ልፋት ለምኔ? ክፍል አሥራ ሦስት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
319 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56)፡ ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181)፡ የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
ሂዳያህ ከማን ይገኛል?
ሂዳያህ ማለት፡- ምሪት፣የተስተካከለ መንገድ ማለት ነው፡፡ አንድን ሰው “አላህ ሂዳያ ይስጥህ” ስንለው፡- ያስተካክልህ፣ያቅናህ፣ጽናቱን ይለግስህ እያልነው ነው ማለት ነው፡፡
“ሂዳያ” የሚለው ቃል ከነ-ርቢው በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ በ 62 ሱራዎች፣ በ 258 አንቀጾች ላይ 301 ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ ታዲያ እኛም ከተጠቀሰባቸው ስፍራዎች ውስጥ የምንወስደው ትምሕርት በተወሰነ መልኩ ይህን ይመስላል፡-

1. አላህ ሰዎችን በተፈጥሮ የመራቸው መሆኑን፡-
ጌታ አላህ ባሪያዎቹን በዚህ ምድር ላይ ከፈጠራቸው በኃላ ሊጠቅማቸው የሚችልን ነገር እንዲያገኙና ከሚጎዳቸውም ነገር እራሳቸውን እንዲያርቁ ሊያግዛቸው የሚችለውን ተፈጥሮአዊ ምሪት(ሂዳያ) ለግሷቸዋል፡፡ ቀጣዮቹ አንቀጾች ይህን የሚገልጹ ናቸው፡-
“سَبِّحِ اسْمَ رَبِّكَ الْأَعْلَى * الَّذِي خَلَقَ فَسَوَّى * وَالَّذِي قَدَّرَ فَهَدَى ” سورة الأعلى 3-1
“ከሁሉ በላይ የሆነዉን ጌታህን ስም አሞግሥ። የዚያን (ሁሉን ነገር) የፈጠረዉን ያስተካ ከለዉንም፤የዚያንም የወሰነዉን። (ለተፈጠረለት ነገር) #የመራዉንም፤” (ሱረቱል አዕላ 87:1-3)፡፡
“قَالَ فَمَنْ رَبُّكُمَا يَا مُوسَى * قَالَ رَبُّنَا الَّذِي أَعْطَى كُلَّ شَيْءٍ خَلْقَهُ ثُمَّ هَدَى ” سورة طه 50-49
“(ፈርዖንም)፦ ሙሳ ሆይ ጌታችሁ ማነው? አለ። ጌታችን ያ ለፍጥረቱ፣ ነገርን ሁሉ (የሚያስፈልገውን) የሰጠ ከዚያም #የመራው ነው አለው።” (ሱረቱ ጣሀ 20:49-50)፡፡
“أَمَّنْ يَهْدِيكُمْ فِي ظُلُمَاتِ الْبَرِّ وَالْبَحْرِ وَمَنْ يُرْسِلُ الرِّيَاحَ بُشْرًا بَيْنَ يَدَيْ رَحْمَتِهِ أَإِلَهٌ مَعَ اللَّهِ تَعَالَى اللَّهُ عَمَّا يُشْرِكُونَ ” سورة النمل 63
“ወይም ያ በየብስና በባሕር ጨለማዎች ውስጥ #የሚመራችሁ ነፋሶችንም ከዝናሙ በፊት አብሳሪ ሆነው የሚልክ (ይበልጣልን? ወይስ የሚያጋሩት?) ከአላህ ጋር ሌላ አምላክ አለን? አላህ (በርሱ) ከሚያጋሩዋቸው ሁሉ ላቀ።” (ሱረቱ-ነምል 27:63)፡፡

2. አላህ የሐቅን መንገድ የሚመራ መሆኑን፡-
አምላካችን አላህ ባሪያዎቹን ለስጋዊ ህይወታቸው የሚጠቅም የሆነውን ተፈጥሮኣዊ ምሪት በመለገስ ብቻ አልተገደበም፡፡ በመንፈሳዊ ህይወታቸውም የእውነትንና የሀሰትን መንገድ እንዲለዩበት ጠቁሟቸዋል፡፡ አመላክቷቸዋልም፡፡ ይህ አይነቱ ምሪት በዐረብኛው “ሂዳየቱል በያን ወል-ኢርሻድ” ተብሎ ይጠራል፡፡ ተከታዮቹ አንቀጾች ይህን ያብራራሉ፡-
“إِنَّا خَلَقْنَا الْإِنْسَانَ مِنْ نُطْفَةٍ أَمْشَاجٍ نَبْتَلِيهِ فَجَعَلْنَاهُ سَمِيعًا بَصِيرًا * إِنَّا هَدَيْنَاهُ السَّبِيلَ إِمَّا شَاكِرًا وَإِمَّا كَفُورًا ” سورة الإنسان 3-2
“እኛ ሰዉን፥ (በሕግ ግዳጅ) የምንሞክረዉ ስንሆን፥ ቅልቅሎች ከሆኑ የፍትወት ጠብታ ፈጠርነዉ፤ ሰሚ ተመልካችም አደረግነዉ። እኛ፥ ወይ አመስጋኝ ወይም ከሐዲ ሲሆን መንገዱን #መራነዉ፤ (ገለጽንለት)።” (ሱረቱል ኢንሳን 76:2-3)፡፡
“فَأَمَّا مَنْ أَعْطَى وَاتَّقَى * وَصَدَّقَ بِالْحُسْنَى * فَسَنُيَسِّرُهُ لِلْيُسْرَى * وَأَمَّا مَنْ بَخِلَ وَاسْتَغْنَى * وَكَذَّبَ بِالْحُسْنَى * فَسَنُيَسِّرُهُ لِلْعُسْرَى * وَمَا يُغْنِي عَنْهُ مَالُهُ إِذَا تَرَدَّى * إِنَّ عَلَيْنَا لَلْهُدَى ” سورة الليل 12-5
“የሰጠ ሰውማ ጌታውን የፈራም፤ በመልካሚቱም (እምነት) ያረጋገጠ፤ለገሪቱ ሥራ እናዘጋጀዋለን። የሰሰተ ሰውማ የተብቃቃም፤ (በራሱ የተመካ)፤ በመልካሚቱ (እምነት) ያስተባበለም፤ ለክፉይቱ ሥራ እናዘጋጀዋለን። በወደወም ጊዜ ገንዘቡ ከርሱ ምንም አይጠቅመውም። ቅኑን መንገድ #መግለፅ በኛ አለብን።” (ሱረቱ-ለይል 92:5-12)፡፡
“أَيَحْسَبُ أَنْ لَمْ يَرَهُ أَحَدٌ * أَلَمْ نَجْعَلْ لَهُ عَيْنَيْنِ * وَلِسَانًا وَشَفَتَيْنِ * وَهَدَيْنَاهُ النَّجْدَيْنِ ” سورة البلد 10-7
“አንድም ያላየው መሆኑን ያስባልን? ለርሱ ሁለት ዓይኖችን አላደረግንለትምን? ምላስንና ሁለት ከንፈሮችንም ሁለት መንገዶችም #አልመራነውምን?” (ሱረቱል በለድ 90:7-10)፡፡

2.1. ነቢያትም የሐቅን ጎዳና ማመላከት የሚችሉ መሆኑን፡-
መለኮታዊ ራእይን ከአላህ በአማና ተቀብለው ለተላኩለት ማኃበረሰብ በታማኝነት የሚያደርሱ ነቢያትም፡ በትምህርትም ሆነ በስራ ለማኃበረሰቡ አርአያ በመሆን እነሱም የሐቁን ጎዳና መግለጽና ማመላከት የሚችሉ መሆናቸውን እንረዳለን፡-
“وَيَقُولُ الَّذِينَ كَفَرُوا لَوْلَا أُنْزِلَ عَلَيْهِ آيَةٌ مِنْ رَبِّهِ إِنَّمَا أَنْتَ مُنْذِرٌ وَلِكُلِّ قَوْمٍ هَادٍ ” سورة الرعد 7
“እነዚያም የካዱት፥ በርሱ ላይ ከጌታው ታምር ለምን አልተወረደለትም ይላሉ፤ አንተ አስፈራሪ ብቻ ነህ ለሕዝብም ሁሉ #መሪ አላቸው።” (ሱረቱ ሁድ 11:7)፡፡
” اذْكُرْ فِي الْكِتَابِ إِبْرَاهِيمَ إِنَّهُ كَانَ صِدِّيقًا نَبِيًّا * إِذْ قَالَ لِأَبِيهِ يَا أَبَتِ لِمَ تَعْبُدُ مَا لَا يَسْمَعُ وَلَا يُبْصِرُ وَلَا يُغْنِي عَنْكَ شَيْئًا * يَا أَبَتِ إِنِّي قَدْ جَاءَنِي مِنَ الْعِلْمِ مَا لَمْ يَأْتِكَ فَاتَّبِعْنِي أَهْدِكَ صِرَاطًا سَوِيًّا * ” سورة مريم 43-41
“በመጽሐፉ ውስጥ ኢብራሂምንም አዉሳ፤ እርሱ በጣም እውነተኛ ነቢይ ነበርና። ላባቱ ባለ ጊዜ (አስታዉስ) ፦ አባቴ ሆይ የማይሰማንና የማያይን፣ ከአንተም ምንንም የማይጠቅምህን (ጣዖት)ለምን ትግገዛለህ? አባቴ ሆይ! እኔ ከዕዉቀት ያልመጣልህ ነገር በእርግጥ መጥቶልኛልና ተከተለኝ ቀጥተኛዉን መንገድ #እመራሃለሁና።” (ሱረቱ መርየም 19:41-43)፡፡
” هَلْ أَتَاكَ حَدِيثُ مُوسَى * إِذْ نَادَاهُ رَبُّهُ بِالْوَادِ الْمُقَدَّسِ طُوًى * اذْهَبْ إِلَى فِرْعَوْنَ إِنَّهُ طَغَى * فَقُلْ هَلْ لَكَ إِلَى أَنْ تَزَكَّى * وَأَهْدِيَكَ إِلَى رَبِّكَ فَتَخْشَى ” سورة النازعات 19-15
“የሙሳ ወሬ መጣልህን? ጌታው በተቀደሰው ሸለቆ በጡዋ በጠራው ጊዜ፤ ወደ ፈርዖን ኺድ፤ እርሱ ወሰን አልፏልና። በለውም፦ ወደ መጥራራትህ ላንተ (መንገድ) አለህን? ወደ ጌታህም #ልመራህ ትፈራውም ዘንድ፤ (መንገድ አለህን?) አለው።” (ሱረቱ-ናዚዓት 79:15-19)፡፡
” وَكَذَلِكَ أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ رُوحًا مِنْ أَمْرِنَا مَا كُنْتَ تَدْرِي مَا الْكِتَابُ وَلَا الْإِيمَانُ وَلَكِنْ جَعَلْنَاهُ نُورًا نَهْدِي بِهِ مَنْ نَشَاءُ مِنْ عِبَادِنَا وَإِنَّكَ لَتَهْدِي إِلَى صِرَاطٍ مُسْتَقِيمٍ * صِرَاطِ اللَّهِ الَّذِي لَهُ مَا فِي السَّمَاوَاتِ وَمَا فِي الْأَرْضِ أَلَا إِلَى اللَّهِ تَصِيرُ الْأُمُورُ ” سورة الشورى 53-52
“እንደዚሁም ወደ አንተ ከትእዛዛችን ሲሆን መንፈስን፣ (ቁርአንን) አወረድን፤ መጽሐፉም እምነቱም ምን እንደሆነ የምታውቅ አልነበርክም። ግን (መንፈሱን) ከባሮቻችን የምንሻውን ሰው በርሱ የምንመራበት ብርሃን አደረግነው። አንተም ወደ ቀጥተኛው መንገድ በእርግጥ #ትመራለህ። ወደዚያ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የርሱ ወደ ሆነው አላህ መንገድ፣ (ትመራለህ)፤ ንቁ ነገሮቹ ሁሉ ወደ አላህ ይመለሳሉ።” (ሱረቱ-ሹራ 42:52-53)፡፡

2.2. የነቢያት ወራሾችም ሊመሩ የሚችሉ መሆኑን፡-
ዑለማኦች የነቢያት ወራሽ ናቸው፡፡ ነቢያት ደግሞ ይህንኑ መለኮታዊ እውቀትን ዕንጂ ንብረትን ወይም ሌላ ነገርን አላወረሱም፡፡ እነዚህ ሊቃውንት ከነቢያት የወረሱትን ዕውቀት ከነቢያት ህልፈት በኋላ ኃላፊነቱን ተሸክመው ለትውልድ እያስተማሩ ወደ ሐቅ መንገድ የሚያመላክቱ መሪዎች መሆን እንደሚችሉ እንረዳለን፡፡ ተከታዮቹን አናቅጽ እንመልከታቸው፡-
” وَمِمَّنْ خَلَقْنَا أُمَّةٌ يَهْدُونَ بِالْحَقِّ وَبِهِ يَعْدِلُونَ ” سورة الأعراف 181
“ከፈጠርናቸውም ሰዎች በእውነት #የሚመሩ፣ በርሱም (ፍርድን) የሚስተካክሉ ሕዝቦች አልሉ” (ሱረቱል አዕራፍ 7:181)፡፡
” وَمِنْ قَوْمِ مُوسَى أُمَّةٌ يَهْدُونَ بِالْحَقِّ وَبِهِ يَعْدِلُونَ ” سورة الأعراف 159
“ከሙሳም ሕዝቦች በውነት #የሚመሩና በርሱም (ፍርድን) የሚያስተካክሉ ጭፍሮች አሉ።” (ሱረቱል አዕራፍ 7:181)፡፡
” وَقَالَ الَّذِي آمَنَ يَا قَوْمِ اتَّبِعُونِ أَهْدِكُمْ سَبِيلَ الرَّشَادِ ” سورة غافر 38
“ያም ያመነው አለ፦ ወገኖቼ ሆይ! ተከተተሉኝ፤ ቀጥታውን መንገድ እመራችኋለሁና።” (ሱረቱ ጋፊር 40:38)፡፡

3. ሂዳያን በልብ ማስቀመጥ የአላህ ብቻ መሆኑን፡-
አምላካችን አላህ በራሱም ሆነ በመልክተኞቹ፡ እንዲሁም በሊቃውንቶቹ አማካኝነት የገለጸውንና ያመላከተውን የሐቅ ጎዳና አምኖ መቀበል ለሚፈልግ ባሪያው በልቦናው ላይ ሂዳያውን ማስቀመጥና ጽናትንም መለገስ እንደሚችል አስረዳ፡፡ ይህ አይነቱ ምሪት በዐረብኛው “ሂዳየቱ-ተውፊቅ ወል-ኢልሀም” ይባላል፡፡ ይህ የአላህ እንጂ የማንም አይደለም፡፡ ነቢያትም ሆኑ ተከታዮቻቸው ሰዎችን የሐቅን መንገድ ከማመላከት ውጪ እውነቱን እንዲቀበሉ የሰዎችን ልብ የማቅናትና የማስተካከል ስልጣን አልተሰጣቸውም፡፡ ምክንያቱም ማን ከልቡ እውነትን እንደሚፈልግና ማን አስመሳይ እንደሆነ፡ ልብን በመመርመር የሚያውቅ እሱ ብቻ ነውና!! ስለሆነም የማቅናቱንና የማስተካከል ኃላፊነቱን ብቻውን ወስዶታል፡፡ ተከታዩን አንቀጽ ከልብ እናጢነው፡-
” لَيْسَ عَلَيْكَ هُدَاهُمْ وَلَكِنَّ اللَّهَ يَهْدِي مَنْ يَشَاءُ وَمَا تُنْفِقُوا مِنْ خَيْرٍ فَلِأَنْفُسِكُمْ وَمَا تُنْفِقُونَ إِلَّا ابْتِغَاءَ وَجْهِ اللَّهِ وَمَا تُنْفِقُوا مِنْ خَيْرٍ يُوَفَّ إِلَيْكُمْ وَأَنْتُمْ لَا تُظْلَمُونَ ” سورة البقرة 272
“እነርሱን #ማቅናት በአንተ ላይ የለብህም፡፡ ግን አላህ የሚሻውን ሰው #ያቀናል፡፡ ከገንዘብም የምትለግሱት (ምንዳው) ለነፍሶቻችሁ ነው፡፡ የአላህንም ፊት (ውዴታውን) ለመፈለግ እንጂ አትለግሱም፡፡ ከገንዘብም የምትለግሱት ሁሉ (ምንዳው) ወደናንተ ይሞላል፡፡ እናንተም አትበደሉም፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡272)፡፡
” إِنَّكَ لَا تَهْدِي مَنْ أَحْبَبْتَ وَلَكِنَّ اللَّهَ يَهْدِي مَنْ يَشَاءُ وَهُوَ أَعْلَمُ بِالْمُهْتَدِينَ ” سورة القصص 56
“አንተ የወደድከውን ሰው ፈጽሞ #አታቀናም፡፡ ግን አላህ የሚሻውን ሰው #ያቀናል እርሱም ቅኖቹን ዐዋቂ ነው፡፡” (ሱረቱል ቀሶስ 28:56)፡፡
” وَيَزِيدُ اللَّهُ الَّذِينَ اهْتَدَوْا هُدًى وَالْبَاقِيَاتُ الصَّالِحَاتُ خَيْرٌ عِنْدَ رَبِّكَ ثَوَابًا وَخَيْرٌ مَرَدًّا ” سورة مريم 76
“እነዚያንም የቀኑትን ሰዎች አላህ #ቅንነትን ይጨምርላቸዋል፤ መልካሞቹ ቀሪዎች (ሥራዎች) እጌታህ ዘንድ በምንዳ በላጭ ናቸዉ፤ በመመለሻም የተሻሉ ናቸው ።” (ሱረቱ መርየም 19;76)፡፡

3.1. ለልቦና ሂዳያን መለገስ ማንም የማይችል መሆኑን፡-
ከላይ ባየነው መሰረት እንዲህ አይነት ቅናቻን መለገስ ከአላህ ውጪ ማንም እንደማይችለው ነው፡፡ ምናልባትም በሁለቱ አይነት ሂዳያዎች (መምራትና ማቅናት) ምን ልዩነት አለ? ከተባለም፡- መምራት ማለት ወደተፈለገው አቅጣጫ የሚያደርሰውን መንገድ ማሳየት፣ ጥቆማ መስጠት ሲሆን፡ ማቅናት ማለት ግን ወደ ተፈለገው ቦታ ማድረስና ማገዝ ማለት ነው፡፡ ነቢያትና ተከታዮቻቸው የሐቅን መንገድ ከባጢል ለይተው አብጠርጥረው ለሰው ማስረዳትና መግለጽ ይችላሉ፡፡ ያ ሰው ግን እንዲቀበልና አምኖ እንዲጓዝ በልቦናው ላይ እውነትን ማስቀመጥ በፍጹም አይችሉም፡፡ ምክንያቱም የልቡ ፍላጎት ኒፋቅ ይሁን ኢኽላስ ለይተው ማወቅ አይችሉምና፡፡ ቀጣዩን እንመልከት፡-
…”مَنْ يَهْدِ اللَّهُ فَهُوَ الْمُهْتَدِ وَمَنْ يُضْلِلْ فَلَنْ تَجِدَ لَهُ وَلِيًّا مُرْشِدًا ” سورة الكهف 17
“…አላህ የሚያቀናው ሰው ቅኑ እርሱ ብቻ ነው፤ የሚያጠመውም ሰው ለርሱ #አቅኝን ረዳት አታገኝለትም።” (ሱረቱል ከህፍ 17)፡፡
“بَلِ اتَّبَعَ الَّذِينَ ظَلَمُوا أَهْوَاءَهُمْ بِغَيْرِ عِلْمٍ فَمَنْ يَهْدِي مَنْ أَضَلَّ اللَّهُ وَمَا لَهُمْ مِنْ نَاصِرِينَ ” سورة الروم 29
“ይልቁንም እነዚያ የበደሉ ስዎች ያለ ዕውቀት ዝንባሌዎቻቸውን ተከተሉ፤ አላህም ያጠመመውን ሰው #የሚያቀናው ማነው? ለነርሱም ከረዳቶች ምንም የላቸውም።” (ሱረቱ-ሩም 29)፡፡
አላህ የበለጠውን ዐዋቂ ነው፡፡
ይቀጥላል
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡