግሞ ‹ሙሲባህ› (ከአላህ የሆነ መከራ፡ ፈተና) ነው፡፡ ውይይቱ የሚያተኩረው ሙሲባው ላይ ነው፡፡

2ኛ. አደም በጀነት እያለ ለፈጸመው አመጽ (መዕሲያህ) በቀደር ሳይሆን ያሳበበው፡ እራሱን በመውቀስ የጌታውንም ምሕረት በመሻት ከባለቤቱ ጋር ተውበት ገብቷል፡፡ አላህም ይቅር ብሏቸዋል፡፡ የኃጢአት ምሕረትንም አግኝተዋል፡፡
” قَالَا رَبَّنَا ظَلَمْنَا أَنْفُسَنَا وَإِنْ لَمْ تَغْفِرْ لَنَا وَتَرْحَمْنَا لَنَكُونَنَّ مِنَ الْخَاسِرِينَ ” سورة الأعراف 23
“ጌታችን ሆይ! ነፍሶቻችንን በደልን፤ ለኛ ባትምር ባታዝንልም በእርግጥ ከከሳሪዎቹ እንሆናለን አሉ።” (ሱረቱል አዕራፍ 7፡23)፡፡
” فَتَلَقَّى آدَمُ مِنْ رَبِّهِ كَلِمَاتٍ فَتَابَ عَلَيْهِ إِنَّهُ هُوَ التَّوَّابُ الرَّحِيمُ ” سورة البقرة 37
“አደምም ከጌታው ቃላትን ተቀበለ፡፡ በርሱ ላይም (ጌታው ጸጸትን በመቀበል) ተመለሰለት፤ እነሆ እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡37)፡፡
“አት-ታኢቡ ሚነ-ዘንቢ ከመን-ላ ዘንበ ለህ” (ከኃጢአት በተውበት የሚመለስ ኃጢአት እንደሌለበት ነውና) አደምም ተውበት ባደረገበት ጥፋት ሊወቀስ አይገባም፡፡ ሙሳም (ዐለይሂ ሰላም) ይህን ነገር ጠንቅቆ ያውቃልና ‹ሊማዛ አከልተ ሚነ-ሸጀራህ?› (ከዛፊቷ ወስደህ ለምን በላህ?) በማለት ወቀሳን አላቀረበም፡፡ ያቀረበው ወቀሳ ‹ሊማዛ አኽረጅተና ወነፍሰከ ሚነል-ጀንናህ?› (ለምን እራስህንም እኛንም ከጀነት አስወጣኸን?) ነበር ያለው፡፡ የአደም ከጀነት መውጣት ደግሞ ሙሲባህ ነው፡፡ ሙሲባህ (መከራንና ፈተናን) ደግሞ ሰው በገዛ ፈቃዱ ፈልጎና አቅዶ የሚያመጣው ነገር ባለመሆኑ፡ አደምም፡- ሙሳ ሆይ! አላህ እኔን ከመፍጠሩ ከአርባ ዓመት በፊት ቀድሞ በወሰነብኝ ነገር ትወቅሰኛለህን? በማለት በቀደር በማሳበብ መለሰለት፡፡ ነቢያችንም (ዐለይሂ ሶላቱ ወስ-ሰላም) አደም ሙሳን ረታው በማለት የንግግሩን እውነተኝነት አጸደቁለት፡፡

3ኛ. ሙሲባህ ከአላህ ዘንድ የሚመጣ ውሳኔ ነው፡፡ ሰበቡ የሰዎች ኃጢአት መብዛት ሊሆን ይችላል (አን-ኒሳእ 4፡79)፡፡ ወይንም አላህ ባሪያዎቹን ለመፈተን የሚያደርገው ሊሆን ይችላል (አል-በቀራህ 2፡155-156)፡፡ በሁለቱም መንገድ ብናየው እንኳ ሰው በሚደርስበት ሙሲባህ ሳይሆን የሚወቀሰው፡ በሰራው ኃጢአት ነው የሚወቀሰው፡፡ ምክንያቱም ኃጢአቱ ላይ የገዛ ፈቃዱ ስለታከለበትና ፈልጎ ስለሰራው ሲሆን፡ ሙሲባውን ግን ፈልጎ ያመጣው ነገር ስላልሆነ ነው፡፡ አደምና ሐዋእም (ዐለይሂማ-ሰላም) ከዛፊቷ ወስደው ሲበሉ፡ በሸይጧን አሳሳችነት ሁሌም ህያው የሚሆኑ መስሏቸው እንጂ ከጀነት ለመውጣት አቅደው አይደለም፡፡ ለፈጸሙት ጥፋት ተውበት አደረጉ፡፡ አላህም ማራቸው፡፡ ቀድሞ በተወሰነው መሰረት ደግሞ ከጀነት እንዲወጡና በምድር ላይ እንዲኖሩ ተደረጉ፡፡ አላህ አስቀድሞውኑ ሰውን ሳይፈጥር በፊት ለመላእክት፡- ‹‹እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ!›› ብሎ አሳወቃቸው እንጂ፡ በጀነት ላይ አደርጋለሁ አላለም (አል-በቀራህ 2፡30)፡፡

4ኛ. ሁኔታውን ግልጽ ለማድረግ አንድ ምሳሌ እንመልከት፡- ወደ ሌላ ከተማ ለመሄድ ጓዝህን ጠቅልለህ እየተሳፈርክ ሳለ፡ በጉዞህ ላይ የመኪና መገልበጥ አደጋ ቢደርስብህና በሰውነትህ ላይ ጉዳት ቢደርስብህ፡ ቤተሰቦችህ፡- ለምን ወደዚያ ከተማ አቀናህ? እቤት አርፈህ ብትቀመጥ ኖሮ ይህ ሁሉ ጉዳት ሊደርስብህ አይችልም ነበር! በማለት አንተን መውቀስ ይችላሉን? በፍጹም አይችሉም!፡፡ ምክንያቱም፡- አንተ ወደ ከተማው ያቀናኸው ለጉዳይ እንጂ ሰውነትህን አደጋ ላይ ለመጣል አይደለም፡፡ እሱ በመንገድ እያለህ ካንተ ፈቃድ ውጪ ሆኖ የተከሰተ የአላህ ቀደር ነው፡፡ ስለዚህ አንተ ልትወቀስበት አይገባም፡፡ አደምና ሐዋእም ለምን ከጀነት ወጣችሁ? ተብለው እንዳይወቀሱ፡ መች ከጀነት እንውጣ ብለው ከዛፊቷ በሉ? የሚል ጥያቄ ይነሳልና፡፡

5ኛ. እኛም ከዚህ ታላቅ ሐዲሥ የምንወስደው ትምህርት፡- ኃጢአት በሰራን ጊዜ በቀደር ከማሳበብ ይልቅ እንደ ሁለቱ ወላጆቻችን በፍጥነት ተውበት መግባትንና፡ የሆነ ሙሲባ በሚደርስብን ጌዜ ደግሞ ‹‹ቀደረላሁ ወማ ሻአ ፈዐል›› (አላህ ወሰነ እሱ የሻውን ሰራ!) በማለት ቀደርን መጠቀም እንዳለብን ነው፡፡ በተለይ በሙሲባህ ወቅት ቀደርን ማሳበብ እንደሚቻል የአላህ ቃልና የመልክተኛው ሐዲሥ ማረጋገጫን ይሰጡናል፡-
عَنْ أَبِي

هُرَيْرَةَ، قَالَ: قَالَ رَسُولُ اللهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: «الْمُؤْمِنُ الْقَوِيُّ، خَيْرٌ وَأَحَبُّ إِلَى اللهِ مِنَ الْمُؤْمِنِ الضَّعِيفِ، وَفِي كُلٍّ خَيْرٌ احْرِصْ عَلَى مَا يَنْفَعُكَ، وَاسْتَعِنْ بِاللهِ وَلَا تَعْجَزْ، وَإِنْ أَصَابَكَ شَيْءٌ، فَلَا تَقُلْ لَوْ أَنِّي فَعَلْتُ كَانَ كَذَا وَكَذَا، وَلَكِنْ قُلْ قَدَرُ اللهِ وَمَا شَاءَ فَعَلَ، فَإِنَّ لَوْ تَفْتَحُ عَمَلَ الشَّيْطَانِ» رواه مسلم 6945
ከአቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ጠንካራ ሙእሚን አላህ ዘንድ ከደካማው ሙእሚን በላጭና ተወዳጅ ነው፡፡ በሁለቱም ዘንድ መልካም አልለ፡፡ የሚጠቅምህ ነገር ላይ ጥረት አድርግ፡፡ በአላህም ታገዝ አትሳነፍ፡፡ (በዚህ መሀል) አንዳች ነገር ቢገጥምህ፡ እንዲህ የሰራሁት ቢሆን ኖሮ እንዲህ ይሆን ነበር! አትበል፡፡ ግን አላህ ወሰነ! እሱ የሻውንም ፈጸመ በል፡፡ ‹‹ቢሆን ኖሮ፣ ባይሆን ኖሮ›› የምትለዋ ቃል የሸይጧንን በር ትከፍታለችና” (ሙስሊም 6945)፡፡
” وَلَنَبْلُوَنَّكُمْ بِشَيْءٍ مِنَ الْخَوْفِ وَالْجُوعِ وَنَقْصٍ مِنَ الْأَمْوَالِ وَالْأَنْفُسِ وَالثَّمَرَاتِ وَبَشِّرِ الصَّابِرِينَ * الَّذِينَ إِذَا أَصَابَتْهُمْ مُصِيبَةٌ قَالُوا إِنَّا لِلَّهِ وَإِنَّا إِلَيْهِ رَاجِعُونَ ” سورة البقرة 156-155
“ከፍርሃትና ከረኃብም በጥቂት ነገር፣ ከገንዘቦችና ከነፍሶችም፣ ከፍራፍሬዎችም በመቀነስ በእርግጥ እንሞክራችኋለን፡፡ ታጋሾችንም (በገነት) አብስር፡፡ እነዚያን መከራ፤ በነካቻቸው ጊዜ «እኛ ለአላህ፤ ነን እኛም ወደርሱ ተመላሾች» ነን የሚሉትን (አብስር)፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡155-156)፡፡
” مَا أَصَابَ مِنْ مُصِيبَةٍ فِي الْأَرْضِ وَلَا فِي أَنْفُسِكُمْ إِلَّا فِي كِتَابٍ مِنْ قَبْلِ أَنْ نَبْرَأَهَا إِنَّ ذَلِكَ عَلَى اللَّهِ يَسِيرٌ * لِكَيْلَا تَأْسَوْا عَلَى مَا فَاتَكُمْ وَلَا تَفْرَحُوا بِمَا آتَاكُمْ وَاللَّهُ لَا يُحِبُّ كُلَّ مُخْتَالٍ فَخُورٍ ” سورة الحديد 23-22
“በምድርም በነፍሶቻችሁም መከራ (ማንንም) አትነካም ሳንፈጥራት በፊት በመጽሐፍ የተመዘገበች ብትሆን እንጅ፤ ይህ በአላህ ላይ ገር ነው። (ይህ ማሳወቃችን) ባመለጣችሁ ጸጋ ላይ እንዳታዝኑ አላህም በሰጣችሁ ነገር (በት ዕቢት) እንዳትደሰቱ ነው፤ አላህም ኩራተኛን ጉረኛን ሰው አይወድም።” (ሱረቱል ሐዲድ 57፡22-23)፡፡
አላህ የበለጠውን ዐዋቂ ነው፡፡
ይቀጥላል
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡