ልፋት ለምኔ? ክፍል አሥራ ሁለት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
303 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56)፡ ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181)፡ የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
ቀደርን በቀደር መከላከል፡-
በሕይወታችን ውስጥ ከላይ ሲታይ የማያስደስተንና የማንወደው የሆነ ‹‹ክፉ›› ነገር በቀደር አማካኝነት ሲከሰት፡ እጅ ሰጥተን አርፈን እንድንቀመጥ አልታዘዝነም፡፡ ምንም ጉዳዩ ቀደር ቢሆንም፡ እኛም በሌላ ቀደር ለመከላከልና ለመቀየር መጣር አለብን፡፡ በጥረታችን ሰበብ ‹‹ክፉ›› ብለን የጠራነው ክስተት፡ በአላህ ተውፊቅ ወደ መልካም ነገር ቢቀየርልንም አሁንም ቀደር ነው እንላለን፡፡ ለለወጠልን ጌታም ምሥጋና እናቀርባለን፡፡ የጥረታችን ውጤት፡ የነበረውን ነገር ለመቀየር ካላስቻለም፡ ቀደር ነው እንላለን፡፡ ሸሪዓችን በዚህ መልኩ ነው እንድንኖር ያዘዘን እንጂ፡ የአርባ ቀን ዕድሌ ነው! ብለን ተጣጥፈን እንድንቀመጥ አላዘዘንም፡፡
ድርቅና ረሐብ በአንድ አካባቢ ወይም መንደር ቢከሰት፡ አዎ ቀደር ነው! ይባላል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችን ይህን ድርቅና ረሐብ ለመከላከል ዱዓእ ከማድረጋቸው ጋር ምግብ ወዳለበት ቦታ በመጓዝ ረሐቡንና ድርቁን ማስወገድ ከተቻላቸውም እሱም ቀደር ነው!፡፡
ዝናብ በተጠበቀው ወቅት በመንደራችን ባይዘንብና የውሀ እጥረት ቢከሰት፡ ሰዎችም ለውሀ ዕጦት ችግር ቢዳረጉ አሁንም ነገሩ ቀደር ነው፡፡ ከዚያም ሰዎቹ አርፎ መቀመጥን ሳይሆን፡ ውሀን ፍለጋ ‹‹ሶላቱል ኢስቲስቃእ›› ከመስገዳቸውና በዱዓእ አላህን ከመለመናቸው ጋር፡ ውሀ ወደሚገኝበት ቦታ በመንቀሳቀስ ውሀን በማግኘት ጥማቸውን በማርካት እራሳቸውንም ሆነ እንስሶቻቸውን ከአደጋ፡ ሰበብ ሆነው ቢታደጉ ይህም ቀደር ነው፡፡
ከጥንቃቄ ጉድለት ወይም ለፈተና እንደ አተት (ኮሌራ) ያለ ተላላፊ በሽታም በሆነ ከተማ ላይ ቢከሰት፡ አርፎ መቀመጥ የአላህን ቀደር አሚን ብሎ መቀበል ሳይሆን ስንፍና ነው የሚባለው፡፡ የከተማው ሰዎች ከዚህ ተላላፊ በሽታ እራሳቸውን ለመከላከል ከመጠንቀቃቸው ጋር፡ በበሽታው የተጠቁ ታማሚዎችን አላህ እንዲያሽራቸው ዱዓእ እያደረጉ ወደ ክሊኒክና ጤና ጣቢያ በመውሰድ ክትትልን አድርገው ከበሽታው እንዲፈወሱ ማድረጋቸውም ቀደር ነው፡፡
ከዚህ ውጭ በመሆን ግን፡ አንድ የአላህ ባሪያ በረሐብ ወይም በውሀ ጥም ወይንም በበሽታ ሲፈተን፡ እነዚህን ነገራት መከላከያ ሰበባቸውን መጠቀም እየቻለ፡ በቃ ‹ቀደር› ነው! ብሎ አርፎ እጅ ቢሰጥና በዛም ሰበብ ህይወቱ ቢያልፍ፡ ከአላህ ትእዛዝ የወጣ አመጸኛ ሆኖ ሞተ ማለት ነው፡፡ ሸሪዐችን የተከሰቱ ነገራት በጠቅላላ መልካምም ሆኑ መጥፎ፡ ቀደር መሆናቸውን አምነን እንድንቀበል ጠየቀን እንጂ፡ መጥፎውን ሰበብ በመሆን ወደ ጥሩ ለመቀየር መንቀሳቀስን መች ከለከለንና? ዱዓእ ከሰበቦች ሁሉ ታላቁና ዋስትና ያለው ከመሆኑ ጋር፡ ሌሎች ሰበቦችንም እንድንጠቀም አላህ አዞናል፡፡ በገዛ እጃችን ሰበብ አደጋ ላይ መውደቅን ከልክሎናል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” وَأَنْفِقُوا فِي سَبِيلِ اللَّهِ وَلَا تُلْقُوا بِأَيْدِيكُمْ إِلَى التَّهْلُكَةِ وَأَحْسِنُوا إِنَّ اللَّهَ يُحِبُّ الْمُحْسِنِينَ ” سورة البقرة 195
“በአላህም መንገድ ለግሱ፡፡ በእጆቻችሁም (ነፍሶቻችሁን) ወደ ጥፋት አትጣሉ፡፡ በጎ ሥራንም ሥሩ፤ አላህ በጎ ሠሪዎችን ይወዳልና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡195)፡፡
አላህ አማኝ ባሪዎቹን በዚህ አንቀጽ ውስጥ፡- ካላቸው ነገር እንዲለግሱ ያዛቸዋል፡፡ በሱ መንገድ ከመታገልና ካላቸው ሲሳይ ደግሞ ከመስጠት መሸሽ ራስን ለጥፋት መዳረግ መሆኑን በመግለጽ፡ እራሳችሁን ለጥፋት አታድርጉ! በማለት ይመክራል፡፡
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የሕይወት ዘመን የተነሳ ጥያቄ ነበር፡፡ ጥያቄውም የቀረበው ለሳቸው ነበር፡፡ የሚገርመውም የሳቸው አጠር ያለ ድንቅ ምላሽ ነበር፡፡ ይኸው ጥያቄና መልሱን፡-
عَنْ أَبِي خِزَامَةَ، عَنْ أَبِيهِ قَالَ: سَأَلْتُ رَسُولَ اللهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ فَقُلْتُ: يَا رَسُولَ اللهِ، أَرَأَيْتَ رُقًى نَسْتَرْقِيهَا وَدَوَاءً نَتَدَاوَى بِهِ وَتُقَاةً نَتَّقِيهَا، هَلْ تَرُدُّ مِنْ قَدَرِ اللهِ شَيْئًا؟ قَالَ: هِيَ مِنْ قَدَرِ اللهِ. رواه ابن ماجه 3563 والترمذي 2065.
አቡ ኺዛማህ ከአባቱ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ሰምቶ እንዳስተላለፈልን፡ አባቱ እንዲህ አለ፡- “የአላህ መልክተኛን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከልክፍትና ከመሳሰለው ለመጠበቅ ዱዓእ ብናስደርግና ቁርኣን ብናስቀራ፣ ለሰውነታችንም መድኃኒትን ብንጠቀም፣ ከአደጋ ለመትረፍም ምሽግንና የመሳሰለውን መጠበቂያ ብንገለገል ከአላህ ቀደር የሚመልሰው ነገር ይኖራልን? በማለት ጠየቅኋቸው፡፡ እሳቸውም ‹‹እሱም የአላህ ቀደር ነው!›› በማለት መለሱልኝ” (ኢብኑ ማጀህ 3563፣ ቲርሚዚይ 2065)፡፡
– ‹‹ሩቅያህ›› ማለት፡ ዱዓእ በማደርግ ወይም የተወሰነ የቁርኣን ክፍልን በማንበብ ከልክፍትና ከመሳሰሉት መንፈሳዊ በሽታዎች እራስን ወይንም ሌላውን ለማከም የምንገለገልበት ሂደት ነው፡፡
በዚህ መንገድም ይሁን ወይም በባህላዊ ወይም ሜዲካል የሆኑ መድኃኒቶችን በመጠቀም እራሳችንን ለመፈወስ መሞከራችን ከአላህ ቀደር ያስጥለናል ወይ? ደግሞስ ጠላትን ፈርተን እራሳችንን ከአደጋ ለመጠበቅ ምሽግን እና ሌሎች መጠበቂዎችን ከለላ ብናደርግ አላህ የቀደረውን ይመልሰዋል ወይ? የሚለው የሶሓቢዩ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ጥያቄ ነበር፡፡
የመልክተኛው ምላሽም፡ በደረቁ ‹‹አዎ! ይመልሰዋል›› ወይም ‹‹አይ! አይመልሰውም!›› የሚል አልነበረም፡፡ ሶሓቢዩ ከቀደር ጋር በማገናኘት ስለሆነ ጥያቄውን ያነሳው፡ እሳቸውም እሱ ባነሳበት የጥያቄ መስመር በመጓዝ ‹‹መድኃኒቶቹንም ሆነ መጠበቂያዎቹን መገልገልህ እራሱ ቀደር ነው!›› የሚል ነበር፡፡
አንድ ሰው በልክፍትና በአካላዊ በሽታ መጠቃቱ፡ ጠላት ደግሞ እሱን ሊያጠፋው መምጣቱን ‹ቀደር ነው!› ብሎ ካመነ፡ ለምን መከላከያውንም አበጅቶ ከአላህ ዕርዳታ ጋር የአቅሙን ያህል እየታገለ ‹ይህም ቀደር ነው!› ለማለት ምን ይከብደዋል? የሚል ነው የመልክተኛው ምላሽ፡፡ ስለዚህ ቀደርን በቀደር መከላከል ይቻላል ማለት ነው፡፡
ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ይላል፡- “ዑመር ኢብኑል ኸጣብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ወደ ሻም ምድር ወጣ፡፡ በመንገድም የአቡ ዑበይዳህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባልደረባዎችና የሰራዊቱ መሪዎች ያገኙትና በሻም ምድር ወረርሺኝ (ተላላፊ በሽታ) እንደተከሰተ ይነግሩታል፡፡ ከዛም ዑመር ኢብኑል ኸጣብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ‹‹የመጀመሪያዎቹን ስደተኛ ሶሓቦች (ወደ በይቱል መቅዲስ ይሰግዱ የነበሩትን) ጥሩልኝ!›› በማለት አስጠርቶ ስለ-ጉዳዩ በመግለጽ ያማክራቸዋል፡፡ እነሱም በሀሳብ ይለያያሉ፡፡ ከፊሎቹ፡- ‹‹ለዓላማ ብለን አንዴ ወጥተናልና መመለስ የለብንም!›› የሚል ሀሳብ ሰጡ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ፡- ‹‹ካንተ ጋር የተቀሩ ሶሓባዎች አልሉ፡፡ እነሱን ወደዚህ ወረርሺኝ ወደ-ተከሰተበት ይዘህ መሄድህ አልታየንም!

›› አሉ፡፡ ዑመርም፡- ‹‹ሁላችሁም ውጡልኝ!›› ይሉና፡ አንሷሮችን (ሙሀጂሮችን የተቀበሉትን) ያስጠራል፡፡ እነሱንም በጉዳዩ ዙሪያ ሲያማክራቸው፡ እንደ ሙሀጂሮቹ ሀሳባቸው ለሁለት ይከፈላል፡፡ ከዛም እነዚህን አንሷሮች ያስወጣቸውና፡ የቁረይሽ ሽማግሌዎችን በማስገባት ሲያማክራቸው፡ እነሱ ሁሉም ባንድ ድምጽ፡- ‹‹ሰዎቹን ይዘህ ብትመለስና ወደ ከተማይቱ ባትገባ መልካም ነው ብለን እናያለን›› አሉ፡፡ ከዛም ዑመር (ረዲየላሁ አንሁ) ሰዎቹን፡- ‹‹እኔ ወደ መዲና ተመላሽ ነኝ!›› ይላቸውና እነሱም እንዲመለሱ ይናገራል፡፡ አቡ ዑበይዳህ ኢብኑል-ጀርራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ለዑመር (ረዲየላሁ አንሁ)፡- ‹‹ከአላህ ቀደር ነውን ሽሽቱ?›› ሲለው፡ ዑመርም (ረዲየላሁ ዐንሁ) ፡- ‹‹ካንተ ውጭ ያልለ ሰው ይህን ቃል ብሎት በነበር (በቀጣሁት ነበር)!፡፡ አዎ! ከአላህ ቀደር ወደ አላህ ቀደር እንሸሻለን›› በማለት መለሰለት” (ቡኻሪይ 5729፡ ኢርሻዱ-ሳሪ 8/383)፡፡
በዚህ ታሪክ ውስጥ ‹‹ከአላህ ቀደር ነውን ሽሽቱ?›› የሚለውና ‹‹አዎ! ከአላህ ቀደር ወደ አላህ ቀደር እንሸሻለን›› የሚለው ትልቅ ትምህርትን ይሰጡናል፡፡ እሱም፡-
• አቡ ዑበይዳህ (ረዲየላሁ ዐንሁ)፡- አላህ ከወሰነው ነገር ማንም ሊሸሽና ሊያመልጥ እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ ይህም ትክክል ነው፡፡ አላህ ከወሰነው ነገር ወደ-የትም መሸሽም አይቻልም፡፡
• ዑመር (ረዲየላሁ ዐንሁ) ደግሞ፡- ከአንድ የአላህ ቀደር ወደ ሌላ የአላህ ቀደር መሸጋገር እንደሚቻል በሌላ ጎን አስተምረዋል፡፡ ይህ ከቀደር መሸሽና ማምለጥ ሳይሆን፡ ከአንዱ ወደ ሌላው መሸጋገርን ነው የሚያሳየው፡፡ በሻም (ሶሪያ) ምድር ወረርሺኝ መከሰቱ ቀደር ከሆነ፡ በከተማይቱ ውስጥ የሌሉ ሰዎች፡ ወደሷ ላለመግባት ብለው ቢሸሹ፡ መሸሻቸውም የአላህ ቀደር ይሆናል ማለት ነው፡፡ የትምህርታችንም ጭብጥ፡- ቀደርን በቀደር መከላከል የሚል ነውና፡፡
ቀደርን በቀደር መከላከል ሲባል በሁለት መንገድ ነው፡፡ እነሱም፡-

ሀ/ ምክንያቶቹ የታዩ ግን ያልተከሰቱ፡- እንዲህ አይነት ነገሮችን እንዳይከሰቱና እውን እንዳይሆኑ፡ እኛም ለምክንያቶቹ ዝግጅት በማድረግ ገና ከመምጣቱ መከላከል እንችላለን፡፡ ለምሣሌ፡- ሊያጠቃን ጊዜና ምክንያትን የሚጠባበቅ ጠላት መኖሩ ከታወቀ፡ መጥቶ አደጋ እስኪያደርስብንና ቀድሞ እስኪያጠቃን አንጠብቅም፡፡ እኛም ለሱ የቻልነውን ህል በመዘጋጀት በተጠንቀቅ ቆመን እንጠብቀዋለን እንጂ፡፡ ለዚህ ቀጣዩ የአላህ ቃል ዋቢያችን ነው፡-
” وَأَعِدُّوا لَهُمْ مَا اسْتَطَعْتُمْ مِنْ قُوَّةٍ وَمِنْ رِبَاطِ الْخَيْلِ…” سورة الأنفال 60
“ለነሱም ከማንኛውም ኀይልና ከታጀቡ ፈረሶችም የቻላችሁትን ሁሉ…አዘጋጁላቸው…” (ሱረቱል አንፋል 8፡60)፡፡
” وَدَّ الَّذِينَ كَفَرُوا لَوْ تَغْفُلُونَ عَنْ أَسْلِحَتِكُمْ وَأَمْتِعَتِكُمْ فَيَمِيلُونَ عَلَيْكُمْ مَيْلَةً وَاحِدَةً…وَخُذُوا حِذْرَكُمْ إِنَّ اللَّهَ أَعَدَّ لِلْكَافِرِينَ عَذَابًا مُهِينًا ” سورة النساء 102
“እነዚያ የካዱት ከመሣሪዎቻችሁና ከጓዞቻችሁ ብትዘነጉና በናንተ ላይ አንዲትን መዘንበል ቢያዘነብሉ ተመኙ፤… ጥንቃቄያችሁንም ያዙ፣ አላህ ለከሐዲዎች አዋራጅን ቅጣት አዘጋጀ።” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡102)፡፡

ለ/ ክስተቱ የተፈጸመና የሆነ፡- እንዲህ አይነቱን የቀደር ክፍል ደግሞ፡ ከሆነና ከተከሰተ በኋላ አንተም እንዳይቀጥልና እንዳይዘወትር ለማንሳት ጥረት በማድረግ መከላከል ይኖርብሀል ማለት ነው፡፡ ለምሣሌ፡- አንድ ሰው በሽታ ላይ ቢወድቅና ቢታመም ቀደር ነው ብሎ ከማመኑ ጋር፡ የሚጠበቅበት እጅ ሰጥቶ መቀመጥን ሳይሆን፡ መድኃኒትን ፍለጋ ላይ ታች ማለቱ ነው፡፡ የሆነውንና የተከሰተውን የበሽታ ቀደር፡ ሰበብ ሆኖ ደግሞ በመድኃኒት አማካኝነት ወደ መጀመሪያው ማንነቱ ወደ ‹ጤና ቀደር› መቀየር ነው ብልህነቱ፡፡ ይህንንም የሚያሳየን የመልክተኛው ሐዲሥ እንዲህ ይቀርባል፡-
عَنْ أُسَامَةَ بْنِ شَرِيكٍ رضي الله عنه قَالَ: قَالَ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم أَنَتَدَاوَى « تَدَاوَوْا فَإِنَّ اللَّهَ عَزَّ وَجَلَّ لَمْ يَضَعْ دَاءً إِلاَّ وَضَعَ لَهُ دَوَاءً غَيْرَ دَاءٍ وَاحِدٍ الْهَرَمُ ». أبو داود 3855 ابن مجه 3562.
ኡሳማህ ኢብኑ ሸሪክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “የአላህ ባሮች ሆይ! መድኃኒትን ተጠቀሙ፡፡ አላህ ከአንድ በሽታ በቀር ማንኛውንም በሽታ መድኃኒት ቢያወርድለት እንጂ አልተወውም፡፡ እሱም እርጅና ነው፡፡” (አቡ ዳዉድ 3855፣ ኢብኑ ማጀህ 3562)፡፡
ከዚህ ነቢያዊ ሐዲሥ በመነሳት፡ በሽታዎች ሁሉ መድኃኒት አላቸው ብለን እናምናለን፡፡ ከመድኃኒቶች ሁሉ በላጩና ግንባር ቀደም ተጠቃሹ፡ ቁርኣንን በራስ ላይ መቅራት እና ዱዓእ ማድረግ ነው፡፡
” يَا أَيُّهَا النَّاسُ قَدْ جَاءَتْكُمْ مَوْعِظَةٌ مِنْ رَبِّكُمْ وَشِفَاءٌ لِمَا فِي الصُّدُورِ وَهُدًى وَرَحْمَةٌ لِلْمُؤْمِنِينَ ” سورة يونس 57
“እናንተ ሰዎች ሆይ! ከጌታችሁ ግሳጼ በደረቶች ውስጥም ላለው (የመጠራጠር በሽታ) መድኃኒት ለምእምናንም ብርሃንና እዝነት በእርግጥ መጣችላችሁ፡፡” (ሱረቱ ዩኑስ 10፡57)፡፡
” وَنُنَزِّلُ مِنَ الْقُرْآنِ مَا هُوَ شِفَاءٌ وَرَحْمَةٌ لِلْمُؤْمِنِينَ وَلَا يَزِيدُ الظَّالِمِينَ إِلَّا خَسَارًا ” سورة الإسراء 82
“ከቁርአንም ለምእመናን መድኀኒትና እዝነት የሆነን እናወርዳለን፤በዳዮችንም ከሳራን እንጂ ሌላን አይጨምርላቸውም።” (ሱረቱል ኢስራእ 17፡82)፡፡
“…قُلْ هُوَ لِلَّذِينَ آمَنُوا هُدًى وَشِفَاءٌ وَالَّذِينَ لَا يُؤْمِنُونَ فِي آذَانِهِمْ وَقْرٌ وَهُوَ عَلَيْهِمْ عَمًى أُولَئِكَ يُنَادَوْنَ مِنْ مَكَانٍ بَعِيد “ٍ سورة فصلت 44
“…እርሱ ለነዚያ ለአመኑት መምሪያና መፈወሻ ነው። እነዚያም የማያምኑት በጆሮዎቻቸው ውስጥ ድንቁርና ነው፤ (አይሰሙትም) እርሱም በነርሱ ላይ ዕውርነት ነው፤ እነዚያ ከሩቅ ስፍራ እንደሚጥጠሩ ናቸው።” (ሱረቱ ፉሲለት 41፡44)፡፡

ሁሉም በሽታዎች መድኃኒት አላቸው ማለት ግን፡ ሁሉም ሰው መድኃኒቱን ያውቀዋል ማለት አይደለም፡፡ በአንድ አካባቢ የታወቀ የበሽታ መድኃኒት፡ በሌላ ስፍራ ላይታወቅ ይችላል፡፡ አንድ የህክምና ባለሙያ የደረሰበትን የአንድን በሽታ መድኃኒት፡ ሌላው የህክምና ባለሙያ ላያውቀው ይችላል፡፡ ደግሞም መድኃኒትነቱ የታወቀ ሆኖ፡ ግን ከአወሳሰድና አጠቃቀም ጉድለት በበሽተኛው ላይ ላይሰራ ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን በሽታው መድኃኒት የለውም ማለት አይደለም!፡፡ በበፊት ጊዜ ስንት መድኃኒት የላቸውም የተባሉ በሽታዎች ዛሬ ተገኝቶላቸዋል፡፡ ዛሬ ያልተደረሰባቸው ደግሞ ነጌ….፡፡ የአላህ መልክተኛ እንዲህ ላሉ፡-
عنَ عَبْدُ اللهِ بْنُ مَسْعُودٍ رضي الله عنه قال: قَالَ رَسُولُ اللهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ
وَسَلَّمَ: ” إِنَّ اللهَ عَزَّ وَجَلَّ لَمْ يُنْزِلْ دَاءً إِلَّا وَقَدْ أَنْزَلَ مَعَهُ دَوَاءً، جَهِلَهُ مِنْكُمْ مَنْ جَهِلَهُ، وَعَلِمَهُ مِنْكُمْ مَنْ عَلِمَهُ “رواه أحمد 4267.
ዐብዱላህ ኢብኒ መስዑድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “አላህ ምንንም በሽታ አላወረደም (አልፈጠረም) ከሱ ጋር አብሮ መድኃኒትን ያወረደ (የፈጠረ) ቢሆን እንጂ፡፡ ይህንንም ከናንተ ውስጥ ያላወቀው አላወቀውም፡፡ ያወቀው ሰው ደግሞ ውቀዋል፡፡” (ሙስነድ ኢማሙ አሕመድ 4267)፡፡
በዚህ መልኩ አንድን ቀደር በሌላ ቀደር መመለስ እንዳለብን ታዝዘን እያለ፡ መሳነፍና እጅ መስጠት ያስወቅሳል፡፡ የሆኑ ነገራትን ቀደር ናቸው ብሎ አምኖ መቀበል አንድ ነገር ሲሆን፡ በሌላ ቀደር መከላከል ደግሞ ሌላ ነገር ነው፡፡ መከላከላችን ተሳካም አልተሳካም ሁሉም ቀደር ናቸው፡፡ በቀዷ ወል-ቀደር ማመናችን ሰበብን ከመጠቀም በፍጹም ሊያሳንፈን አይገባም!፡፡ የነገራትን ፍጻሜ ከወዲሁ ማስተንተን፣ መልካሙን ለማግኘት መልፋት፣ አሸናፊ ሆኖ ለመገኘት መትጋት፣ ከመጥፎና ከጎጂ ነገራት መራቅና መጠንቀቅ የእምነታችን ቋሚ መርሆች ናቸው፡፡
አላህ የበለጠውን ዐዋቂ ነው፡፡
ይቀጥላል
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡