ልፋት ለምኔ? ክፍል አሥራ አምስት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
503 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
ማጠቃለያ፡-
እስከዛሬ ባሳለፍነው አሥራ አራት ክፍሎች ስለ ቀዷ ወል-ቀደር የተወሰነ ግንዛቤ እንዲኖረን፡ በጉዳዩ ላይ መጠነኛ ዳሰሳ አድርገናል፡፡ የነበረውን አጠቃላይ ሁኔታ ጠቅለል በማድረግ እኛ በቀደር ዙሪያ ሊኖረን የሚገባውን መሰረታዊ አቋም ለመግለጽ እሞክራለሁ ኢንሻአላህ፡፡

1ኛ/ በቀደር እናምናለን፡፡ ቀደርን አምኖ መቀበል ከስድስቱ የእምነት ማዕዘናት (አርካኑል ኢማን) አንዱ ነውና፡፡ ስለዚህም በዚህ ዓለም ላይ የሚከናወኑ ክስተቶች፡ ጥሩም ሆኑ መጥፎ፣ ሰው በነጻ ፈቃዱ የሚተገብራቸውም ሆኑ ከሰው ፈቃድ ውጪ ያሉ ነገራት በጠቅላላ የቀዷ ወል-ቀደር ውጤት ናቸው ብለን እናምናለን፡፡ የቀዷ ወል-ቀደር ውጤት ነው ስንልም በውስጡ የሚካተቱት ደረጃዎች፡-

ሀ/ አላህ ቀድሞ ያወቃቸው መሆኑን እናምናለን፡- ከአላህ ዕውቀት ውጭ ሊሆን የሚችል ነገር የለም፡፡ አላህ ከዚህ በፊት ተፈጽሞ ያለፈን፣ አሁን እየተፈጸመ ያለን፣ ወደፊት ሊመጣ ያለ ገና ያልተፈጸመን፡ እንዲሁም የማይሆንን ነገር ራሱ የመሆን ዕድል ቢሰጠው ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያውቅ አምላክ ነውና፡፡ (አል-አንዓም 6፡59፣ ዩኑስ 10፡61፣ አል-ሙልክ 67፡13-14፣ ጋፊር 40፡7፣ አጥ-ጦላቅ 65፡12)፡፡

ለ/ አላህ በለውሐል መሕፉዝ ወስኖ የጻፈው (እንዲጻፍ ያዘዘው) መሆኑን እናምናለን፡- በዚህ ዓለም ላይ የሚከናወኑ ነገራት በጠቅላላ አላህ ዘንድ ቀድመው የታወቁ ናቸው እንደምንለው ሁሉ፡ በድጋሚም ተወስነው በመጽሐፍ ላይ የሰፈሩ ናቸው ብለንም እናምናለን፡፡ ስለዚህም ሁሉ ነገር ቀድሞ ተጽፎ ተጠናቋል፡፡ ቀድሞ ከታወቀውና በለውሐል መሕፉዝ ከተጻፈው ውጭ የሆነ እንግዳ ክስተት በዓለማችን ላይ ሊገባ አይችልም፡፡ የሚደርሰን መልካም ነገርም ሆነ የሚደርስብን መጥፎ ነገር (ሙሲባህ) በጠቅላላ ቀድሞ የተጻፈ ነው፡፡ አላህ ለኛ ያልጻፈው ወይም በኛ ላይ ያልጻፈው ምንም ነገር አያገኘንም ብለንም እናምናለን፡፡ (አል-አንዓም 6፡59፣ ዩኑስ 10፡61፣ አል-ቀመር 54፡52-53፣ ሁድ 11፡6፣ አት-ተውባህ 9፡51፣ አን-ነምል 27፡75፣ ሰበእ 34፡3፣ ፋጢር 35፡11፣ አል-ሐዲድ 57፡22-23)፡፡

ሐ/ ፈቃድ ሁሉ የአላህ መሆኑን እናምናለን፡- በዚህ ዓለማችን ውስጥ የሚከናወን ማንኛውም ክስተት፡ ገና ከመምጣቱ በፊት አላህ አስቀድሞ አውቆታል፡ በለውሐል መሕፉዝም ጽፎታል ብለን እንደምናምነው ሁሉ፡ በተጨማሪም ጊዜው ደርሶ ሲከሰትና ሲከናወን በአላህ ፈቃድና ይሁንታ የሚከናወን መሆኑንንም አምነን ተቀብለናል፡፡ ያለ አላህ ፈቃድ ንፋስ ሊነፍስም ሆነ አዋራ ከመሬት ሊነሳ አይችልም፡፡ አላህ እንዲሆን ሳይፈቅድ፡ ከፈቃዱ ውጭ በሆነ መልኩ የሚሆን ምንም ነገር የለም፡፡ ብቸኛው የዓለሙ ንጉስ እሱ ነውና፡ በንግስናው ላይ እሱ ያልሻው ነገር አይከሰትም፡፡ አላህ የሻው ነገር በጠቅላላ ይሆናል፡፡ አላህ ያልሻው ነገር በጠቅላላ አይሆንም ብለን እናምናለን፡፡ (አል-ኢንሳን 76፡29-30፣ አት-ተክዊር 81፡25-29፣ አል ከህፍ 18፡23-24፣ አል-ሙደሢር 74፡54-56)፡፡

መ/ መፍጠር የሱ ባሕሪና ሥራ ብቻ እንደሆነ እናምናለን፡- አላሁ (ሱብሐነሁ ወተዓላ) ብቻውን ፈጣሪና አስገኚ ጌታ ነው፡፡ ከሱ ውጭ ያለው ሁሉ፡ ፍጥረትና ግኝት ነው፡፡ ካለመኖር ወደ-መኖር የመጣ፣ ከሙታን ዓለም ወደ ህያዋን ዓለም፣ ከምንምነት ወደ ማንነት የተሸጋገረ ፍጥረት ነው፡፡ ስለዚህ አላህ ሰውን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ‹ስም› ያለውን ነገር ሁሉ የፈጠረ ጌታ ነው፡፡ ሰው ምንም ነገር አልፈጠረም ሊፈጥርም አይችልም፡፡ አላህ የሁሉ ነገር ብቸኛ ፈጣሪ ነው ብለን እናምናለን፡፡ (አል-አንዓም 6፡120፣ አር-ረዕድ 13፡16፣ አዝ-ዙመር 39፡62፣ አል-አንዓም 6፡101፣ ጋፊር 40፡62፣ አል-ፉርቃን 25፡2)፡፡

2ኛ/ ቀዷ ወል-ቀደር እውን ሆኖ በዚህ ዓለም ውስጥ ሲከሰት እና ሲከናወን፡ በሁለት መንገዶች እንደሆነ እናምናለን፡፡ ሁለቱም ቀደር ተብለው ይሰኙ እንጂ፡ እኛን በኃላፊነት ተጠያቂ የሚያደርገን ወይም ተጠቃሚ የሚያደርገን አንደኛው ክፍል ብቻ ነው፡፡ ሌላኛው ክፍል ደግሞ የአላህ ውሳኔ ‹ቀደር› መሆኑን አምነን መቀበል ብቻ ነው የሚጠበቅብን እንጂ ሌላ ድርሻ የለንም፡፡ ሁለቱም አይነት ክስተቶች ግን ከቀደር የወጡ አይደሉም፡፡ እነዚህም ክፍሎች፡-

ሀ/ ከሰው ነጻ ፈቃድ ውጭ የሆኑ ነገራት፡- ህያው ሆነን መፈጠራችን ወይም በአጀላችን (የሞት ጊዜ ሲደርስ) መሞታችን፣ ፆታችን ወንድ ወይም ሴት መሆኑ፣ መልካችን ጥቁር ወይም ቀይ ወይም ነጭ መሆኑ፣ ዘራችን ኦሮሞ ወይም አማራ፡ ትግሬ ወይም ጉራጌ፡ ሲዳማ ወይም ኩናማ መሆኑ፣ ቁመታችን መርዘሙና ማጠሩ እንዲሁም የመሳሰሉት ነገራት ላይ የአላህ ፈቃድ ብቻ ነው የሚከናወነው፡፡ በእንደዚህ አይነቱ የቀደር ክፍል ላይ እኛ ድርሻ ስለሌለን ተጠያቂ ወይም ተጠቃሚም ልንሆን አንችልም፡፡ ምክንያቱም የኛ ሥራ ጣልቃ-ገብነት የለበትምና፡፡ ከኛ የሚጠበቀው አላህ ወስኖ በሰጠንና ባከፋፈለን ነገር ወዶ መቀበልና ማመን ብቻ ነው፡፡ የአላህን ውሳኔ ማንም ሊቃወም አይችልም!፡፡ ለምን ወንድ ወይም ሴት አድርገህ ሰራኸኝ? ለምን ከኦሮሞ ወይም ከአማራ ዘር አስገኘኸኝ? ለምን ጥቁር አፍሪካዊ ወይም ነጭ አውሮፓዊ ሆኜ ተፈጠርኩ? የሚሉ መጠይቆችን በሀሳብ ደረጃም ቢሆን ወደ ህሊናችን እንዲመጡ መፍቀድ የለብንም፡፡ አላህ እንደፈለገው መሥራት ይችላልና፡፡ (አሊ-ዒምራን 3፡6፣ አሊ-ዒምራን 3፡47፣ አሊ-ዒምራን 3፡145፣ አል-ማኢዳህ 5፡17፣ አል-ቀሶስ 28፡68፣ አሽ-ሹራ 42፡49-50)፡፡

ለ/ በሰው ነጻ ፈቃድ ውስጥ ያሉ፡- ጉዳዩ አሁንም ከቀዷ ወል-ቀደር ያልወጣ ሆኖ፡ ግን የሰውን ነጻ ፈቃድ ጣልቃ ያስገባ፣ ሰበቢያን (ምክንያትን) የተቀበለ፣ ፈቃዳችንና ፍላጎታችንን ያካተተ የቀደር ክፍል አልለ፡፡ መብላትና መጠጣት፣ መነሳትና መቀመጥ፣ መሄድና መመለስ፣ መስጠትና መቀበል፣ መመረቅና መራገም፣ ምክርና ሐሜትን መስማት፣ ሰውን ማስታረቅና ነገር ማዋሰድ፣ መለገስና መስረቅ፣ ትዳር መመስረትና ዚና መፈጸም፣ ውሀና ኸምር መጠጣት፣ መስገድና መተው፣ አላህን ማምለክና በሱ ማሻረክ እንዲሁም የመሳሰሉት፡፡ በዚህ አይነቱ ተግባር ላይ ሰው ሰበብ ሆኖ በአላህ እገዛና ተውፊቅ መልካሙንና ጥሩውን ከሰራና ከፈፀመ የልፋቱን ዋጋ በአኼራ ያገኛል፡፡ የላቡን ደሞዝም በአላህ ቸርነት እጥፍ ድርብ ሆኖ ይቀበላል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በሸይጧንና በነፍሲያው አሳሳችነት፡ በዚህ ዓለም ብልጭልጭ ነገሮችና በመጥፎ ጓደኞች አታላይነት የተከለከለው ነገር ላይ ቢዘፈቅና፡ ተውበት ሳያደርግ እንዲሁም የአላህ ተውፊቅ ሳይገጥመው በዚያው ቢሞት፡ በአኼራ ከጥፋቱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት ይጠብቀዋል ብለን እናምናለን፡፡

3ኛ/ ሰው ነጻ ፈቃድ ያለው ፍጥረት እንደሆነ እናምናለን፡- ሰው በተሞላው መልኩ ብቻ የሚንቀሳቀስ ሮቦት አይደለም፡፡ ፈቃድ ያለው ፍጡር ነው፡፡ ስለዚህም ይህን አድርግ! ያንን ደግሞ አትቅረብ! የሚል አምካዊ ትእዛዝ ይመለከተዋል፡፡ አዕምሮ የሚባል መሳሪያ ከጌታው ዘንድ ተለግሷል፡፡ በሱም የሚጠቅመውን ከሚጎዳው መለየት ይችላል፡፡ ፈቃድና ምርጫም ተሰጥቶታል፡፡ የፈለገውን ነገር መምረጥና ወደሱም ማዘንበል ይችላል፡፡ ውስን ኃይል ተለግሷል፡፡ በሱ አማካኝነት የመረጠውን ነገር ጥሩም ሆነ መጥፎ ወደ ሥራ ሊቀይረው ይችላል፡፡ በዚህም ሰበብ ኃላፊነትን ተሸክሞ ነጌ በጌታው ዘንድ ተጠያቂ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በአኼራ ሰዎች ለፍርድ ሚዛን የሚቀርቡት በምድራዊ ህይወታቸው በተሰጣቸው ነጻ ፈቃድና ውስን ችሎታ አማካኝነት ባደረጉት እንጂ፡ ቀድሞ በታወቀውና በተጻፈው እንዲሁም በተወሰነው አይደለምና፡፡ (አን-ነሕል 16፡78፣ አል-ኢስራእ 17፡36፣ አል-ሙእሚኑን 23፡78፣ አስ-ሰጅዳህ 32፡9፣ አል-ሙልክ 67፡23፣ አል-አንፋል 8፡50-51፣ አል-ሐጅ 22፡9-10፣ አል-ጃሢየህ 45፡22፣ አጥ-ጡር 52፡21፣ አል-ሙደሢር 74፡38)፡፡

4ኛ/ ጥፋታችንን በቀደር ማሳበብ እንደማይበቃልን እናምናለን፡- በአላህ እገዛና ተውፊቅ መልካም ነገር ሰርተን ስናበቃ ‹‹አል-ሐምዱ ሊላህ›› ብለን እናመሰግንና፡ በአኼራ ደግሞ የጌታችንን ዕጥፍ ድርብ ምንዳ ተስፋ የምናደርግ ከሆነ፡ በዛው ተቃራኒ በሸይጧን ጉትጎታና በነፍሲያችን ድክመት ኃጢአት ላይ ስንወድቅም፡ ወዲያውኑ ‹‹አዑዙ ቢላህ›› በማለት ተነስተን በመጸጸት፡ ተውበት መግባትና አላህ በአኼራ በኃጢአቱ ሰበብ እንዳይቀጣን መማፀን አለብን፡፡

ይህን እምቢ ብለን፡ ተውበት ከመግባት ይልቅ፡- የሰራሁት ኃጢአት አላህ የወሰነብኝ የቀደር ውጤት ነውና እኔ ልጠየቅበት አይገባም! የሚል አቋም ከያዝን፡ እንግዲያውስ የሰራነው መልካም ሥራ ካለም እሱንም የአላህ ውሳኔ፡ የቀደር ውጤት ስለሆነ እንጂ እኛ ፈልገን አልሰራነውምና አጅርንም ከአላህ ተስፋ ማድረግ አይጠበቅብንም ማለት ነዋ!፡፡ ቀደር ከተባለ ሁሉም ቀደር ነውና፡፡ የተንሸዋረረ እይታ ከግብ አያደርስምና መጠንቀቁ ይበጀናል፡፡
እውነተኛ ሙእሚን ለሚሰራው ኃጢአት ቀደርን አያመካኝም፡፡ ምክንያቱም ከኃጢአቱ በፊት አላህ በሱ ላይ ቀድሞ የወሰነውና የጻፈው ምን እንደሆነ የሚያውቀው ነገር የለምና፡፡ እሱ የሚያውቀው ጌታው ይህንን አድርግ! ብሎ እንዳዘዘውና፡ ይህን ደግሞ ራቅ! በማለት እንደከለከለው ነው፡፡ በተሰጠው ነጻ ፈቃድ አማካኝነት ወደ መልካም ነገር ከሄደ አላህም አግዞት ካሳካለት ከጌታው አጅርን ይጠብቃል፡፡ ወደ ተከለከለው ቦታ ደግሞ ነፍሲያውና ሸይጧን አታለውት ሄዶ ከወደቀ ቶሎ በተውበት ይመለሳል እንጂ በቀደር አያሳብብም፡፡ ስለዚህም በቀደር ማመካኘት ለማንም አይጠቅምም፡፡ (አል-አንዓም 6፡39፣ አን-ኒሳእ 4፡165)፡፡
ይቀጥላል
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡