ለምን ይገደሉ?

840 Views


(አቡ ሀይደር)

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኛ በሆነው፡፡

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡

” وَلَا تَقْتُلُوا النَّفْسَ الَّتِي حَرَّمَ اللَّهُ إِلَّا بِالْحَقِّ وَمَنْ قُتِلَ مَظْلُومًا فَقَدْ جَعَلْنَا لِوَلِيِّهِ سُلْطَانًا فَلَا يُسْرِفْ فِي الْقَتْلِ إِنَّهُ كَانَ مَنْصُورًا ” سورة الإسراء 33

“ያቺንም አላህ ያወገዛትን ነፍስ ያለ ሕግ አትግደሉ፤ የተበደለም ሆኖ የተገደለ ሰው፣ ለዘመዱ (በገዳዩ ላይ) በእርግጥ ስልጣንን አድርገናል፤ በመግደልም ወሰንን አይለፍ፤ እርሱ የተረዳ ነውና።” (ሱረቱል ኢስራ 33)፡፡
ትላንት በአላህ ፈቃድ፡ በኢስላም በሃይማኖት ማስገደድ የለም! በማለት፡ በተወሰነ መልኩ ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾችን ተመልክተናል አልሐምዱ ሊላህ፡፡

ዛሬ ደግሞ የምንመለከተው፡- በግድያ ዙሪያ የተነገሩ አንቀጾችንና፡ የጠላትን ከንቱ የማሳሳት ሙከራ በአላህ ፈቃድ እውነታውን በማብራራት ነው፡፡

ክስ ቁጥር አንድ፡-

” وَاقْتُلُوهُمْ حَيْثُ ثَقِفْتُمُوهُمْ وَأَخْرِجُوهُمْ مِنْ حَيْثُ أَخْرَجُوكُمْ وَالْفِتْنَةُ أَشَدُّ مِنَ الْقَتْلِ وَلَا تُقَاتِلُوهُمْ عِنْدَ الْمَسْجِدِ الْحَرَامِ حَتَّى يُقَاتِلُوكُمْ فِيهِ فَإِنْ قَاتَلُوكُمْ فَاقْتُلُوهُمْ كَذَلِكَ جَزَاءُ الْكَافِرِينَ ” سورة البقرة 191

“ባገኛችኋቸውም ስፍራ ሁሉ ግደሉዋቸው፡፡ ከአወጧችሁም ስፍራ አውጧቸው፡፡ መከራም ከመግደል ይበልጥ የበረታች ናት፡፡ በተከበረው መስጊድም ዘንድ በርሱ ውስጥ እስከሚጋደሉዋችሁ ድረስ አትጋደሉዋቸው፡፡ ቢጋደሉዋችሁም ግደሉዋቸው፤ የከሓዲዎች ቅጣት እንደዚህ ነው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 191)፡፡

አንዱና ዋነኛው ክስ የማቅረቢያ ጥቅሳቸው ነው፡፡ አንቀጹ ስለነማን ያወራል? ለምን ይገደላሉ? መች ይገደላሉ? እስከምን ድረስ ነው ግድያው? አላማውስ ምንድነው? የሚሉትን ነጥቦች ለማወቅም ሆነ ለመረዳት ዝግጁዎች አይደሉም፡፡ እነሱ ቶሎ ‹‹ወደ ገደለው›› በመግባት ብቻ ብዥታ ለመልቀቅ ነው፡፡ እውነታውን ማብራራት ደግሞ የኛ ግዳጅ ስለሆነ፡ ከዚህ ቀጥሎ ምላሹን እንከታተል፡፡

መልስ፡-

የዚህን አንቀጽ ሙሉ ሀሳብ ለማግኘትና ለመረዳት፡ ከፊቱና ከኋላው ያሉትን ጥቅሶች መመልከቱ ወሳኝ ነው፡፡ ይህችን አንቀጽ ብቻ ቆንጥሮ ማውጣት ለራስ ተሳስቶ ሌላውንም ማሳሳት ይሆናል፡፡ በመሆኑም ከአንቀጽ 190 በመጀመር እንመልከተው፡-

” وَقَاتِلُوا فِي سَبِيلِ اللَّهِ الَّذِينَ يُقَاتِلُونَكُمْ وَلَا تَعْتَدُوا إِنَّ اللَّهَ لَا يُحِبُّ الْمُعْتَدِينَ ” سورة البقرة 190

“እነዚያንም የሚጋደሉዋችሁን (ከሓዲዎች) በአላህ መንገድ ተጋደሉ፡፡ ወሰንንም አትለፉ፤ አላህ ወሰን አላፊዎችን አይወድምና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 190)፡፡

 • ‹‹እነዚያንም የሚጋደሉዋችሁን (ከሓዲዎች)›› የሚለው፡ እነማንን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ነው፡፡ የአንቀጹ መልእክት እኛን ስለሚጋደሉ ሰዎች እንጂ፡ ሰላምን ፈልገው አርፈው የተቀመጡትን ወይንም ከኛ ጋር ጦር ላለመማዘዝ ቃል የተጋቡትን ሰዎች አይደለም፡፡ አንቀጹ በግልጽ ‹‹የሚጋደሉዋችሁን›› ሰዎች ነው ያለው፡፡ ታዲያ ምኑ ላይ ጥፋቱ? ሊጋደሉን የመጡ ሰዎችን አርፈን ቁጭ ብለን መጠበቅ አለብን? መስጂዶቻችንን ሲያፈራርሱ፣ ደማችንን ሲያፈሱ፣ ንብረታችንን ሲወርሱ፣ በሴቶቻችን ክብር ሲረማመዱ ተመልካች መሆን አለብን? መፍትሄው ግን፡ እኛም እነሱን መጋደል አለብን የሚለው ነው፡፡ ደግሞም አካሄዳችን እንዴት መሆን እንዳለበት ሲገልጽ፡- ‹‹በአላህ መንገድ ተጋደሉ›› ይላል፡፡ አዎ የመጋደሉ አላማ ይህ ነው፡፡ ለስሜታችን ወይም ለዘራችን ክብር ሳይሆን፡ በአላህ መንገድ መሆን አለበት፡፡ በአላህ መንገድ ሲባል፡- የአላህ ቃል የበላይ እስኪሆን፣ ፍትህ እስኪሰፍን እና በደል እስኪጠፋ፣ በሃይማኖታችን ሰበብ የሚደርስብን ጥቃት እስኪቆም ድረስ ማለት ነው፡፡ ከዛም በመቀጠል አንቀጹ፡- ‹‹ወሰንንም አትለፉ፤ አላህ ወሰን አላፊዎችን አይወድምና›› ይላል፡፡ የፍትህ ጥግ ማለት እንዲህ ነው፡፡ ‹‹ወሰንን አትለፉ›› የሚለው ኃይለ ቃል፡ አራት ነገሮችን በውስጡ ያቅፋል፡፡ እነሱም፡-
 1. ያልተጋደሉንን ሰዎች መጋደል ወሰን ማለፍ ነው፡፡
 2. ሰዎች መጋደሉን ሳይጀምሩ ቀድሞ መጀመሩም ወሰን ማለፍ ነው፡፡
 3. የሚገደሉ ሰዎችን፡ ከመደበኛው ግድያ ውጪ የሰውነት አካልን መቆራረጥ በራሱ ወሰን ማለፍ ነው፡፡
 4. በዚህ የመገዳደል ወቅት ላይ እንዳይነኩ የተከለከልናቸው ሰዎች አሉ፡፡ እነሱንም መግደል ወሰን ማለፍ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ሴቶችን፣ ህጻናትን፣ በእድሜ የገፉ አዛውንትን፣ ባህታውያንን፣ እንሰሳትን…በሙሉ፡፡ (ተፍሲር ኢብኑ ከሢር፡ ሱረቱል በቀራህ 190)፡፡

  በተለይ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ታላቁ ሶሐባ (የነቢዩ ባልደረባ) ዐብዱላህ ኢብኑ-ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ይላል፡-

  عن ابن عباس: ” وقاتلوا في سبيل الله الذين يُقاتلونكم ولا تعتدوا إنّ الله لا يحب المعتدين ” يقول: لا تقتلوا النساء ولا الصِّبيان ولا الشيخ الكبير وَلا منْ ألقى إليكم السَّلَمَ وكفَّ يَده، فإن فَعلتم هذا فقد اعتديتم. جامع البيان في تأويل القرآن ፡ محمد بن جرير الطبري.

  “ሴቶችን፣ ህጻናትን፣ አዛውንትን፣ እጁን ከናንተ በመሰብሰብ ሰላምታን ያቀረበ ሰውን ሁሉ እንዳትገድሉ፡፡ ይህን ካረጋችሁ በርግጥም ወሰን አልፋችኋል” (ተፍሲሩ-ጠበሪይ፡ ሱረቱል በቀራህ 190፡ ቁ 3094)፡፡

  በዚህ መልኩ ወሰን እንዳናልፍ ከከለከለን በኋላ አንቀጹን ሲዘጋው ‹‹አላህ ወሰን አላፊዎችን አይወድምና›› አለን፡፡ አላሁ አክበር!!

  በዚህ መልኩ እኛን መጋደል ስለፈለጉ ሰዎች፡ የኛ አቋም ምን መሆን እንዳለበት ካብራራ በኋላ፡ ወደ ቀጣዩ አንቀጽ በመሄድ እነዚህን ወሰን ያለፉ አካላት እንዴትና የት እንደሚገደሉ አስረዳ፡፡ ቀጣዩ አንቀጽም እንዲህ ይላል፡-

  ” وَاقْتُلُوهُمْ حَيْثُ ثَقِفْتُمُوهُمْ وَأَخْرِجُوهُمْ مِنْ حَيْثُ أَخْرَجُوكُمْ وَالْفِتْنَةُ أَشَدُّ مِنَ الْقَتْلِ وَلَا تُقَاتِلُوهُمْ عِنْدَ الْمَسْجِدِ الْحَرَامِ حَتَّى يُقَاتِلُوكُمْ فِيهِ فَإِنْ قَاتَلُوكُمْ فَاقْتُلُوهُمْ كَذَلِكَ جَزَاءُ الْكَافِرِينَ ” سورة البقرة 191

  “ባገኛችኋቸውም ስፍራ ሁሉ ግደሉዋቸው፡፡ ከአወጧችሁም ስፍራ አውጧቸው፡፡ መከራም ከመግደል ይበልጥ የበረታች ናት፡፡ በተከበረው መስጊድም ዘንድ በርሱ ውስጥ እስከሚጋደሉዋችሁ ድረስ አትጋደሉዋቸው፡፡ ቢጋደሉዋችሁም ግደሉዋቸው፤ የከሓዲዎች ቅጣት እንደዚህ ነው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 191)፡፡
 • ‹‹ባገኛችኋቸውም ስፍራ ሁሉ ግደሉዋቸው›› በማለት፡ ልክ እነሱ እኛን በየትም ስፍራ ለመጋደል ቆርጠው እንደተነሱት፡ እናንተም ባገኛችኋቸው ስፍራ ግደሏቸው አለ፡፡ ደግሞም፡- ‹‹ከአወጧችሁም ስፍራ አውጧቸው›› በማለት፡ ከሀዲያን ሙስሊሞቹን (ሶሐቦቹን) ከመካ እንዳበረሯቸው፡ እነሱም እንዲያስወጧቸው ታዘዙ፡፡ ደግሞም የነሱ በአላህ ማጋራት፡- ‹‹መከራም ከመግደል ይበልጥ የበረታች ናት›› በማለት፡ የነሱ የጣኦት አምልኮ ተግባር ከሚደርስባቸው ግድያ በላይ የሆነ ጥፋት እንደሆነ ገለጸ፡፡ መከራ(በአላህ ማጋራት) ለአንድ ሰው ከሞት የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ ስጋዊ ሞት ምድራዊ ቆይታን ያሳጥራል እንጂ፡ የመጨረሻውን ዓለም አያጠፋም፡፡ በአላህ ማጋራት ግን፡ ምንም እዚህ ምድር ላይ የኖሩትን ያህል ቢኖሩ፡ ነጌ መቋረጥ ለሌለው ዘላለማዊ ጀሀነም እሳት የሚዳርግ ጥፋት ነውና፡ የነሱ በመካ ውስጥ ጣኦት የማምለክ ኃጢአት (መከራ) ከሚደርስባቸው የነፍስ ግድያ አንጻር እጅግ የከፋ ድርጊት እንደሆነ ገለጸ፡፡ እንደዛም ሆኖ ደግሞ፡- ‹‹በተከበረው መስጊድም ዘንድ በርሱ ውስጥ እስከሚጋደሉዋችሁ ድረስ አትጋደሉዋቸው›› ይላል፡፡ የተከበረው መስጂድ ‹‹መስጁዱል ሐረም›› (የሙስሊሞች የሶላት ቂብላ) አላህ ዘንድ እንዲሁም ሙስሊሞች ዘንድ እጅግ የተከበረ ከመሆኑ የተነሳ፡ ጠላት ጦር አንስቶ እስኪጋደላቸው ድረስ እንዳይጋደሏቸው ታዘዙ፡፡ ጠላት ከጀመረ ግን፡- ‹‹ቢጋደሉዋችሁም ግደሉዋቸው፤ የከሓዲዎች ቅጣት እንደዚህ ነው›› በማለት፡ እነሱም አጸፋውን መመለስ እንዳለባቸው ተነገራቸው፡፡ ለከሀዲዎች የሚገባቸው ቋንቋ ይሄ ብቻና ብቻ ነው፡፡
  ይህን አንቀጽ በዚህ ከቋጨ በኋላ በቀጣዩ ላይ ደግሞ እንዲህ ይላል፡-

  ” فَإِنِ انْتَهَوْا فَإِنَّ اللَّهَ غَفُورٌ رَحِيمٌ ” سورة البقرة 192
  “ቢከለከሉም አላህ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 192)፡፡

  ‹‹ቢከለከሉም›› የሚለው ቃል፡ ሁለት ትርጉሞችን ያቅፋል፡-
  አንደኛ፡- እናንተን ከመጋደል ቢቆጠቡ ማለት ሲሆን፡ ያ ከሆነ ደግሞ እናንተም ተቆጠቡ፡ አትጋደሏቸው የሚል ይሆናል፡፡

  ሁለተኛ፡- ከነበሩበት የጣኦት አምልኮ ታቅበው ወደ አላህ መንገድ በፈቃደኝነትና በተውበት ቢመለሱ የሚል ሲሆን፡ ያ ከሆነ ደግሞ ለዚህ ድርጊታቸው የሚገጥማቸው ምን እንደሆነ እዛው ላይ እንዲህ በማለት መልሱን ሰጣቸው፡- ‹‹አላህ መሓሪ አዛኝ ነው››፡፡ የሰዎች ወንጀል የቱንም ያህል የበዛና የከፋ ቢሆንም፡ ከአላህ ራሕመት እና ምህረት ጋር ሊስተካከል አይችልም፡፡ የሱ እዝነቱ ዓለሙን በሞላ ያካለለ ነውና (ሱረቱ ጋፊር 7)::

  ከዚህ በኋላ የቀረው አንቀጽ ደግሞ፡- የዚህ የጦርነቱ የመጨረሻ ዓላማና ግብ እስከምን ድረስ ነው የሚለውን በማብራራት የሚቋጭ ነው፡፡ እስኪ እንየው፡-

  ” وَقَاتِلُوهُمْ حَتَّى لَا تَكُونَ فِتْنَةٌ وَيَكُونَ الدِّينُ لِلَّهِ فَإِنِ انْتَهَوْا فَلَا عُدْوَانَ إِلَّا عَلَى الظَّالِمِينَ ” سورة البقرة 193
  “ሁከት እስከማይገኝና ሃይማኖት ለአላህ ብቻ እስከሚኾን ድረስ ተጋደሉዋቸው፡፡ ቢከለክሉም ወሰንን ማለፍ፤ በበዳዮች ላይ እንጂ የለም (ወሰን አትለፉባቸው)፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 193)፡፡

‹‹ሁከት እስከማይገኝና ሃይማኖት ለአላህ ብቻ እስከሚኾን ድረስ ተጋደሉዋቸው›› የሚለው የመጨረሻን ግብ የሚገልጽ ነው፡፡ የኛ ዓላማ መሆን ያለበት፡ የሰው ዘር እንዲጠፋ፣ ወይም ብሄርተኝነት እንዲስፋፋ ሳይሆን፡ የአላህ ዲን የበላይ እንዲሆን ነው፡፡ የጣኦት አምልኮ ተንኮታኩቶ፡ እውነትም ነግሶ በምድር ላይ እንዲታይ፡ አማኞችም ጌታቸውን የማምለክ ነጻነታቸው ተጠብቆ እንዲቆይ ነው፡፡ ጠላት እንዳይበታትነን ሁሌም በንቃት መስራት ይጠበቅብናል፡፡

 • ‹‹ሃይማኖት ለአላህ ብቻ እስከሚኾን ድረስ ›› ማለትም ትርጉሙ ይኸው ነው፡፡ የአላህ ሸሪዓ በምድር ላይ ነግሶ፡ የሰዎች ነጻነት ታውጆ፡ የኩፍር የበላይነት አክትሞ እስኪንኮታኮት ድረስ ማለት ነው፡፡
  አንዳንድ ወገኖች፡- ሰዎች ሁሉ እስኪሰለሙ ድረስ ለማለት ነው ይሉናል፡፡ እነሱ እንደሚሉት ከሆነማ፡- ‹‹ሃይማኖት ለአላህ ብቻ እስከሚኾን ድረስ›› ከማለት ይልቅ፡ ‹‹ሰዎች ሁሉ ሃይማኖተኛ እስኪሆኑ ድረስ›› አይልም ነበር ታዲያ? ከየት ያመጣችሁት ግንዛቤ ነው? እንደውም ቀጣዩ ቃል ይህን ሃሳብ ያፈርስባችኋል፡፡

 • ‹‹ቢከለክሉም›› የሚለው ሁለት ትርጉምን ያቅፋል፡፡
  አንደኛ፡- ከዚህ ካሉበት የጣኦት አምልኮ ተከልክለው ኢስላምን በፈቃደኝነት ቢቀበሉ የሚል ሲሆን፡
  ሁለተኛው፡- በነበሩበት የክህደት እምነት መዘውተርን ፈልገው፡ ኢስላምን ባይመርጡና ነገር ግን ለሚያስተዳድረው ኢስላማዊ መንግስት ያለባቸውን ‹‹ግብር›› በአግባቡ ቢከፍሉ የሚል ሲሆን፡ ከሁለት አንዱን ቢተገብሩ ውጤቱ ደግሞ፡-

 • ‹‹ ወሰንን ማለፍ፤ በበዳዮች ላይ እንጂ የለም (ወሰን አትለፉባቸው)›› በማለት፡ በነሱ ላይ ወሰን ማለፍን ይከለክላል፡፡ (ተፍሲር ቁርጡቢይ፡ ጃሚዑል አሕካም)፡፡

  እንደሰዎቹ ግንዛቤ፡ ሙስሊም እስኪሆኑ ድረስ ከተባለማ፡ ካልሰለሙ ግደሏቸው እንጂ፡ ወሰን አትለፉባቸው እንዴት ይባላል? ስለዚህ ‹‹ሃይማኖትም ለአላህ እስኪሆን ድረስ›› ማለት፡- ሰዎች ያለ ፈቃዳቸው አምነው እስኪቀበሉ ማለት አይደለም፡፡ ትላንት በጉዳዩ ላይ በመጠኑ ተመልክተነዋል)፡፡
  ነገር ግን መልእክቱ፡- ፈቅደውና ወደው ኢስላምን እስኪቀበሉ፡ ያ ካልሆነም ለኢስላማዊው መንግስት የሚጣልባቸውን ግብር እስኪከፍሉ ድረስ ነው የሚለውን ያቀፈ ነው፡፡

ወንድምና እህቶች ከቁጥር 190-193 ያለውን የቅዱስ ቁርኣን አንቀጽ በመጠኑም ቢሆን እንዲህ ከተረዳነው፡ ታዲያ የታለ ሰዎች እስኪሰልሙ ድረስ ግደሏቸው የሚለው? የታለ ከመሬት ተነስታቹ ሰው አጥፉ የሚለው? መልሱን ለህሊና፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡

ሌሎች አንቀጾችን ደግሞ እንዳይረዝምባችሁ በማለት እዚህ ላይ ማቆሙን ስለ መረጥኩ፡ በቀጣዩ ደግሞ ቀሪዎቹ ላይ በአላህ ፈቃድ እመለስበታለሁ፡፡ ነገር ግን ከመጽሀፍ ቅዱስ አንድ ጥቅስ ጠቅሼ ልለያችሁ፡፡ እንዲህ ይላል፡-

‹‹እግዚአብሔርም፡- በከተማይቱ በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ፥ በመካከልዋም ስለ ተሠራው ርኵሰት ሁሉ በሚያለቅሱና በሚተክዙ ሰዎች ግምባር ላይ ምልክት ጻፍ አለው። እኔም እየሰማሁ ለሌሎቹ፡- እርሱን ተከትላችሁ በከተማይቱ መካከል እለፉ ግደሉም፤ ዓይናችሁ አይራራ አትዘኑም፤ሽማግሌውንና ጐበዙን ቈንጆይቱንም ሕፃናቶቹንና ሴቶቹን ፈጽማችሁ ግደሉ፤ ነገር ግን ምልክቱ ወዳለበት ሰው ሁሉ አትቅረቡ፤ በመቅደሴም ጀምሩ አላቸው። በቤቱም አንጻር ባሉ ሽማግሌዎች ጀመሩ። እርሱም። ቤቱን አርክሱ፥ በተገደሉትም ሰዎች አደባባዮችን ሙሉ፤ ውጡ አላቸው። እነርሱም ወጥተው በከተማይቱ ገደሉ።›› (ትንቢተ ሕዝቅኤል ምዕ9 ቁ4-7)፡፡

የአላህ ሰላምና መልካም ውዳሴ በነቢያችንና በቤተሰቦቻቸው፡ ፈለጋቸውንም በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን፡፡