ህመምተኛን መጎብኘት በኢስላም

ሼር ያድርጉ
486 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡

عن أبي هريرة قال: قال رسول الله صلى الله عليه وسلم: «ثلاث كلهن حق على كل مسلم: عيادة المريض، واتباع الجنائز، وتشميت العاطس إذا حمد الله عز و جل» رواه الإمام أحمد.
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ሶስት ነገሮች በያንዳንዱ ሙስሊም ላይ የተገቡ ተግባራት ናቸው፡ በሽተኛን መጎብኘት፣ የሞተን (ጀናዛ) መሸኘት፣ ላስነጠሰ ሰው አልሐምዱ ሊላህ ካለ በመልካም ዱዓ ማድረግ ” (አሕመድ የዘገቡት)፡፡

የአላህ ነቢይ (ዐለይሂ ሶላቱ ወስ-ሰላም) በዚህ ቦታ ማስተላለፍ የፈለጉት ሶስቱን ትምሕርቶች ስለሆነ ነው እንጂ፡ ሙስሊም በሌላው ሙስሊም ላይ ያለው ሐቅ ሶስት ብቻ ስለሆነ አይደለም፡፡ በሌሎች ሐዲሦች እንደተረጋገጠው አምስትና ስድስት የሚሆኑ ሐቆችም ተዘርዝረዋል፡፡

‹‹የሙስሊም ሐቅ›› ሲባል፡- አንዱ ሙስሊም ለሌላው ወንድሙ (እህቱ) በነፍስ-ወከፍ ሊፈጽመው የሚገባ ግዴታው፣ ወይንም የተወሰኑት ላይ ብቻ የሚጣል ግዴታ፣ ካልሆነም ሊተገበር የሚገባው ጠንካራ ሱና ማለት ነው፡፡

ህመምተኛን መጠየቅ፡-

ይህ ሙስሊም ህመምተኛ በጤነኛው ላይ ያለው መብቱ ነው፡፡ ወንድሞችና እህቶች ከታመሙ ልንጎበኛቸው ይገባል፡፡ ምንም ልናደርግላቸው ባንችል እንኳ፡ እነሱን ለመጎብኘት መገኘታችን ለነሱ ግማሽ ጤና ነው፡፡ በሙስሊም ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው እንዳልተረሱ ማወቃቸው ብቻ ያስደስታቸዋል፡፡ መተባበርንና መተዛዘንን የደነገገው ኢስላም ያኮራቸዋል፡፡ የአክፍሮት ኃይላት በየሆስፒታሉ እየዞሩ ወንድምና እህቶቻችን በኛ ቦታ ከጎበኙብን ውጤቱ አደጋ ነው፡፡ የነሱ ጉብኝት ለስጋዊ ጤንነት ቢሆንም ዘላለማዊ ክስረትንም ተሸክመው ነው የሚሄዱት፡፡ ነጌ ከሆስፒታሉ ሲወጣ ከበፊት ወንድሞችና እህቶች ጋር የነበረው ወዳጅነት ይሻክራል፡፡ መራራቅና ለጠላት ተንኮል ሰለባ መሆንን ያስከትላል፡፡ በመሆኑም ህመምተኛን በመጎብኘት ላይ ልንጠናከርበት ይገባል፡፡ እኛ እንኳ ህመምተኛው ወዳለበት ስፍራ መገኘት ባንችል፡ ሌሎች እንዲገኙና ቦታው እንዲሸፈን ያድርጉ፡፡ በስልክም ሆነ በሌላ መንገድ ህመምተኛውን በማግኘት እናጽናናው፡፡ ህመምተኛን መጎብኘት የፈለገ ሰው ከቻለ ቀጥሎ ያሉትን አዳቦች ቢያሟላ ተወዳጅ ነው፡-

1. በር አይደብድብ፡- ወደ ህመምተኛው ሰው ቤት ስትሄዱ ውስጥ ያለውን ሰው በሚያስደነግጥ መልኩ በሩን በኃይል አይደብድቡ፡፡ ከውስጥ ማነው? ተብለው ሲጠየቁም ማንነትዎን አይደብቁ፡፡ ሳይፈቀድልዎት አይግቡ፡፡ ተፈቅዶልዎት ከገቡም አይንዎትን ሰበር ያድርጉ፡፡

2. ህመምተኛውን ለመጠየቅ አመቺ ሰዓታትን ይምረጡ፡፡ እነሱ ተሰብስበው በሚመገቡበት ወይም የውጭ ሰው በማይጠበቅበት ሰዓት አይሂዱ፡፡

3. ህመምተኛውን ሊጎበኙ ከመጡ ከወደ ጎኑ በመጠጋት አመቺ በሆነ መልኩ ይቀመጡ፡፡ እጆትንም ግንባሩ ላይ በማሳረፍ ስለ-ህመሙ ሁኔታና አሁን ምን እንደሚያስፈልገው ይጠይቁት፡፡ መልካም አክብሮት የፈውስ አንድ አካል ነውና፡፡ ከቤት ሰው ተሸክሟቸው ሆስፒታል የሚወሰዱ ህመምተኞች በሐኪሙ ፊት እራሳቸውን ችለው ሲቆሙ አልገጠማችሁንም? መፍትሄ የሚሰጥ ባለሙያ ዘንድ መጥቻለሁ ብለው ስለሚያስቡ ህመሙ በተወሰነ መልኩ ጋብ ይላል፡፡

4. ከተመቾት ህመምተኛውን መጎብኘት ይደጋግሙ፡፡ ገና በመጀመሪያው ጉብኝትዎት ብቻ ‹‹አላህ ያሽርህ›› ብለው አይጥፉበት፡፡ ህመም እየባሰ ወይም እየሻረ ሊሄድ የሚችል ነገር ነውና፡፡

5. የርሶ በህመምተኛው ቤት መቆየት ታማሚውን ወይም ቤተሰቦቹን ያስቸግራል ብለው ከገመቱ ብዙም አይቆዩ፡፡ የርሶ በቦታው መኖር ግን ጠቀሜታ ካለው ይቆዩ፡፡

6. ከቻሉም ተከታዩን ዱዓእ ሰባት ጊዜ በመደጋገም ያድርጉለት፡- ‹‹አስአሉላሀ-አል ዐዚም፣ ረበል-ዐርሺል ዐዚም፣ አን-የሽፊየክ/ኪ››፡፡ እንዲሁም ሱረቱል ፋቲሐህ፣ አል-ፈለቅ እና አን-ናስን ይቅሩበት፡፡ ይህንን ዱዓእ ህመምተኛን ጎብኝቶ ከልቡ አምኖ ያደረገ ሰው አላህ ህመምተኛውን ያሽረዋል በማለት ተወዳጁ ነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነግረውናል፡፡ (አቡ ዳዉድ 3108፣ ቲርሚዚይ 2227፣ ነሳኢይ ሱነኑል-ኩብራ 10883፣ ሶሒሕ ኢብኑ-ሒባን 2975)፡፡

7. ህመምተኛውን ልቡን በተስፋ ይምሉት፡፡ አላህ እንደሚያሽረው በመንገር ያጽናኑት፡፡ እስከዛም ሶብር ካደረገ ታላቅ ምንዳ እንዳለው ያበስሩት፡፡ ተስፋ መቁረጥ የሙስሊም ባሕሪ እንዳልሆነ በመንገር ተስፋውን ያድሱለት፡፡

8. ህመምተኛውን ለመጎብኘት የመጡ ሰዎች በዛ ካሉ በመሐል ለጭቅጭቅ መንስኤ የሚሆኑ ነገሮችን ይራቁ፡፡ በናንተ ጭቅጭቅ ለህመምተኛው ሌላ በሽታን እንጂ ማጽናናትን አይጨምርለትምና፡፡

እስካሁን ያየናቸው የህመምተኛውን ሙስሊም ሐቅ ሲሆን፡ ጎብኚዎች ደግሞ በዚህ ስራቸው አላህ ዘንድ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የሚያመላክቱ ነቢያዊ ሐዲሦችን በመጠኑ እንመለከታለን፡-

አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ነጌ የውሙል ቂያም አላህ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የአደም ልጅ ሆይ! ታምሄ ሳለሁ አልጎበኘኸኝምሳ?›› ባርያውም፡- ‹‹ጌታዬ ሆይ! አንተ የዓለማቱ ጌታ ሆነህ እንዴት ነው ታመህ የምጎበኝህ?›› ይላል፡፡ አላህም፡- ‹‹እንትና ባሪያዬ ታሞ ሳለ አንተ አለመጎብኘትህን አታውቅምን? እሱን ብትጎበኘው እኔን እሱ ዘንድ እንደምታገኘኝ አታውቅምን?›› ይለዋል፡፡” (ሙስሊም የዘገበው)፡፡

በዚህ ሐዲሥ መሰረት በሽተኛን መጎብኘት አላህ ዘንድ ታላቅ ጥቅም እንዳለው እንረዳለን፡፡ ኢማሙ ነወዊይ (ረሒመሁላህ) እንዳብራሩት፡ አላህን እዛ ማግኘት ማለት፡- የዚያራን አጅርና ክብር መጎናጸፍ ማለት ነው፡፡

ሠውባን (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ህመምተኛን የጎበኘ ሰው በጀነት የበሰሉ ፍሬዎች ጥላ ስር ከመሆን አይወገድም” (ሙስሊም)፡፡

አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ዛሬ ከመሐከላችሁ የጾመ ማነው? ሲሉ ፡ አቡ በከር-ሲዲቅ(ረዲየላሁ ዐንሁ) ‹‹እኔ›› አለ፡፡ ዛሬ ህመምተኛን የጎበኘ ማነው? ሲሉ፡ አቡ በከር-ሲዲቅ(ረዲየላሁ ዐንሁ) ‹‹እኔ›› አለ፡፡ ዛሬ ጀናዛን(አስከሬን) የሸኘ ማነው? ሲሉ ፡ አቡ በከር-ሲዲቅ(ረዲየላሁ ዐንሁ) ‹‹እኔ›› አለ፡፡ ዛሬስ ምስኪንን የመገበ ማነው? ሲሉ ፡ አቡ በከር-ሲዲቅ(ረዲየላሁ ዐንሁ) ‹‹እኔ›› አለ፡፡ ከዛም እሳቸው፡- ‹‹እነዚህ ተግባራት በአንድ ሰው ላይ አይሰባሰቡም ሰውየው ጀነት የገባ ቢሆን እንጂ›› አሉ” (ሙስሊም)፡፡

ዐሊይ ኢብኑ አቢ-ጧሊብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ አሉ፡- “የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው፡- ‹‹አንድ ሙስሊም ሌላውን ሙስሊም በንጋቱ ሰዓት አይጎበኘውም፡ እስኪያመሽ ድረስ ሰባ ሺህ መላእክት ዱዓእ የሚያደርጉለት ቢሆን እንጂ፣ በምሽቱ ወቅትም ከጎበኘው እስኪያነጋ ድረስ ሰባ ሺህ መላእክት ዱዓእ የሚያደርጉለትና ከጀነት የሆነ የበሰሉ ፍሬዎች ቢኖሩት እንጂ››” (ቲርሚዚይ 969)፡፡ አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ህመምተኛን የጎበኘ ሰው፡ ከሰማይ ተጣሪ እንዲህ ብሎ ይጣራል፡- ‹‹ኑሮህ ያማረ፣ መንገድህ የተስተካከለ፣ ለጀነት ክቡር ስፍራ የታጨህ ሁን›› ይለዋል” (ቲርሚዚይ 2008)፡፡

ሀሩን ኢብኑ አቢ-ዳዉድ (ረሒመሁላህ) እንዲህ አለ፡- “አነስ ኢብኑ ማሊክ ዘንድ መጣሁና እንዲህ አልኩት ‹‹አባ ሐምዛ ሆይ! አንተን መጎብኘት እየፈለግን ቦታው ግን ራቀብን›› እሱም ራሱን ቀና አድርጎ፡- የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማሁ ‹‹ማንኛውም ሰው ህመምተኛን የሚጎበኝ ከሆነ የሚመላለሰው በራሕመት ውስጥ ነው፣ ህመምተኛው ጎን ከተቀመጠ ራሕመት ይሸፍነዋል›› እኔም፡- ‹‹የአላህ መልክተኛ ሆይ! ይህ ሁሉ ለጤነኛው ነው፡ ለህመምተኛውስ ምን አለው?›› ስላቸው፡ ‹‹ኃጢአቱ ይሰረዝለታል›› ብለው መለሱልኝ በማለት ነገረኝ” (አሕመድ 12782)፡፡

Shortlink http://q.gs/EwnXx