ልፋት ለምኔ? ክፍል አሥራ ሰባት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
313 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56)፡ ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181)፡ የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
በቀዷ ወል-ቀደር የማመን ጥቅሞች!

በክፍል አሥራ ስድስት ትምሕርታችን ላይ፡ ስለ ቀዷ ወል-ቀደር ሀሳብ አንስተን፡ በውስጡም በቀደር ማመን ለአንድ ሙስሊም ሊሰጡት ከሚችሉ ጥቅሞችና ፍሬዎች ውስጥ ሶሥቱን ለአብነት አንስተን ነበር፡፡ እነሱም፡-
ሀ/ ትእግስትንና ውዴታን
ለ/ የቀልብ እርጋታና የህሊና እረፍትን
ሐ/ ለሥራ መበርታትንና አለመስነፍን የሚሉት ነበሩ፡፡ አላህ ፈቃዱ ከሆነ ለዛሬው ደግሞ ቀሪውን ነጥብ ለማቅረብ እሞክራለሁ ኢንሻአላህ፡፡ መልካም ንባብ፡-

መ/ ጀግንነትንና ከፊት መገኘትን፡-

በቀዷ ወል-ቀደር ያመነ ሙስሊም ፈሪ ሊሆን በፍጹም አይችልም፡፡ ሁሌም ጀግንነትና ከፊት መገኘትን ይላበሳል፡፡ መከራዎችንና ስቃዮችን ለመቋቋም አቅሙንና ብርታቱን ይጎናጸፋል፡፡ ምክንያቱም፡ በሱ ላይ የሚደርሱት መከራዎችም ሆኑ ማንኛውም ነገር፡ ገና ከመፈጠሩ በፊት ቀድመው የተወሰኑ መሆናቸውን አምኖ ተቀብሏልና፡፡ የሱ መፍራትም ሆነ ወደ ኋላ መሸሽ አላህ ከወሰነበት ነገር ሊያርቀውና ሊያተርፈው እንደማይችል ጠንቅቆ ያውቃል ያምናልም፡፡ ደግሞም የሱ ሲሳይ በጌታው በአላህ እጅ እንጂ በፍጡራን እንዳልሆነ ያምናል፡፡ ስለዚህም እንዲህ የሚለውን የአላህ ቃል እያስታወሰ መከራና ችግርን ለመጋፈጥ እራሱን ያዘጋጃል፡-

” قُلْ لَنْ يُصِيبَنَا إِلَّا مَا كَتَبَ اللَّهُ لَنَا هُوَ مَوْلَانَا وَعَلَى اللَّهِ فَلْيَتَوَكَّلِ الْمُؤْمِنُونَ ” سورة التوبة 51

“አላህ ለኛ የጻፈልን (ጥቅም) እንጂ ሌላ አይነካንም እርሱ ረዳታችን ነው በአላህ ላይም ምእምናን ይመኩ በላቸዉ።” (ሱረቱ-ተውባህ 9፡51)፡፡

በዚህም ምክንያት ሙስሊም ከፍርሀት ቀንበር ይላቀቃል፡፡ ለአላህ እንጂ ለማንም አይዋረድም፡፡ እድሜውም ሆነ ሲሳዩ በጌታው በአላህ እጅ ብቻ መሆኑን ስለሚያምን ጌታውን እንጂ ማንንም አይፈራም፡፡ ተከታዩ ነቢያዊ ሐዲሥም ይህን ይበልጥ ያብራራዋል፡-

قال سيدنا رسول الله (صلى الله عليه وسلم) لا بن عمه عبد الله بن عباس رضي الله عنهما: ” واعلم أن ما أصابك لم يكن ليخطئك ، وما أخطأك لم يكن ليصيبك واعلم بأن الأمة لو اجتمعت على أن ينفعوك بشيء لن ينفعوك إلا بشيء قد كتبه الله لك ، ولو اجتمعوا على أن يضروك بشيء لن يضروك إلا بشيء قد كتبه الله عليك، رفعت الأقلام وجفب الصحف” أحمد و الترمذي.

የአላህ ነቢይ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአጎታቸውን ልጅ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስን (ረዲየላሁ ዐንሁማ) ሲመክሩት እንዲህ ብለዉት ነበር፡- “አንተን ያገኘህ ነገር ሁሉ ከመጀመሪያው ሊያልፍህ እንዳልነበር ዕወቅ፣ አንተን የሳተህ ነገር ሁሉ ከመጀመሪያው ሊያገኝህ ያልነበረ መሆኑን ዕወቅ፣ ህዝቦች አንተን በሆነ ነገር ለመጥቀም ቢሰባሰቡ፡ አላህ ቀድሞውኑ የጻፈልህን ካልሆነ በስተቀር በምንም ነገር ሊጠቅሙህ እንደማይችሉ ዕወቅ፣ ህዝቦች አንተን በሆነ ነገር ለመጉዳት ቢሰባሰቡ፡ አላህ ቀድሞውኑ ባንተ ላይ የጻፈብህን ካልሆነ በቀር በምንም ነገር ሊጎዱህ አይችሉም፣ (የውሳኔው) ብዕሮቹም ተነሱ፡፡ መዝገቡም (ቀለሞቹ) ደረቁ” (ቲርሚዚይ 2516)፡፡

ሠ/ የአቋም ጽናትን፡-

ሰው በተፈጥሮው መልካም ነገር ካገኘው ይኮራል ይንጠባረራል፡፡ መጥፎ ነገር ቢነካውና ጉዳት ቢገጥመው ደግሞ፡ ተስፋ ይቆርጣል፡ ያዝናል ይተክዛል፡፡ ታዲያ ይህን ሰው መልካም ነገር በሚገጥመው ጊዜ ከመኩራትና ከመንጠባረር፡ እንዲሁም መጥፎ ነገር በሚገጥመው ጊዜ ተስፋ ከመቁረጥና ከማዘን ሊጠብቀው የሚችል ነገር ቢኖር ‹‹ቀዷ ወል-ቀደር››ን አምኖ መቀበል ብቻ ነው፡፡

በቀደር ያመነ ሙስሊም፡ አንድ መልካም ነገር ቢገጥመው፡ ከጌታው ዘንድ የመጣ ችሮታ (ራሕመት) መሆኑን በማወቅ አመስጋኝ ይሆናል እንጂ፡ ከልክ አልፎ አይኮራም አይኩራራም፡፡ በዛው ተቃራኒ፡ የማያስደስተው የሆነ መጥፎ ነገር ቢደርስበት፡ ይህም ከጌታው ዘንድ የተወሰነበት መሆኑን በማወቅ እራሱን ለትእግስት ያዘጋጃል እንጂ፡ በምሬት ለሃዘንና ተስፋ መቁረጥ አይዳረግም፡፡ የተፈጠረው ለፈተና መሆኑን አውቋልና፡፡ ማግኘት እንዳለ ሁላ ማጣትም አልለ፡፡ በመልካም መፍፈተን እንዳለ ሁሉ በመጥፎ መፍፈተንም መኖሩን ያምናል፡፡ እንዲህ የሚለውን የጌታውን ቃልም ያስታውሳል፡-

” مَا أَصَابَ مِنْ مُصِيبَةٍ فِي الْأَرْضِ وَلَا فِي أَنْفُسِكُمْ إِلَّا فِي كِتَابٍ مِنْ قَبْلِ أَنْ نَبْرَأَهَا إِنَّ ذَلِكَ عَلَى اللَّهِ يَسِيرٌ * لِكَيْلَا تَأْسَوْا عَلَى مَا فَاتَكُمْ وَلَا تَفْرَحُوا بِمَا آتَاكُمْ وَاللَّهُ لَا يُحِبُّ كُلَّ مُخْتَالٍ فَخُورٍ ” سورة الحديد 23-22

“በምድርም በነፍሶቻችሁም መከራ (ማንንም) አትነካም ሳንፈጥራት በፊት በመጽሐፍ የተመዘገበች ብትሆን እንጅ፤ ይህ በአላህ ላይ ገር ነው። (ይህ ማሳወቃችን) ባመለጣችሁ ጸጋ ላይ እንዳታዝኑ አላህም በሰጣችሁ ነገር (በትዕቢት) እንዳትደሰቱ ነው፤ አላህም ኩራተኛን ጉረኛን ሰው አይወድም።” (ሱረቱል ሐዲድ 57፡22-23)፡፡

ረ/ የሞራል የበላይነትን፡-

በቀደር ማመን፡ ለአንድ ሙስሊም ውስጣዊ ክብርንና የሞራል የበላይነትን ያጎናጽፈዋል፡፡ ለነፍሱ ውርደትንና ሽንፈትን አይወድም፡፡ በውርደትና በበደል ላይ መዘውተርን አይቀበልም፡፡
በአንድ ወቅት ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በሁለት ሰዎች መሐል ዳኝነትን አስተናግደው ከፈረዱ በኋላ፡ ያ የተፈረደበት ሰው ‹‹ሐስቢየላሁ ወኒዕመል ወኪል›› ብሎ ዞር ሲል፡ የአላህ ነቢይም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም)፡- ‹‹አላህ ስንፍናን ይወቅሳል፡፡ ነገር ግን ጉብዝና ላይ አደራህን፡፡ ጉዳዩ ከአቅምህ በላይ የሆነ ጊዜ ግን ‹‹ሐስቢየላሁ ወኒዕመል ወኪል በል›› አሉት፡፡ (አቡ ዳዉድ)፡፡

በዚህ ሐዲሥ መሰረት፡ ሰው የገዛ ስንፍናውን ለማስቀረት ከመጣር ይልቅ ‹‹ሐስቢየላሁ ወኒዕመል ወኪል›› በሚል ቃል መሸሸግ የሚፈልግ ከሆነ፡ የተወገዘ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ከሱ የሚጠበቀው የአቅሙን ያህል ለለውጥ ይታገልና ከአቅሙ በላይ ሲሆን፡ ‹‹ሐስቢየላሁ ወኒዕመል ወኪል›› ማለቱ ነው፡፡

ሰ/ ከምቀኝነት መትረፍን፡-

በቀደር ያመነ ሙስሊም፡ በሰዎች ላይ ከመመቅኘት እራሱን ይቆጥባል፡፡ ምቀኝነት ማኃበረሰብን የሚጎዳ በሽታ ነው፡፡ በቀደር ያመነ ሰው፡ ሰዎች ባገኙት መልካም ነገር አይመቀኝም፡፡ አላህ የወሰነላቸው መልካም ነገር መሆኑን ያውቃልና፡፡ እሱ አላህ ደግሞ ለሚፈልገው ሲሳይን በማስፋት፡ ከሚፈልገው ላይ ደግሞ ሲሳዩን በማጥበብ ይፈትናል፡፡ ሰዎች ባገኙት ነገር መመቅኘት ማለት፡ የአላህን ውሳኔ ወዶ አለመቀበል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለጥፋት የሚዳርግ ትልቅ በሽታ ነው፡፡ አላህ ይጠብቀን፡፡

” أَمْ يَحْسُدُونَ النَّاسَعَلَى مَا آتَاهُمُ اللَّهُ مِنْ فَضْلِهِ فَقَدْ آتَيْنَا آلَ إِبْرَاهِيمَ الْكِتَابَ وَالْحِكْمَةَ وَآتَيْنَاهُمْ مُلْكًا عَظِيمًا ” سورة النساء 51

“ይልቁንም ሰዎችን፣ አላህ ከችሮታው በሰጣቸው ነገር ላይ ይመቀኛሉን? ለኢብራሂምም ቤተሰቦች መጽሐፍንና ጥበብን በእርግጥ ሰጠን፤ ታላቅንም ንግሥና ሰጠናቸው።” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡51)፡፡
የተከበራችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ! ለአሥራ ሰባት ተከታታይ ክፍሎች አብረን የቆየንበት የቀዷ ወል-ቀደር ትምሕርት በዚህ ተጠናቋል፡፡ እስካሁን በሰላም ላቆየን ጌታ አልሐምዱ ሊላህ፡፡ በቀደር ዙሪያ ብዙ ያልተነሱ ነጥቦች አልሉ፡፡ ወደፊት አላህ ፈቃዱ ከሆነ እነሱንም ጨምሬ በመጽሐፍ መልክ የማውጣት ዓላማው አለኝ፡፡ በአላህ ፈቃድም ዓላማዬ ይሳካል ኢንሻአላህ፡፡ የናንተም ዱዓ ወሳኝ ነው፡፡
ተፈፀመ!